በሃሚድ አወል
በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በቅርቡ ወደ ስፍራው ሊጓዝ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ የኮሚቴው ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያውያኑን የመመለሱ ስራ እንደሚጀመር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አስራ ስድስት የመንግስት ተቋማት የተካተቱበት የስደተኞች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ነው። የፍትህ ሚኒስቴር፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በኮሚቴው ከተካተቱ ተቋማት መካከል ናቸው።
የብሔራዊ ኮሚቴው ከ10 ቀናት ገደማ በፊት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙት ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በተዘጋጀው እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል። ኮሚቴው በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 100 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ማቀዱን አስታውቆ ነበር።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሲካሄድ የቆየው ዝግጅት ሊጠናቀቅ “ጫፍ” ላይ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ሳዑዲ አረቢያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አማካኝነት ስደተኞቹን የማጣራት፣ የመመዝገብ እና የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
“የዝግጅት ምዕራፉ እየተጠናቀቀ ነው። የዝግጅት ምዕራፉ እንደተጠናቀቀ ሁሉም እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ሀገር ቤት ይመለሳሉ” የሚሉት ዲና ሙፍቲ፤ “ማምጣት አንድ ነገር ነው። አምጥቶ ማስፈር ሌላ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ኢትዮጵያውያኑን የመመለሱ ሂደት “ውጣ ውረድ” ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ለሚደረግላቸው መልሶ ማቋቋም፤ ብሔራዊ ኮሚቴው ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ጨምረው ገልጸዋል። ለስደት ተመላሾች ስልጠና መስጠት እና ለስራ ምቹ ሁኔታዎቹን የመፍጠር ኃላፊነት የተሰጠው፤ የብሔራዊ ኮሚቴው አባል የሆነው የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ነው።
ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በቅርቡ ወደ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚጓዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ቢያስታውቁም፤ ኮሚቴው በጉብኝቱ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚጀምሩበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዲና፤ “ቀን አልተቆረጠም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችን ሁኔታ የሚከታተል ልዑክ ወደ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲልክ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የተመራ የልዑካን ቡድን ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዞ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር የስደተኞችን አያያዝ በተመለከተ መነጋገሩ ይታወሳል።

ከልዑካን ቡድኑ ጉብኝቱ በኋላ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ስደተኞቹን ለመመለስ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ቢገልጽም፤ የሂደቱ መዘግየት በተወካዮች ምክር ቤት ጭምር ጥያቄ አስነስቷል። ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ በነበረ የፓርላማ ስብሰባ ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ መንግስታቸው “ስጋት ስላለበት” የስደተኞቹን ጉዳይ “ያዝ” ማድረጉን ገልጸው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ሁሉም ፓስፖርት ያለው አይደለም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። ሁሉም ከዚህ ሳዑዲ የሄደ መሆኑን ማወቅ ያስቸግራል። የሰለጠኑ ገዳዮች አሉበት ይባላል። ብዙ ነገር ነው የሚወራው። ቁጥሩ ደግሞ ብዙ ነው” ሲሉ በመንግስታቸው በስጋትነት የተፈረጀውን ጉዳይ ለፓርላማ አባላት አብራርተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት፤ በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኙት 750 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መካከል 450 ሺህ ያህሉ በሀገሪቱ የሚኖሩት ህጋዊ ሰነድ ሳይኖራቸው ነው። በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት ስደተኞች ውስጥ “የሰለጠኑ ገዳዮች አሉበት ይባላል” ሲሉ በፓርላማ ስብሰባው ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “በደንብ አጥንተን ዜጎቻችን እንመልሳለን። ስንመልስ ጥፋት የሚያስከትሉ ሰዎች ካሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን” ሲሉ በጉዳዩ ላይ የሚከተሉትን አካሄድ አስረድተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)