በጀርመናውያን ባለሃብቶች ሲተዳደሩ የነበሩ አራት ትምህርት ቤቶች ለቱርክ መንግስት ተላልፈው ተሰጡ

በሃሚድ አወል

በአወዛጋቢው የፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ ስር የነበሩ እና በስተኋላ ለጀርመን ባለሃብቶች የተሸጡ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች፤ በቱርክ መንግስት ስር ላለ ተቋም ተላልፈው ተሰጡ። ላለፉት አራት ዓመታት ትምህርት ቤቶቹን ሲያስተዳድር የቆየው የግል ድርጅት ግን ትምህርት ቤቶቹን አላግባብ ተነጥቄያለሁ ብሏል። 

በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ህብረት፣ ሳር ቤት፣ ፈረንሳይ እና ሲ ኤም ሲ አካባቢዎች የሚገኙት አራት ትምህርት ቤቶች መጀመሪያ የተከፈቱት፤ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ባደረጉት ቱርካዊ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ፌቱላህ ጉለን ስም በተመሰረተው “የሂዝመት ንቅናቄ” ነው። በ2008 በቱርክ ከተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጀርባ ፌቱላህ ጉለን ነበሩበት ሲል የወነጀለው የቱርክ መንግስት፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ንቅናቄውን በአሸባሪነት ፈርጇል። 

የቱርክ መንግስት በፍረጃ ብቻ ሳይወሰን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የንቅናቄው አባላትን በእስራት ቀጥቷል። የሀገሪቱ መንግስት ከጉለን እና ደጋፊዎቻቸው ጋር ንኪኪ አላቸው ያላቸውን በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ድርጅቶችን እና ተቋማት ጭምር እንዲዘጉ አድርጓል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በ160 ሀገራት በንቅናቄው የተከፈቱ የትምህርት ተቋማትንም፤ በቱርክ መንግስት ስር ወዳለው “ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን” ለማዛዋወር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ መንግስታዊው የቱርክ የዜና አገልግሎት አናዶሉ ዘገባ ከሆነ፤ የቱርክ መንግስት የማሪፍ ፋውንዴሽንን በ2008 ያቋቋመው፤ “ከፌቱላህ ጉለን አሸባሪ ድርጅት” ጋር ግንኙነት አላቸው የሚላቸውን ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር ነው፡፡ 

የቱርክ መንግስት የማሪፍ ፋውንዴሽንን በ2008 ያቋቋመው፤ “ከፌቱላህ ጉለን አሸባሪ ድርጅት” ጋር ግንኙነት አላቸው የሚላቸውን ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር መሆኑን “አናዶሉ” የዜና አገልግሎት ዘግቦ ነበር

በኢትዮጵያ “ነጃሺ ኢትዮ-ተርኪሽ” በሚል ስያሜ ስር ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ፤ በጉለን ንቅናቄ ስር የነበሩ አምስት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ነበሩ። ከትምህርት ቤቶቹ ውስጥ አምስቱ “ስቲም ኤዱኬሽን” ለተባለ የጀርመን ድርጅት በ2009 ዓ.ም መሸጣቸው ውዝግብ ቀስቅሶ ቆይቷል። የይገባኛል ጥያቄው ፍርድ ቤት ጭምር የደረሰ ነበር።

አምስቱን ትምህርት ቤቶቹን የሸጠው፤ በቱርካውያን ባለሃብቶች የሚተዳዳረው ካይናክ የትምህርት እና ህክምና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፤ “የተከተለው የሽያጭ ሂደት ህጋዊ አይደለም” በሚል ነበር በፍርድ ቤት ክስ የቀረበው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚያሳየው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን የከፈተው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ነው።  

የትምህርት ቤቶቹ የሽያጭ ሂደት “የቱርክ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙት የካይናክ ንብረቶች ተላልፈው እንዲሰጡት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት፤ ንብረቶቹ ወደ ቱርክ መንግስት እንዲተላለፉ ስራ እንዲጀመር መመሪያ ከተሰጠ በኋላ፤ የንብረቱን መወረስ ለማስቀረት በማሰብ በህገ-ወጥ መንገድ [የተከናወነ ነው]” በማለት ዐቃቤ ህግ የጀርመኑ ድርጅት ንብረቶች እንዲታገዱ ጠይቋል።  

