በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ ክልሎች የሚፈጸሙ የዜጎች የመብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ መንግስት አጣርቶ አስቸኳይ እርምጃ በመውሰድ ማስቆም ካልቻለ፤ “ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ቀውሱ ሊከፋ” እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስጠነቀቀ። ኢሰመጉ ማስጠንቀቂያውን የሰጠው በአስቸኳይ መሻሻል ያለባቸው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 15 ባወጣው መግለጫ ነው።
የሰብዓዊ መብት ተሟጓች ድርጅቱ በመግለጫው በአገራዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች እውቅና ያገኙ መብቶች፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ለጥሰት መጋለጣቸውን አስታውቋል። ኢሰመጉ በዚሁ መግለጫው ግድያዎችን ጨምሮ በአራቱ ክልሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን አስመልክቶ የደረሱትን ጥቆማዎች ዘርዝሮ አቅርቧል።
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት፤ ጃርቴ ወረዳ ሰንቦ ጨፌ ቀበሌ እና አሙሩ ወረዳ ጦምቤ ደጋ ቀበሌ “በርካታ ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች” መገደላቸውን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው ጉባኤው በመግለጫው ጠቁሟል። በሰንቦ ጨፌ ቀበሌ ውስጥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካቶች በሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ የተቀሩትም በሻምቡ በኩል አድርገው ወደ ተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ለመሔድ ሲሞክሩ ተከልክለው ችግር ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፤ አሙሩ ወረዳ ጦምቤ ደጋ ቀበሌ ከሐምሌ 1፤ 2013 ጀምሮ በርካታ ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች እየተገደሉ እና እየቆሰሉ መሆኑን የገለጸው ኢሰመጉ፤ በቦታው ያሉ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ “ዛቻ እና ማስፈራሪያ” እንደደረሳቸው አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ነዋሪዎች አካባቢውን ለቅቀው ለመውጣት ሲሞክሩ መንገድ እንደተዘጋባቸውም አትቷል።
በተመሳሳይ ዞን ውስጥ በምትገኘው ጃርቴ ወረዳ፤ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሸኔ ታጣቂዎች “በአካባቢው መኖር አትችሉም፤ ለቅቃችሁ ውጡ” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው የኢሰመጉ መግለጫ አክሏል። በዚህም የተነሳ በወረዳው ከሚገኙ ሀሮሎጎ፣ ጃንጂማረ፣ ሆሮዳዴ፣ አብዲ ዳንዲ እና አሣ ጉዲና ከተባሉ አምስት ቀበሌዎች ነዋሪዎች የእርሻ መሬታቸውን እና ንብረቶቻቸውን ጥለው ስለመውጣታቸው ጥቆማ እንደደረሰው ጉባኤው ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም በወረዳው በሚገኙ ስድስት ቀበሌዎች ያሉ ነዋሪዎች “በእነዚሁ ታጣቂዎች አካባቢውን ለቅቃችሁ ውጡ ተብለው ማዋከብ እና ጫና እየተደረገባቸው ይገኛል” ብሏል።
በኡሙሩ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በሕግ ቁጥጥር ስር የነበሩ ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ ሰዎች ሐምሌ 11፤ 2013 ከግምጃ ቤት መሳሪያ እና ጥይት መዝረፋቸውን በመግለጫው የጠቀሰው ኢሰመጉ፤ እነዚሁ ሰዎች በዕለቱ ከሌሊቱ ስድስት እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ሲተኩሱ ማደራቸውን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው ገልጿል። “በወረዳው ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአማራ ብሔር ተወላጆች ከአካባቢው መውጣት አትችሉም ተብለው በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን አቤቱታ አቅርበዋል” ሲልም የሁኔታውን አሳሳቢነት አስገንዝቧል።
ኢሰመጉ በኦሮሚያ ክልል “በመንግስት የጸጥታ አካላት እንዲሁም ህገ ወጥ ታጣቂዎች ግድያ እና መሰወር እየተፈጸመ መሆኑን” መረጃ እንደደረሰው በመግለጫው አስታውቋል። ለኢሰመጉ ከደረሱ መረጃዎች መካከል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች “በርካታ ሰዎች ‘ሸኔን ተባብራችኋል፤ ልጆቻችሁ ሸኔን ተቀላቅለዋል’ እየተባሉ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለበርካታ ጊዜያት በጠባብ እና በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንደሚታሰሩ እና ለበሽታ እየተዳረጉ መሆኑን” የሚገልጹ ይገኙበታል።
“ከህፃናት ልጆቻቸው ጋር ታስረው ለበሽታ የተዳረጉ እና ሕክምና ለማግኘት የተቸገሩ ሴቶች እንደሚገኙ፤ ከታሰሩበት ቦታ ተወስደው የት እንዳሉ የማይታወቁ ሰዎች” መኖራቸውን የገለጸው ኢሰመጉ፤ በጉቶ ጊዳ ወረዳ የሚገኘው ኡኬ ፖሊስ ጣቢያ እና በዲጋ ወረዳ አርጆ ጉዳቱ ፖሊስ ጣቢያዎች እነዚህ ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው አትቷል።
የኢሰመጉ የዛሬ መግለጫ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በትግራይ ክልል ተከስተዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አካትቷል። በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ወረታ ከተማ ፎገራ ወረዳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሐምሌ 4፤ 2013 በሶስት የትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጸመ የተባለው ግድያ ከጥሰቶቹ ውስጥ አንዱ ነው።
ሶስቱ የትግራይ ተወላጆች የተገደሉት በአካባቢው ሰዎች ተደብድበው መሆኑን የሚጠቁም መረጃ እንደደረሰው የገለጸው ኢሰመጉ፤ ግድያውን በመግለጫው አውግዟል። “በዚህ መንገድ ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ፤ ክቡሩን የሰው ልጅ ሕይወት የመቅጠፍ ተግባራት ሊወገዙ እና ተጣርተው ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” ሲልም ጉባኤው አሳስቧል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተወሰኑ አካባቢዎች “ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ችግር እንዳለ” የጠቀሰው የኢሰመጉ መግለጫ፤ ለዚህም በማሳያነት በቡለን እና ድባጤ ወረዳዎች በሕገ ወጥ ታጣቂዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን አንስቷል። በጥቃቱ ምክንያትም ነዋሪዎች የደህንነት ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ኢሰመጉ ገልጿል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በምትገኘው በቻግኒ ወረዳ፤ የጨረቃ ቀበሌ ዳቲ ዓለም ጸሀይ ጎጥ በተባለ ቦታ፤ ሐምሌ 12፤ 2013 በርካታ ከብቶች በህገ ወጥ ታጣቂዎች መዘረፋቸውንም መግለጫው ጠቅሷል።
በትግራይ ክልል ዕድሜያቸው ለአካለ መጠን ያልደረሰ ታዳጊዎች “የጦር መሳሪያ በመያዝ በግጭት ውስጥ እየተሳተፉ” መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች እንደደረሰውም ኢሰመጉ በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።ድርጊቱ የኢትዮጵያን ህገ-መንግሥት፣ አገሪቱ የፈረመቻቸውን የአፍሪካ ህፃናት መብቶች እና ደህንነት ቻርተር እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መብቶች ቻርተር “ይጥሳል” ብሏል። ይህ ሁኔታም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱን “በእጅጉ እንደሚያሳስበውም” ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)