የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልሎች የጋራ የልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አቋቋሙ

በሃሚድ አወል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልሎች በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ በልማት እና ሰላም ላይ የሚሰራ የጋራ የልማት ጽህፈት ቤት አቋቋሙ። ለሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ተጠሪ የሆነው ጽህፈት ቤቱ፤ የጸጥታ ችግሮች ሳይፈጠሩ በፊት የመከላከል ኃላፊነት እንደተጣለበትም ተገልጿል። 

ዋና መቀመጫው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የሚሆነው የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ፤ የጸጥታ ስጋት ምልክቶችን በመከታተል ግጭቶች እንዳይከሰቱ የማድረግ ስራዎችን ይሰራል ተብሏል። ጽህፈት ቤቱ ይህን የሚያደርገው፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከአማራ ክልል መንግስታት ጋር በመምከር መሆኑን የሁለቱ ክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ በመተከል ዞን እንዲሆን የተደረገውም፤ ተቋሙ ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ የሆነውን የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችለው በሚል መሆኑን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል። በመተከል “ጽንፈኛ ኃይሎች ጉዳት ሲያደርሱ ቆይተዋል” የሚሉት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ የጽህፈት ቤቱ መቋቋም “እንዲህ አይነት ችግሮችን ተነጋግሮ ለመፍታት የሚያስችል፤ ህዝቦች ከልማት ውጭ እንዲሆኑ እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን የሚቀርፍ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካሉት ሶስት ዞኖች መካከል የመተከል ዞን ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና ግጭቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። በጸጥታ ስጋት ምክንያት እስካሁን አጠቃላይ ምርጫ ካልተካሄደባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች መካከል የመተከል ዞን ይገኝበታል። 

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ አዲስ የተቋቋመው ጽህፈት ቤቱ የጸጥታ ስጋቶችን ከመከታተል ባለፈ ሌሎች ዓላማዎች አሉት ይላሉ። ጽህፈት ቤቱ “የሁለቱን አዋሳኝ ክልል ህዝቦች ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶችን ይቀርጻል” የሚሉት የዞኑ አስተዳዳሪ፤ ተቋሙ የትምህርት፣ ጤና እና መንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለጽህፈት ቤቱ የሚሆን ቢሮ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ እያዘጋጀ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጋሹ፤ ጽህፈት ቤቱን በኃላፊነት የሚመሩ ግለሰብም “በሁለት ሶስት ቀን ውስጥ” እንደሚታወቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጽህፈት ቤቱ በስሩ የቴክኒካል ባለሙያዎች እንደሚኖሩት የዞኑ አስተዳዳሪ አክለዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱን በኃላፊነት የሚመሩት ግለሰብ የሚወከሉት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሲሆን ምክትላቸው ደግሞ ከአማራ ክልል ይመደባሉ። “የእኛ [ሚና] የአጋዥነት ነው። ጽህፈት ቤቱን የሚመራው በዋናነት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው” የሚሉት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ ጽህፈት ቤቱን በምክትል ኃላፊነት የሚመሩ ግለሰብ በክልላቸው ከወዲሁ መመደባቸውን ገልጸዋል። 

የአማራ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መንግስታት ይህን ጽህፈት ቤት ለማቋቋም የጋራ መድረክ ሲያካሄዱ መቆየታቸውን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው፤ የተቋሙ ምስረታ እስካሁንም የዘገየው “በወቅታዊ አጀንዳዎች ነው” ምክንያት መሆኑን አብራራተዋል። የአማራ ክልል ከሌሎች ጋር በሚዋሰንባቸው እና ችግር ባለባቸው ተመሳሳይ ችግር ፈቺ ተቋማትን የመመስረት ሀሳብ እንዳለው የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)