በሃሚድ አወል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ከአራት ወራት በፊት የቢሮ ኃላፊ ሹመት የሰጣቸውን ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ከስልጣን አነሳ። ባለፈው ጥቅምት ወር የተሰጣቸውን ሹመት የተነጠቁት፤ የቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) ሁለት ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።
የክልሉ መንግስት ለአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች አዳዲስ ኃላፊዎችን በመደበበት ወቅት፤ የቤህነን ሊቀመንበር አቶ አብዱልሰላም ሸንግልን የክልሉን ገጠር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ ሾሟቸው ነበር። የተቃዋሚ ፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ እስማኤል ደግሞ፤ በክልሉ ትምህርት ቢሮ የምክትል ኃላፊነት ቦታ አግኝተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ትላንት አርብ የካቲት 4፤ 2014 ይፋ ባደረገው “የአመራር ምደባ ማስተካከያ” ግን በሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የኃላፊነት ቦታ ላይ ሌሎች ግለሰቦች ተሹመውባቸዋል። የክልሉ መንግስት ለተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ የሰጠውን ሹመት ያነሳው፤ ተሿሚዎቹ “ወደ ስራ ባለመግባታቸው” መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

“እነዚህ ሰዎች ከአራት ወር በፊት የመደብናቸው ናቸው። እስካሁን አንድም ቀን ቢሮ ገብተው አያውቁም። ተቋማቱ ከአራት ወር በላይ ባለቤት አልባ ሆነው እየተበደሉ ስለሆነ፤ ፓርቲው እና መንግስት አይቶ ሌላ አመራር እንዲመደብ ተደርጓል” ሲሉ አቶ ኢስሃቅ እርምጃው የተወሰደበትን ምክንያት አብራርተዋል።
የቤህነን አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባይወጡም፤ ከእነርሱ ጋር ተሹመው የነበሩት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራሮች ግን ሹመቱን ተቀብለው ወደ ስራ መግባታቸውን አቶ ኢስሃቅ አስረድተዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተቃዋሚ ፓርቲነት ሲንቀሳቀስ የቆየው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ በክልል ደረጃ ሁለት፤ በዞን ደግሞ አንድ ሹመቶችን አግኝቷል።
ባለፈው ጥቅምት ወር በተሰጠው በዚህ ሹመት፤ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አመንቴ ገሺ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬት አስተዳደር እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል። የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥራ አመራር ተቋም ዋና ዳይይሬክተር ሆነው ተሹመዋል። የዞን ሹመት የተሰጣቸው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ጅራ ናቸው። አቶ መልካሙ የመተከል ዞን ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሆነው ነው የተሾሙት።

ሹመት የሚሰጠው የገዢው ፓርቲን አሰራር ታሳቢ አድርጎ መሆኑን የሚገልጹት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሃቅ፤ ፓርቲው ሹመት የሰጠው ግለሰብ “ስራውን የማይሰራ ከሆነ አንስቶ ሌላ ሰው ይሾማል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ይህን መሰረት አድርጎ በተላለፈ ውሳኔም፤ ለቤህነን ሁለት ከፍተኛ አመራሮች ተሰጥቶ የነበረው የኃላፊነት ቦታ ተነጥቆ ለብልጽግና ፓርቲ አባላት ተሰጥቷል።
የቤህነን ሊቀመንበር ተመድበውበት በነበረው የገጠር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊነት ቦታ፤ የገዢው ፓርቲ አባሉ አቶ አልጄሊ ሙሳ መሾማቸው ትላንት የክልሉ መንግስት ባወጣው የምደባ ዝርዝር ተመላክቷል። ለቤህነን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተሰጥቶ የነበረው የትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊነትም፤ ለሌላው የብልጽግና ፓርቲ አባል አቶ ጃፈር ሃሩን መተላለፉን በዝርዝሩ ላይ ሰፍሯል።
በቤኒሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ መርቀኒ አዙቤር፤ ቤህነን “የተነጠቀው ሹመት ሲጀመርም ፓርቲው ያልተቀበለው ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የቤህነን አመራሮች ሹመቱን በተመለከተ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር ከአራት ወራት በፊት መነጋገራቸውን ያልሸሸጉት አቶ መርቀኒ፤ ሆኖም ፓርቲው የቀረበለትን የ“አብረን እንስራ” ጥያቄ መርምሮ ውድቅ አድርጎት ነበር ይላሉ።

