የስድስተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመክፈቻ ስብሰባቸውን ባለፈው መስከረም ወር ካከናወኑ ወዲህ፤ እስከ ትላንት ድረስ መደበኛ ስብሰባ ያካሄዱት ለሁለት ጊዜያት ብቻ ነው። ምክር ቤቱ በትላንትናው ዕለት ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ አባላቱን ሲጠራ፤ የተደራረቡ ስራዎችን ለማቃለል ያሰበ ይመስል ስድስት አጀንዳዎችን ይዞ ነበር።
ከስድስቱ አጀንዳዎች ሶስቱ፤ ለምክር ቤቱ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ ውይይት እንዲካሄድባቸው የታሰቡ ነበሩ። ከእነዚህ ረቂቅ አዋጆች መካከል የፓርላማ አባላቱ ሰፊ ጊዜ ወስደው የተወያዩት አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው። በአነጋጋሪው አዋጅ ላይ አራት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል።
ለተወካዮች ምክር ቤት ከመቅረቡ በፊት ከአንድም ሁለት ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎበታል የተባለው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ሰባት መሠረታዊ አላማዎች እንዳሉት ተገልጿል። ከኮሚሽኑ ዓላማዎች መካከል በአዋጅ ረቂቁ ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው፤ “በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በመለየት እና ውይይቶቹ የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ-ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግባቸው ማመቻቸት” የሚለው ነው።
የምክክሮቹን “አካታችነት” እንዲሁም “ብቃት ባለው እና ገለልተኛ በሆነ አካል የሚመሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት” ረቂቁ ሲጸድቅ በሚቋቋመው ኮሚሽን ትከሻ ላይ የወደቀ ኃላፊነት ሆኗል። ኮሚሽኑ “መተማመን የሰፈነበት እና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር በሚያስችል አግባብ ውይይቶቹ እንዲካሄዱ ሥርዓት መዘርጋት” እንደሚኖርበትም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።
በዚህ መልክ ከሚካሄዱ ምክክሮች “የሚገኙ የመፍትሔ ምክረ-ሃሳቦች ሥራ ላይ እንዲውሉ ድጋፍ በማድረግ መተማመን የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲገነባ” ማስቻል ሌላው የኮሚሽኑ መሠረታዊ ዓላማ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን አወቃቀር ምን ይመስላል?
“ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ” ይሆናል የተባለው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሚሆን ተቋም ነው። ኮሚሽኑ ከመንግሥት በሚመደብለት በጀት የሚተዳደር ሲሆን ከሌሎች ሕጋዊ ምንጮች [ድጋፍ] ማግኘት እንደሚችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የአዋጅ ረቂቅ ያሳያል።
ኮሚሽኑ ሲቋቋም ምክር ቤት፣ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነር፣ ጽህፈት ቤት እንዲሁም አስፈላጊ ኮሚቴዎች እና ሠራተኞች እንደሚኖሩት በአዋጅ ረቂቁ ተዘረዝሯል። “ጠንካራ ቅቡልነት ያለው አገረ መንግስት ለመገንባት ጽኑ መሰረት እንዲጥል” የሚጠበቅበት ይህ ተቋም፤ 11 ኮሚሽነሮች ይኖሩታል።
የኮሚሽኑ ምክር ቤት አስራ አንዱን ኮሚሽነሮች የሚያቅፍ ሲሆን “ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር በመፈተሽ መወሰንን የመሳሰሉ ከፍ ያሉ ኃላፊነቶች የተጣሉበት ነው። ይኸን ምክር ቤት ዋና ኮሚሽነሩ የመምራት ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ኮሚሽነር እና ሌሎች ኮሚሽነሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ይጸድቃል። ኮሚሽነሮቹ የሚመረጡት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከሕዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበራት ጥቆማ ከሚቀበላቸው ዕጩዎች መካከል እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ተገልጿል።
ከእነዚህ ዕጩዎች መካከል አስራ አራቱ ተመርጠው ለህዝብ ይፋ ከተደረጉ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርቧቸውን ዕጩዎች ከመወሰናቸው በፊት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ምክክር ማድረግ እንደሚኖርባቸው በአዋጅ ረቂቁ ተመልክቷል። በምክክሩ የሚሳተፉት ከፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ከሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሚወከሉ ግለሰቦች እና አመራሮች እንደሆኑም ተብራርቷል።
