ኢዜማ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጥቆማ መቀበያ ጊዜ እንዲራዘመ ጠየቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የጥቆማ መቀበያ ጊዜ እንዲራዘም ለተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አቀረበ። ኢዜማ ጥያቄውን ያቀረበው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 3፤ 2014 በጻፈው ደብዳቤ ነው።   

ፓርቲው ከሶስት ቀናት በኋላ አርብ ጥር 6 የሚጠናቀቀው የጥቆማ ጊዜ እንዲራዘም የጠየቀው በአራት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው ምክንያት ከማህበረሰቡ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። 

ማህበረሰቡ “በሌሎች በርካታ አጀንዳዎች” ተጠምዶ ከርሟል ያለው ኢዜማ ማህበረሰቡ ጦርነቱ ካሳደረበት ስነ ልቦናዊ ጫናም አለመላቀቁን በደብዳቤው አስፍሯል። በዚህም ምክንያት “በሀገራዊ ምክክሩ አጠቃላይ ፋይዳና ሂደቱ ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ ማስጨበጥ” ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ፓርቲው ጠቁሟል።

የመገናኛ ብዙሃን ሚና ሁለተኛው ኢዜማ በምክንያት የጠቀሰው ጉዳይ ነው። ኢዜማ የብዙኃን መገናኛዎች በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የህዝብን ተሳትፎ ከማንቃት አንጻር “ተገቢውን ሚና እየተጫወቱ አይደለም” ብሏል። ተጠሪነታቸው ለተወካዮች ምክር ቤት የሆኑ መገናኛ ብዙሃን፤ ዜጎች የኮሚሽነሮችን ጥቆማ ይሰጡ ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንዲሰሩ እንዲሁም በምክከሩ ሂደት ላይ ትኩረት እንዲሰጡ ፓርቲው ጠይቋል።

ሶስተኛው ምክንያት ከኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የጥቆማ  ሂደት ጋር የተያያዘ ነው። ኢዜማ በደብዳቤው “ውስብስብነት የሚታይበት” ያለው የኮሚሽነሮች የጥቆማ ሂደት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ እንዲደረግ ጠይቋል።

ለጥቆማ መቀበያ የተሰጠው ጊዜ በቂ አለመሆኑ ኢዜማ በመጨረሻ የጠቀሰው ምክንያት ነው። ኢዜማ ከፖለቲካው ገለልተኛ የሆኑ እና ብቃት ያላቸውን ዜጎችን ለመምረጥ የተሰጠው ጊዜ በቂ አለመሆኑን በደብዳቤው ገልጿል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው የኮሚሽነሮች ጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ የእጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ለአስር ቀናት እንደሚቀበል ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት ሰኞ ታህሳስ 25፤ 2014 ነበር። ኮሚቴው ማስታወቂያው ባስነገረ በማግስቱ የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ መቀበል ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የኮሚሽሮችን ጥቆማ እንደሚቀበል ይደነግጋል። ኢዜማ በደብዳቤው “የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ከወዲሁ የሚያመላክት” ሲል የገለጸውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በጥንቃቄ መምራት አለበት” ሲል አሳስቧል።

ኢዜማ በዚሁ ደብዳቤው የኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የጸደቀበት ሂደትንም ተችቷል። በአዋጁ ረቂቅ ላይ ማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት “በበቂ ሁኔታ ተደጋጋሚ ውይይቶች ሳያደርጉ በፍጥነት” ጸድቋል ሲል ፓርቲው ቅሬታውን አቅርቧል። ፓርቲው የአዋጁ “በፍጥነት” መጽደቅ በቀጣይ የምክክሩን “ፍትሃዊነት ጥያቄ ውስጥ እንዳያስገባው” ሲል ስጋቱን ገልጿል።

የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ከሁለት ሳምንት በፊት በጸደቀበት የተወካዮች ምክር ቤት ስብስባም ከፓርላማ አባላት ተመሳሳይ አስተያየት ተደምጦ ነበር። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ “አዋጁን ለማጽደቅ እየተሄደበት ያለው የችኮላ ስሜት ጥርጣሬ ይፈጥራል” ብለው ነበር። የተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ “ምክክር ማካሄድም ሆነ፤ የምክክር ኮሚሽን የማቋቋሙ ስራ ዘግይቷል” ማለታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)