አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፤ ከደቡብ ክልል ስልጣን ተረከበ

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል እና አዲስ በተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መካከል ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 24፤ 2014 የስልጣን ርክክብ ተካሄደ። የስልጣን ርክክቡን ያካሄዱት፤ የደቡብ ክልል ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ እና አዲሱን ክልል የመሰረቱት የአምስት ዞኖች እና የአንድ ልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች ናቸው።  

አዲሱን ክልል የመሰረቱት በደቡብ ክልል የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። ከዛሬው የስልጣን ርክክብ ስነ ስርዓት በኋላ ስድስቱን አፈ ጉባኤዎች በመወከል ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት የምዕራብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ቢልልኝ ወልደሰንበት ናቸው። 

የደቡብ ክልል ምክር ቤት በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባው፤ በደቡብ ክልል እና አዲስ በተቋቋመው ክልል መካከል የሚኖረውን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን የቀረበ ውሳኔ ሃሳብን በሙሉ ድምጽ አድድቋል። አራት ክፍሎች እና 17 አንቀጾች ያሉት የውሳኔ ሃሳቡ ከዘረዘራቸው ጉዳዮች መካከል በነባሩ እና በአዲሱ ክልል መካከል ያለውን የሽግግር ጊዜ እና የስልጣን ርክክብ ይገኝበታል። 

የውሳኔ ሃሳቡ ከዚህ በተጨማሪም የሃብት እና የዕዳ ክፍፍል እንዲሁም የሰው ሃይል ድልድልና ስምሪት ምን እንደሚመስሉ በዝርዝር የተቀመጠበት ነው። በጉባኤው ላይ  የሃብትና ዕዳ ክፍፍል እንዲሁም በ2014 በስራ ላይ ያሉ  ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ዕጣ ፈንታን የተመለከቱ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት ተነስተው ነበር። ለእዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎች የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)