የአዋጅ ረቂቁ ኮሚሽነሮች የሚመረጡባቸውን ዘጠኝ መሥፈርቶች በዝርዝር አቅርቧል። ከመሥፈርቶቹ መካከል በቀዳሚነት የተቀመጠው፤ ኮሚሽነር ሆኖ የሚሾም ግለሰብ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ነው። ኮሚሽነሮቹ “የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል” ሊሆኑ እንደማይገባ በረቂቅ አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌ ተካትቷል።
“ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ የተለያዩ ብሔሮችን፣ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን በእኩል ዓይን” መመልከት ሌላው በኮሚሽነርነት ለመመረጥ የሚያበቃ መሥፈርት ነው። ለቦታው የሚታጭ ሰው “ለአገራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል” መሆን እንደሚገባውም በመሥፈርትነት ተጠቅሷል።
እነዚህን መሥፈርቶች አሟልተው የሚሾሙ ኮሚሽነሮች በተቋሙ በሚያገለግሉበት ወቅት ያለ መከሰስ መብት ይኖራቸዋል። የጥቅም ግጭትን ማስወገድ እና በሥራ የሚያገኙትን ምሥጢር መጠበቅን ጨምሮ ስድስት ግዴታዎች እንዳሉባቸው በአዋጅ ረቂቁ ሰፍሯል። ኮሚሽነሮች ግልጽ በሆነ የብቃት ማነስ እንዲሁም ከባድ የሥነ ምግባር ጉድለትን በመሳሰሉ ምክንያቶች ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደሚችሉም ተገልጿል።
ኮሚሽነሮች ከኃላፊነታቸው የሚነሱት “ማስረጃ ባለው ወገን ጠያቂነት”፤ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአንድ ሶስተኛው አነሳሽነት አሊያም በተቋሙ ከሶስት ያላነሱ ኮሚሽነሮች ጥያቄ መሠረት እንደሚሆን በአዋጅ ረቂቁ ተቀምጧል። የመጨረሻው ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚተላለፍ ነው።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ኮሚሽነሮች ከተሾሙለት ጀምሮ የሚቆጠር የሶስት ዓመታት የሥራ ዘመን ይኖረዋል ተብሏል። ይህ የሥራ ዘመን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊራዘም የሚችልበት ዕድል እንዳለም በአዋጅ ረቂቁ ተመላክቷል። ኮሚሽኑ ሥራ ሲጀምር ምክክሮችን የሚያመቻቹ፣ የሚያስፈጽሙ ጥናቶች የሚያከናውኑ፣ ምክረ-ሐሳቦችን የሚያመነጩ ኮሚቴዎች እና የባለሙያዎች ቡድን እንደሚያቋቁም ይጠበቃል።
የትኞቹ ጉዳዮች ለአገራዊ ምክክር ይቀርባሉ?
በአዋጅ ረቂቁ ላይ ከዚህ ቀደም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተደርገው ነበር በተባሉ ውይይቶች ላይ፤ በተደጋጋሚ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ “ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው?” የሚል እንደነበር ለፓርላማ አባላት በተሰራጨ ማብራሪያ ላይ ተጠቅሷል። በማብራሪያው መሠረት ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ሥራ ሲጀምር “ጠቃሚ እና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ጉዳዮች ሁሉ” ለምክክር አይቀርቡም።
“ሃገራዊ ፋይዳ ያላቸው እጅግ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ያሉ” መሆኑን ያነሳው ማብራሪያው፤ “እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች አሳታፊ በሆነ የምክክር ሂደት ለመዳሰስ ቢሞከር መቋጫና ብዙም ፍሬ የሌለው እና እጅግ እጅግ የተንዛዛ ሂደት ውስጥ የመግባት አደጋ” እንዳለው ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሚደረግ አገራዊ ምክክር “የአገረ መንግሥቱን ህልውና እና ቅቡልና ለማጠናከር ወሳኝ ሚና ያላቸው አንኳር ጉዳዮች” ላይ ማተኮር እንዳለበት አትቷል።
በዚሁ ማብራሪያ ላይ በአዋጁ ዝርዝር የምክክር አጀንዳዎችን መደንገግ ያልተፈለገበት ምክንያትም ተብራርቷል። “ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው ኮሚሽነሮች የህዝብን ፍላጎት፣ የሃገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ እና ታሪክ ከግምት ውስጥ በማስገባት አገባብነት ያላቸውን ሳይንሳዊ መንገዶች በመጠቀም ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን እና እጅግ መሰረታዊ ከመሆናቸው የተነሳ ሀገራዊ መግባባት ሊኖርባቸው የሚገቡ ጭብጦችን በተሻለ ሁኔታ ሊለዩ ይችላሉ” የሚለው ማብራሪያው፤ በዚህም የተነሳ የምክክር አጀንዳዎቹን የመወሰኑ ጉዳይ ለኮሚሽኑ መተውን ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ሥራዎች “የጋራ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ያተኮረ በመሆኑ” ምክክር የሚለው ቃል ተመራጭ እንደሆነ ተገልጿል። የኢትዮጵያን “ልሂቃን እና አብዛኛውን ማህበረሰብ ባካተተ መንገድ የጋራ መፍትሔ የሚፈለግበት” ነው በተባለው አገራዊ ምክክር፤ በውስጡ “ውይይት እና ድርድርን ያካተተ አውድ ሊኖረው” እንደሚችልም በማብራሪያው ተነስቷል።
በሂደቱ መጨረሻ ግልጽ እና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ ሐሳቦች ይጠበቃሉ። እነዚህ ምክረ ሐሳቦች “በሚደረገው አገራዊ ውይይት እና ምክክር ሒደት የመነጩ፣ የአብዛኛው ዜጋ ድጋፍ ያላቸው እና አገራዊ አውዱን ከግምት ውስጥ ያስገቡ” መሆን እንዳለባቸው በማብራሪያው ሰፍሯል።
በአገራዊ ምክክሩ ላይ እነማን ተሳታፊዎች ይሆናሉ?