የአምስቱን ትምህርት ቤቶች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ንብረቶቹ ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ዐቃቤ ህግ ከዚህ በተጨማሪም፤ በጀርመኑ ድርጅት ስር ያሉ ንብረቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን “ማናቸውንም ህገወጥ ተግባራት ለማስቀረት” በሚል የንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾም ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ይህን ጥያቄ የመረመረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 3፤ 2013 ባዋለው ችሎት፤ የ“ማሪፍ ፋውንዴሽን” ንብረቶቹን ተረክቦ እንዲያስተዳድር ትዕዛዝ ሰጥቷል። የፍርድ ቤቱን ውሳኔን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ወደ ፋውንዴሽኑ መተላለፋቸውን፤ ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው አንድ ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ትምህርት ቤቶቹ ወደ ፋውንዴሽኑ የተላለፉበትን ዝርዝር አካሄድ በተመለከተ አዲስ አበባ ከሚገኘው የማሪፍ ፋውንዴሽን ቢሮ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። የፋውንዴሽኑ የኢትዮጵያ ተወካይ ሌቫን ሳህን “ከፋውንዴሽኑ ዋና ቢሮ በጉዳዩ ላይ እንድናገር አልተፈቀደልኝም” በማለት መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።  

በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢ የሚገኘው ትምህርት ቤት ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ለ“ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን” ተላልፎ ተሰጥቷል

“ኢንተለክቹዋል” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ትምህርት ቤቶች ሲያስተዳድር የቆየው “ስቲም ኤዱኬሽን” የተባለው ድርጅት የአስተዳደር እና የሰው ኃይል ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሃካን አሉስ ግን ትምህርት ቤቶቹን “ከማሪፍ ፋውንዴሽን በመጡ ሰዎች ተቀምተናል” ሲሉ ይወነጅላሉ። በትምህርት ቤቶቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ የቱርክ ሰንደቅ ዓላማ መሰቀሉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት አቅራቢያ እና ሳር ቤት አካባቢ ወዳሉ የትምህርት ቤቱ ሁለት ቅርንጫፎች ዛሬ አርብ ነሐሴ 7፤ 2013 ረፋድ ላይ ያቀናው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢም፤ በትምህርት ቤቶቹ የቱርክ ሰንደቅ ዓላማ መሰቀሉን ተመልክቷል። ትምህርት ቤቶቹም በፌደራል ፖሊስ እየተጠበቁ መሆናቸውን ታዝቧል።

ከአራት አመታት በፊት የተከናወነው የትምህርት ቤቶቹ ሽያጭ “ህጋዊ ነበር” ሲሉ የሚከራከሩት ሃካን አሉስ፤ “የጀርመን ባለሃብቶች በድርጅቶቹ ላይ ፍላጎት በማሳደራቸው ነው የተገዙት” ሲሉ ሂደቱ የ“ንግድ ውሳኔ” ብቻ እንደነበር ያስረዳሉ። እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ በስራ አስኪያጅነት የሚያገለግሉበት ድርጅት፤ በሰበታ አለም ገና ከተማ የሚገኘውን ሌላኛው የትምህርት ቤት ቅርንጫፉን ባለፈው ወር በፍርድ ቤት ትዕዛዝ አጥቷል። ይህንኑ ቅርንጫፍ የ“ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን” ሐምሌ 7፤ 2013 ጀምሮ መረከቡን አስታውቆ ነበር። 

“ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን” በሰበታ አለም ገና ከተማ የሚገኘውን ትምህርት ቤት ባለፈው ሐምሌ ወር መረከቡን አስታውቋል

የማሪፍ ፋውንዴሽን ባለፈው ወር እና በዚህ ሳምንት ከጀርመኑ ድርጅት ከተከረከባቸው አምስት ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ፤ በሐረር ከተማ የሚገኝ በጉለን ንቅናቄ የተከፈተ ትምህርት ቤትንም ከሁለት ዓመት በፊት የመጠቅለል ዕድል አግኝቷል። “ሬይንቦው የበጎ አድራጎት ማህበር” በተባለ ድርጅት ስር ይተዳደር የነበረው ትምህርት ቤት፤ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ የሚያስተምር ነው።   

ከትምህርት ቤቱ በተጨማሪ ግንባታው አልቆ የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት ላይ የነበረ የበጎ አድራጎት ማህበሩ ሆስፒታልም፤ ወደ ማሪፍ ፋውንዴሽኑ መተላለፉን ለፋውንዴሽኑ ቅርበት ያላቸው ግለሰብ አስታውሰዋል። የሐረሩ ትምህርት ቤት “ማሪፍ አለምአቀፍ ትምህርት ቤት” የሚል አዲስ ስያሜን አግኝቶ ስራ ቢጀምርም፤ ሆስፒታሉ ግን እስካሁን ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመረ ግለሰቡ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)