የሰላም ጥረቶች እና ውጥኖችን የመደገፍ ዓላማ ያለው ሀገር አቀፍ ቡድን ተቋቋመ

በተስፋለም ወልደየስ 

በኢትዮጵያ የተጀመሩ የሰላም ውጥኖች ከግብ እንዲደርሱ የመደገፍ ዓላማ ያለው ሀገር አቀፍ የሰላም ቡድን ተቋቋመ። ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አባ ገዳዎች እና የሰላም እናቶችን ያካተተው የሰላም ቡድን፤ በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትን የማነጋገር ዕቅድ አለው ተብሏል። 

ሀገር አቀፍ የሰላም ቡድን መቋቋሙ ይፋ የተደረገው ዛሬ ቅዳሜ ጥር 7፤ 2014 በአዲስ አበባው ራማዳ ሆቴል በተካሄደ የማህበረሰብ የምክክር መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ ላይ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 69 የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የሰላም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። 

የመድረኩ ተሳታፊዎች በውይይቱ ማጠናቀቂያ ላይ ባወጡት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ፤ ለመንግስት፣ በቅርቡ ከእስር ለተፈቱ ፖለቲከኞች እና ለሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የሰላም ጥሪዎች አስተላልፈዋል። መንግስት በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን መፍታቱን ያደነቁት ተወያዮቹ፤ በተመሳሳይ መልኩ “በእስር ላይ ያሉ ተጨማሪ ፖለቲከኞችን እንዲፈታ እና የተጀመረውን የምክክር ሂደት እንዲያቀላጥፍ” ጥሪ አቅርበዋል።  

እነዚህ እስረኞች እንዲለቀቁ “የተጀመረው የሰላም መንገድ እውን እንዲሆን”፤ በቅርቡ ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞች ጥረት እንዲያደርጉ የማህበረሰብ የምክክር መድረክ ተሳታፊዎቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ፖለቲከኞቹ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክርም ሆነ ለሌሎች የሰላም ውጥኖች መሳካት “ጉልህ አስተዋጽኦ” እንዲያደርጉ የጠየቁት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ ኢትዮጵያ “ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንድትሸጋገር” ከመንግስት ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ለመተባበር ዝግጁ እንዲሆኑም አሳስበዋል።

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ያነሱት ሌላው ጉዳይ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው። የውይይቱ ተሳታፊዎች ጦርነት በተካሄደባቸው ክልሎች በደረሰው ሞት፣ ውድመት እና መፈናቀል የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን የገለጹ ሲሆን፤ ሁሉም አካላት በጦርነት የተጎዱ ክልሎችን መልሶ ለመገንባት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ በትብብር እንዲሰሩም ጥሪ አድርገዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በዛሬው መግለጫቸው “ታጥቀው በጫካ ያሉ” ላሏቸው ሁሉም ወገኖችም መልዕክት አስተላልፈዋል። የሀገር ሽማግሌዎቹ “ታጥቀው በጫካ ያሉ ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላማዊ መድረክ ተመልሰው ግጭቶችን በምክክር እንዲፈቱ” ጥሪ አድርገዋል። መንግስትም በበኩሉ ይህንን ጥሪ ተቀብሎ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል።

እነዚህ የሰላም ጥሪዎች እና ውጥኖች ተግባራዊ ለማድረግም የመድረኩ ተሳታፊዎች “ሀገር አቀፍ የሰላም ቡድን” ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል። የሰላም ቡድኑ በእስር ላይ ያሉ ሌሎች ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ለማበረታት፤ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር የመነጋገር እቅድ እንዳለው በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።  

በተመሳሳይ ሁኔታም ከእስር የተፈቱ እና የሚፈቱ ፖለቲከኞች እንዲሁም ከሌሎች የባለ ድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በ“ኢትዮጵያ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን” ጥረት እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)