ኦብነግ በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ራሱን አገለለ

በሃሚድ አወል

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በመጪው መስከረም 20 በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ራሱን አገለለ። የተቃዋሚው ፓርቲው በምርጫው ላለመሳተፍ ከውሳኔ ላይ የደረሰው፤ የኦብነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ላለፉት አምስት ቀናት በጅግጅጋ ከተማ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ነው። 

የኦብነግ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ አብዱላሂ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ከምርጫ ራሱን እንዲያገልል ምክንያት የሆነው ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ያቀረበው ቅሬታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል በአግባብ ባለመመለሱ ነው። በሶማሌ ክልል ሰኔ 14 ሊካሄድ ለነበረው ምርጫ በተደረገው የመራጮች ምዝገባ የተስተዋሉ ችግሮች እና የምርጫ አስፈጻሚዎች ገለልተኝነት፤ በኦብነግ በኩል ቅሬታ የቀረበባቸው ጉዳዮች ነበሩ። 

የመራጮች ምዝገባው “ብዙ ችግሮች ነበሩበት” የሚሉት አቶ አህመድ፤ በሂደቱ ከታዩ የአሰራር ግድፈቶች መካከል ጉልህ የሚሉትን በማሳያነት ጠቅሰዋል። “የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በግለሰብ ደረጃ እስከ 300 የምርጫ ካርዶችን ወስደዋል” የሚል ክስ የሚያቀርቡት እኚሁ የኦብነግ አመራር፤ ፓርቲያቸው እኒህን መሰል ችግሮች ከማስረጃ ጋር በማያያዝ ለምርጫ ቦርድ ማስገባቱን አስታውሰዋል። 

ኦብነግን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ለምርጫ የሚወዳደሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች የተቀበለው ምርጫ ቦርድ፤ በክልሉ ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ “ጉልህ የሆነ የአሰራር እና የህግ ጥሰቶች ግድፈት ተስተውሎባቸዋል” በተባሉ ሰባት የምርጫ ክልሎች ላይ ሲደረግ የቆየው የመራጮች ምዝገባ በሚያዝያ ወር 2013 በጊዜያዊነት እንዲቋረጥ አድርጎ ነበር። ቦርዱ በግንቦት አጋማሽ ባወጣው መግለጫ፤ በመጀመሪያ ከተገለጹት ሰባት የምርጫ ክልሎች በተጨማሪ አራት የምርጫ ክልሎችን በማከል በአጠቃላይ በ11 የምርጫ ክልሎች ምርመራ እንዲከናወን መወሰኑን አስታውቋል።

የምርጫ ቦርድ አጣሪ ቡድን ከላከባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ፤ ጅጅጋ 1 እና ጅጅጋ 2 በተባሉት ለፓርላማ መቀመጫ ውድድር በሚደረግባቸው የምርጫ ክልሎች፤ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ እንዲደገም ባለፈው ነሐሴ ወር ወስኗል። ቦርዱ የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ለሆኑት የቀብሪደሃር ከተማ እና የቀብሪደሃር ወረዳም ተመሳሳይ ውሳኔ አስተላልፏል። 

በዋርዴር፣ ፊቅ፣ ገላዴን እና ጎዴ ከተማ ምርጫ ክልሎች ባሉ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች፤ የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ከውሳኔ ላይ መደረሱን በቦርዱ የነሐሴ ወር ውሳኔ ተገልጿል። ከዚህ በጨማሪም፤ በጸጥታ እና ሌሎች ምክንያቶች የመራጮች ምዝገባ አልተከናወነባቸውም በተባሉት የመኢሶ እና አፍደም የምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እንዲደረግ ቦርዱ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። 

ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ባስተላለፈባቸው የሶማሌ ክልል የምርጫ ክልሎች ከነሐሴ 26 እስከ መስከረም 2 የመራጮች ምዝገባ ሲያከናወን ቆይቷል። የቦርዱ ድጋሚ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ግን በተቃዋሚው ፓርቲ ኦብነግ በኩል ተቀባይነት አላገኝም። የኦብነግ የአዲስ አበባ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፤ ፓርቲያቸው ቅሬታ በቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ ተደረገው የመራጮች ምዝገባ “ገለልተኛ በሆኑ በአዲስ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሙሉ በሙሉ መደገም ነበረበት” የሚል አቋም እንዳለው ያስረዳሉ።

የሶማሌ ክልል በተወካዮች ምክር ቤት ላሉት 23 መቀመጫዎች ኦብነግ ሙሉ ለሙሉ ዕጩዎችን አቅርቦ ነበር። ፓርቲው የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 273  መቀመጫዎች በ217ቱ እንደሚወዳደር አስታውቆ የነበረ ቢሆንም ዛሬ አርብ መስከረም 7 ባስተላለፈው ውሳኔ ከምርጫው ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።   

ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ከቀረው የክልሉ ምርጫ ያለመሳተፍ ውሳኔውን በማሳወቅ ኦብነግ ብቸኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አይደለም። በሶማሌ ክልል የሚንቀሳቀሰው የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲም (ነእፓ) መስከረም 20 በክልሉ ከሚካሄደው ምርጫ ራሱን ማግለሉን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል።  

ነእፓ በምርጫው ላለመሳተፍ ገፊ የሆነው ምክንያት፤ ምርጫ ቦርድ በክልሉ ከነበረው የመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሆነ የፓርቲው የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑር ወለላ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፓርቲያቸው በዕጩዎች እና በመራጮች ምዝገባ ወቅት በክልሉ ተስተውለዋል ያላቸውን የአሰራር ግድፈቶች ለምርጫ ቦርድ ቢያስገባም አጥጋቢ ምላሽ አለማግኘቱንም ገልጸዋል።

ነእፓ ጷጉሜ 3፤ 2013 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤም ይህንኑ አስተጋብቷል። የምርጫ ቦርድ ውሳኔ “የፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ያነሷቸውን ችግሮች ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው” ሲል ፓርቲው በደብዳቤው ተችቷል። “ውሳኔው የሶማሌ ህዝብ ለዘመናት ሲናፍቀው የነበረውን መሪዎቹን በነጻነት መምረጥ ህልም እውን ለማድረግ የነበረውን ተስፋ የሚያጨለም ነው” ሲል ነእፓ በደብዳቤው ወቅሷል። 

የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ በሶማሌ ክልል 165 ዕጩዎችን ለውድድር አቅርቦ ነበር። ከዕጩዎቹ ውስጥ አስራ ስድስቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የቀረቡ ሲሆኑ፤ 149ኙ ደግሞ ለክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚወዳደሩ ነበሩ። 

ኦብነግ እና ነእፓ ከምርጫ ራሳቸውን ለማግለል ምክንያቶች ናቸው ሲሉ የጠቀሷቸውን ችግሮች በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ቦርዱ ሶማሌ ክልልን ጨምሮ በመስከረም 20 ምርጫ በሚደረግባቸው ቦታዎች ስላለው አጠቃላይ ሂደት በመጪው ሰኞ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)