በሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መንግስት ያዝ ያደረገው፤ በስጋት ምክንያት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ተናገሩ

የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ለጊዜው “ያዝ አድርጎ” እየሰራ ያለው “ስጋት ስላለበት” እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በሳዑዲ አረቢያ አሉ ከሚባሉት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ እርግጠኛ እንዳልሆኑ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከመካከላቸው “የሰለጠኑ ገዳዮች” እንዳሉበት እንደሚነገር ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፤ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ያሉ ዜጎችን ወደ ኢትዮጵያ የመመለሱ ሂደት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የፓርላማ አባል ከሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት እንኳን ቢሆን ቢሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ መመለሷን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ እንዳሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ከእነርሱ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ዜጎችን ጉዳይ መከታተል ለኢትዮጵያ መንግስት “ፈተና” እንደሆነበት አስረድተዋል። ከእነርሱ ውስጥ ምን ያህሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማወቁም አዳጋች እንደሆነ ገልጸዋል።  

“ሁሉም ፓስፖርት ያለው አይደለም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ሁሉም ከዚህ ሳዑዲ የሄደ መሆኑን ማወቅ ያስቸግራል። የሰለጠኑ ገዳዮች አሉበት ይባላል። ብዙ ነገር ነው የሚወራው። ቁጥሩ ደግሞ ብዙ ነው” ሲሉ የስደተኞቹ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከእነዚህ ውስጥ “የሰለጠኑ ገዳዮች አሉበት ይባላል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት ከመመለስ በፊት ጥናት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል። መንግስት ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት መመለስ እንዳልጠፋው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጉዳዩ “ቆም ብሎ ማጥናት፣ ማስላት ስለሚፈልግ”፤ “መከራም አብሮ እንዳይመጣ” በሚል ጊዜ መውሰዱን አስረድተዋል። 

“በደንብ አጥንተን ዜጎቻችን እንመልሳለን። ስንመልስ ጥፋት የሚያስከትሉ ሰዎች ካሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን። እንደዚያ አይነት አካሄዶች እና ምልክቶች ስላሉ፤ ስጋት ስላለብን ነው ነገሩን ያዝ አድርገን ቆም አድርገን እየሰራን ያለነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። 

በዚህ ሂደት የሚጎዱ “ንጹሃን ሰዎች” ሊኖሩ እንደሚችሉ የሚቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ሆኖም ከእነርሱ ጋር አብረው ያሉ ሰዎች ተቀላቅለው ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡ “የሚደርሰው ጥፋት እና አደጋ” ከፍ ያለ ሊሆን ይችል  እንደነበር አብራርተዋል። ጉዳዩን ይበልጥ “አደገኛ” ያደረገው፤ ኢትዮጵያ የነበረችበት ወቅታዊ ሁኔታ እንደነበርም አስረድተዋል። 

እንዲያም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ለመመለስ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። መንግስት ይህንኑ ጉዳይ የሚከታተል ልዑክ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ልኮ እንደነበር ያስታወሱት አብይ፤ በቅርቡም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ጉዳዩን የሚከታተል የሚኒስትሮች ኮሚቴ መቋቋሙን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)