የኢትዮጵያ መንግስት በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች ላሉ ኤርትራውያን ስደተኞች “የከተማ ስደተኝነት” እውቅና ሊሰጥ ነው

1

በበእምነት ወንድወሰን

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል በማይ ዓይኒ እና አዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች፤ “በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት” እውቅና እንደሚሰጥ አስታወቀ። የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የፌደራል መንግስት ተቋም ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ለኤርትራውያን ስደተኞች ከሚሰጠው እውቅና በተጨማሪ ስደተኞቹን በአማራ ክልል እየተቋቋመ ባለ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ ለማስፈር እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጿል።

የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ይህን ያለው በኢትዮጵያ ያሉ የኤርትራ ስደተኞችን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ሐምሌ 7፤ 2013 ባወጣው መግለጫ ነው። “በትግራይ ክልል ውስጥ በኤርትራ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የተመለከቱ ዘገባዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየወጡ ነው” ያለው ተቋሙ፤ ህወሓት በስደተኞቹ ላይ ላይ ሲያደርሳቸው ነበር ያላቸውን ጥቃቶች በዝርዝር በመጥቀስ ወንጅሏል። 

“የህወሓት ኃይሎች በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ማድረስ የጀመሩት ከህዳር 2013 ጀምረው ነው” ሲል የሚከስሰው ኤጀንሲው፤ ለዚህም ሽመልባ እና ህጻጽ በተባሉ የስደተኛ ጣቢያዎች ያሉ አገልግሎቶች “ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጡ ማድረጋቸውን” በማስረጃነት ይጠቅሳል። በዚህ እርምጃ ምክንያትም ስደተኞቹ ወደተለያዩ አካባቢዎች እንዲበተኑ አድርጓል ሲልም ተጨማሪ ውንጀላ ያቀርባል።

ሽመልባ እና ህጻጽ መጠለያ ጣቢያዎችን ለቅቀው ለወጡ ስደተኞች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠትም አዲስ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በማዘጋጀት ሂደት ላይ መሆኑን ተቋሙ አስታውሷል። ከተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት በመቋቋም ላይ ነው የተባለው ይህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚገኘው በአማራ ክልል፤ ሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ፤ “አለም ዋጭ” ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ ነው። ሆኖም ግን ለጣቢያው ምስረታ ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚጠበቀው ድጋፍ አለመገኘት፤ “ሂደቱ በተጠበቀው ደረጃ እንዳይሳለጥ አድርጎታል” ሲል የዛሬው የተቋሙ መግለጫ አትቷል። 

ይህ ሂደት በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ “ህወሓት ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አዳዲስ ጥቃቶችን መክፈቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል” ብሏል የኤጀንሲው መግለጫ። ጥቃቶቹን ተከትሎም በማይ-ዓይኒ እና አዲ-ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ደህንነታቸው ሊጠበቅ ወደሚችልባቸው አካባቢዎች እንዲዛወሩ እና “አፋጣኝ መፍትሄዎች” እንዲሰጣቸው ጥያቄ ማቅረባቸውንም መግለጫው ይጠቅሳል። 

“ህወሓት ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አዳዲስ ጥቃቶችን መክፈቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል”

– የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ

የስደተኞችን ጥያቄዎች በተመለከተ ከተወካዮቻቸው ጋር ውይይት ማድረጉን የሚጠቅሰው ተቋሙ፤ በዚህም ላይ በመመስረት መንግስት ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ጥረቶች ማድረግ መጀመሩን አብራርቷል። ተቋሙ ከጀመራቸው ጥረቶች መካከል ለስደተኞች “በድጋፍ ላይ የተመሰረተ የከተማ ስደተኝነት እውቅና መስጠት” እና ስደተኞቹን በ“አለም ዋጭ” በሚገኘው አዲሱ መጠለያ ጣቢያ ማስፈር እንደሚገኝበት አመልክቷል። 

የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው የፌደራል መንግስት ተቋም የዛሬውን መግለጫ ያጠቃለለው፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚደርሰውን ስቃይ እና ግድያ በአንድነት እንዲያወግዝ” ጥሪ በማቅረብ ነው። የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በትግራይ ያሉ የኤርትራ ስደተኞችን በሚመለከት፤ ከጥሪው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ያወጣው መግለጫ ግን አንድን ወገን ለይቶ ከማውገዝ ይልቅ በውጊያው የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ ህግን እንዲያከብሩ ጥሪ በማቅረብ ላይ አተኩሯል።

የድርጅቱ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ፊሊፖ ግራንዴ ትላንት ሐምሌ 6፤ 2013 ባወጡት በዚሁ መግለጫ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ “እጀግ በጣም ያሳስበኛል” ብለዋል። በትግራይ ክልል በጥቅምት 2013 ውጊያ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ኤርትራውያን ስደተኞች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታውሰዋል።

ለዚህም በማሳያነት ስደተኞቹ በተፋላሚ ቡድኖች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን፣ መጠለያቸው የነበሩት ሽመልባ እና ህጻጽ ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን እንዲሁም በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ለህይወታቸው በመስጋት እንደገና ወደ ሽሽት መግባታቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህኛው አሊያም ከዚያኛው ወገን ጋር ወግነዋል በሚል በስደተኞች ላይ የበቀል ጥቃቶች፣ ጠለፋዎች፣ እስሮች እና ሁከቶች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ እና በተጨባጭ ማስረጃዎች የተደገፉ ሪፖርቶች እንደደረሷቸውም በትላንቱ መግለጫቸው አንስተዋል። 

የተለያዩ ወገኖች ምሽትን ተገን አድርገው በማይ ዓይኒ እና አዲ ሐሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች በስደተኞች ላይ የሚፈጽሟቸው የጭካኔ ተግባራት በተለይ እንደረበሻቸው የጠቀሱት ፊሊፖ ግራንዴ፤ “በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚፈጸም ሁከት እና ዛቻ ሊቆም ይገባል’’ ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው አሳስበዋል። ስደተኞች ዓለም አቀፍ ጥበቃ የማግኘት መብት ያላቸው እና እገዛ የሚፈልጉ ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል። 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሁሉም ወገኖች ለሰላማዊ ሰዎች የሚደረግ ጥበቃን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ህጋዊ ግዴታቸውን በማክበር ብቻ ሳይወሰኑ፤ “የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር” ስደተኞችን መጠቀሚያ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስቧል። 

ይህንን የኮሚሽኑን መግለጫ በትዊተር ገጻቸው ያጋሩት የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ሁኔታውን “በጣም አሳሳቢ” ሲሉ ገልጸውታል። ተጨማሪ የህይወት መጥፋት እንዳይከሰት “በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሁሉም ወገኖች አፋጣኝ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)