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በይፋ ከተቋቋመ በኋላ በሚያካሄዳቸው ምክክሮች የሚሳተፉ አካላት ጉዳይ፤ ትላንት ሐሙስ ታህሳስ 7፤ 2014 በነበረው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አነጋግሯል። አቶ ባያብል ሙላቴ የተባሉ የፓርላማ አባል ኮሚሽኑ ሲቋቋም የሚያካሄዳቸው አገራዊ ምክክሮች “ሁሉን አካታች ነው” መባሉ ማብራሪያ እንደሚያሻው አንስተዋል። “ሁሉን አካታች የሚለው ቃል ህዝቡን ግራ ያጋባል” ያሉት የገዢው ፓርቲ አባል፤ ይህ አባባል ግልጽ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ላለፈው አንድ አመት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውጊያ የገጠመው እና በምክር ቤቱ “ሽብርተኛ” ተብሎ የተፈረጀው ህወሓት፤ በአገራዊው ምክክር የሚኖረው ተሳትፎ ሌላው ያነጋገረ ጉዳይ ነው። የብልጽግና ፓርቲን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት የቀደሞው የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሐመድ “ህወሓት እና ኢትዮጵያ የማይታረቁ ቅራኔዎች አሏቸው” ብለዋል። አቶ ሰይድ “ህወሓት ኮሚሽኑ በሚያዘጋጃቸው ምክክሮች ላይ ሊሳተፍ አይገባም” የሚል አቋማቸውን በስብሰባው አንጸባርቀዋል።
በትላንትናው ዕለት ለፓርላማው የቀረበ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከተቋሙ ምስረታ በኋላ በሚደረጉ አገራዊ ምክክሮች የሚሳተፉ ወገኖችን ማንነት አያብራራም። አዋጁን የሚያብራራው ሰነድ ግን የምክክሩ ተሳታፊዎች በአዋጁ ያልተገለጹበትን ምክንያት ለማስረዳት ሞክሯል።
“የምክክር ሂደቱን ተሳታፊዎች በተመለከተ፣ በየትኛው ደረጃ፣ በምን አይነት አካሄድ እና መስፈርት ተሳታፊዎች እንደሚመለመሉ የአሰራር ስርዓቱ በአዋጅ በዝርዝር ከሚቀመጥ ይልቅ ለኮሚሽኑ ቢተው የተሻለ ነው የሚል አቋም ተወስዷል። ገለልተኛ እና ብቁ የሆኑ ኮሚሽነሮች ይህን አሰራር ቢዘረጉ እና ዝርዝር ጉዳዮችን በመመሪያ ቢወስኑ ይበልጥ ውጤታማ የሆነ ስራ ለመስራት ይችላሉ ተብሎ ታምኗል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ አትቷል።
በፓርላማ አባላት ጥያቄዎች የተነሱበት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ የአዋጅ ረቂቅ፤ የምክር ቤቱ የፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲመለከተው በትላንቱ ስብሰባ ተመርቶለታል። በአምስት ክፍሎች እና በሰላሳ አንቀጾች የተደራጀው የአዋጅ ረቂቁ፤ የኮሚሽኑ ዓላማ፣ አደረጃጀት ተግባር እና ኃላፊነቶች በዝርዝር የቀረቡበት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]