በወቅቱ በነበረው ውይይት ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን፤ “የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በመንግስት መዋቅር ውስጥ የማሳተፍ ፕሮግራምን እንዴት ታዩታላችሁ?” ብለው የቤህነን አመራሮችን ጠይቀው እንደነበር አቶ መርቀኒ ወደ ኋላ መለስ ብለው አስታውሰዋል። በውይይቱ የቤህነን አመራሮች በሰላም እና ልማት ዙሪያ የክልሉን መንግስት ለማገዝ መስማማታቸውን ነገር ግን ሹመቱን በተመለከተ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅርበው ምላሹን ለርዕስ መስተዳድሩ እንደሚያሳውቁ ገልጸው መለያየታቸውን አስረድተዋል።
የቤህነን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከክልሉ መንግስት የቀረበለትን የ“አብረን እንስራ” ጥያቄ ያልተቀበለው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ህዝባችን እየታሰረ፣ እየተፈናቀለ፣ ሰላም በለሌበት የምን ስልጣን መጋራት ነው በሚል አንፈልግም ብለን [ጥያቄውን] ውድቅ አድርገናል” ሲሉ አቶ መርቀኒ ፓርቲው ሹመቱን ያልተቀበለበትን የመጀመሪያ ምክንያት ገልጸዋል።
ሁለተኛው ፓርቲው ጥያቄውን ውድቅ ያደረገበት ምክንያት “የክልሉ መንግስት ህጋዊ የሆነ መንግስት አይደለም” የሚል ነው። “በምርጫ የተመረጠ መንግስት አይደለም። በጉልበት ነው እየቀጠለ ያለው” የሚሉት አቶ መርቀኒ፤ የክልሉ መንግስት “ስልጣን ሊሰጥም ሊነሳም አይችልም ብለን እንደ ድርጅት ወስነናል” ሲሉ የፓርቲውን ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ አብራርተዋል።

በጸጥታ መደፍረስ እና በሰላም እጦት በሚቸገረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ባለፈው ዓመት ሰኔ 14 በተካሄደው ምርጫ የክልሉን መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ የለም። በወቅቱ የክልሉ ምክር ቤት ካሉት 99 መቀመጫዎች መካከል፤ ምርጫ የተካሄደው ለ34ቱ ብቻ ነበር።
ከ34ቱ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ገዢው የብልጽግና ፓርቲ፤ ሃያ ስምንቱን ሲያሸነፍ በስድስቱ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር። ገዢው ፓርቲ ምርጫ በተካሄደባቸው ቦታዎች ቢያሸነፍም፤ በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት ግን መንግስት ለመመስረት የሚያስችለውን የመቀመጫ ብዛት አላገኘም።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች መስከረም 20፤ 2014 ምርጫ ቢያካሄድም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግን ከዚህ ሂደት ውጭ ሆኗል። ክልሉ ከምርጫው ውጭ የሆነው፤ በካማሺ እና መተከል ዞኖች እንዲሁም በአሶሳ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በነበሩ የጸጥታ ስጋቶች ምክንያት ነው።

ምርጫ ቦርድ በክልሉ በታህሳስ ወር ምርጫ ለማካሄድ አቅዶ ዝግጅቶች ቢጀመርም፤ በሀገሪቱ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የምርጫ ዝግጅቱን ማቋረጡ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እስካሁንም እየተዳደረ ያለው ከስድስት ዓመት በፊት በተመረጡ ተመራጮች ነው።
አሁን ክልሉን እያስተዳደረ ባለው መንግስት ሹመቶች የተሰጡት የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፤ እንደ ቤህነን ሁሉ የክልሉ መንግስት “ህጋዊ አይደለም” የሚል አቋም አለው። የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መብራቱ አለሙ “አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ህጋዊ ነው የሚል እምነት የለንም። ይሄ በሆነበት ሁኔታ ህጋዊ ካልሆነ መንግስት ጋር ነው አብረን እየሰራን ያለነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር መብራቱ “በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን በመጮህ መግለጫዎች በማውጣት ያቀረብናቸው ነገሮች ውጤታማ ስላልሆኑ፤ ውጪ ሆነን ከምንጮህ እስኪ ውስጥ ሆነን የአቅማችንን ያህል እናበርክት ብለን ነው የወሰንነው” ሲሉ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ “ህጋዊ አይደለም” ከሚለው የክልሉ መንግስት ጋር አብሮ መስራት የጀመረበትን ምክንያት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)