በትላንትናው ዕለት ከተሾሙት አምባሳደሮች የተወሰኑት፤ ተቀማጭነታቸው በሀገር ውስጥ እንደሚሆን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

በሃሚድ አወል

በፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በትላንትናው ዕለት ከተሾሙ 27 አምባሳደሮች ውስጥ የተወሰኑት ወደ ተሾሙበት ሀገር ሳይሄዱ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ አምባሳደሮች (non-resident ambassadors) እንደሚሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ፤ ሹመቱ “ዲፕሎማሲያዊ ሙያን መሰረት ያደረገ ነው” ብለዋል። 

ቃል አቃባዩ ዛሬ ሐሙስ ጥር 19 በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫቸው፤ የአምባሳደሮች ሹመት የተከናወነው “በጥናት” መሆኑን ተናግረዋል። ሹመቱ ሶስት አሰራሮችን የተከተለ መሆኑን ለጋዜጠኞች የተናገሩት ዲና፤ ከእነዚህ መካከል አንደኛው አምባሳደሮች ወደ ተወከሉበት ሀገር ሳይሄዱ ነዋሪነታቸው በሀገራቸው ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። 

“Non-resident አምባሳደር የሚባል አለ። እዚሁ ነው የሚኖሩት፤ እዚያ ሀገር አይኖሩም። የተወከሉበት ሀገር አስፈላጊ ሲሆን እየተመላለሱ የሚሰሩ non – resident ambassadors የሚባሉ እዚህ ውስጥ አሉ ማለት ነው”  ሲሉ ከትላንቱ ተሿሚዎች ውስጥ የተወሰኑት ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ እንደሚሆን ጠቁመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት ሰኔ በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር ካሏት ኤምባሲዎች ውስጥ ቢያንስ ሰላሳ ያህሉን እንደምትዘጋ ገልጸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባቀረቡት ማብራሪያ፤ ተቀማጭነታቸው በሀገራቸው የሆኑ አምባሳደሮችን የመጠቀም አሰራርን መከተል የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለመቆጠብ እንደሚያስችል ተናግረዋል። 

በዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ወደ ተወከሉበት ሀገር የማይሄዱ አምባሳደሮች ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ጥያቄ ቢነሳም፤ ዲና ሙፍቲ ጥያቄውን ምላሽ ሳይሰጡ አልፈውታል። አምባሳደሮቹ የተሾሙባቸው ሀገራት ዝርዝርን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተጨማሪ ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ፤ “ገና እየተሰራ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

በሳምንታዊው መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደሮችን ለመሾም የተከተለው ሌላኛው አሰራር፤ “በአነስተኛ የሰው ኃይል የሚሰሩ ኤምባሲዎች እንዲኖሩ ማድረግ” የሚለው መሆኑ ተገልጿል። “ስራ እና ሰራተኛን ማመጣጠን” የሚለው በሚኒስቴሩ ተግባራዊ የተደረገው ሶስተኛው አሰራር መሆኑንም ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

ሹመቱ “ዲፕሎማሲያዊ ሙያን መሰረት ያደረገ ነው” ያሉት ቃል አቃባዩ፤ ለዚህም ከተሿሚዎቹ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያገለገሉ መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል። ዲና ይህን ቢሉም በትላንቱ ሹመት “ከሌላም ሙያ የመጡ ሰዎች” መካተታቸውን አልሸሸጉም።

ትላንት ረቡዕ ጥር 18፤ 2014 ሹመታቸው ይፋ ከተደረጉ አምባሳደሮች መካከል ሁለት ከፍተኛ የጦር አመራሮች እና በአባይ ግድብ ድርድር ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የቀድሞ ሚኒስትር መካተታቸው አነጋግሯል። የባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንት፤ ጄነራል ባጫ ደበሌ እና ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም ናቸው።

ሁለቱ አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅራቢነት በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ከሶስት ሳምንት በፊት ነበር። ጄነራል ባጫ ከመከላከያ ሰራዊት የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪነታቸው ተነስተው በአምባሳደርነት የተሾሙ ሲሆን፤ ጄነራል ሀሰንም ከሁለት ወራት በፊት በአስተባባሪነት ከተሾሙበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረሃይል መሪነት በተመሳሳይ መልኩ የሚለቅቁ ይሆናል። 

ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ፤ ይመሩት ከነበረው የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተነስተው በሚኒስትር ማዕረግ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪና አማካሪ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ስለሺ በቀለም የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች ዕጣ ገጥሟቸዋል። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በአዲስ አበባ ከተማ ለፓርላማ አባልነት ተወዳድረው የተመረጡት ዶ/ር ስለሺ፤ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት 16 ግለሰቦች አንዱ ሆነዋል። 

የአምባሳደሮችም ሹመት “የተለመደ” እንደሆነ ያስረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቃባይ፤ ሆኖም የትላንትናው ሹመት የሚለይበት ሁለት ምክንያቶች እንዳሉት አስረድተዋል። ሹመቱ “ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ ክብርን በተሻለ ሁኔታ ማስጠበቅን ዓላማ ያደርጋል” ያሉት ዲና መፍቲ፤ “የለውጡን መንፈስ፤ በተለይ [ላለፉት] ሶስት ዓመት የተያዘውን የሪፎርሙን መንፈስ መሰረት” ማድረጉም ሌላው የተለየ የሚያደርገው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል። “አንዱ ዓላማ፤ በዲፕሎማሲ መስክ የለውጡን ግብ ለማሳካት የሚያስችለንን አቅጣጫ ለመከተል ነው” ብለዋል ዲና ሙፍቲ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)