በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ውጥረት መነሾ ምንም ይሁን ምን ሁለቱ አገሮች “ከየትኛውም ወታደራዊ እርምጃ እንዲቆጠቡ” የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ። የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ዛሬ ረቡዕ ባወጡት መግለጫ ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው የተፈጠረውን “የትኛውንም ውዝግብ” በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ጥሪ የቀረበው ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚወዛገቡበት የአል-ፋሽጋ አካባቢ ካለፉት ጥቂት ቀናት ወዲህ አዲስ ውጥረት ከተቀሰቀሰ በኋላ ነው። በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት “በጥልቅ ስጋት” እየተከታተሉ እንደሚገኙ የገለጹት ሙሳ ፋኪ ማህማት፤ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን በአፍሪካ ህብረት ስር ባለው ማዕቀፍ በኩል እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ማህማት የጠቀሱት የአፍሪካ ህብረት የድንበር ፕሮግራም በአባል አገራቱ መካከል በድንበር ይገባኛል የሚነሱ ውዝግቦችን ለመፍታት ከ15 ዓመታት በፊት ስራ ላይ የዋለ ነው። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር በዛሬው መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው አዲስ የድንበር ግጭት “ለሁለቱ አገሮች ውስጣዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመፈለግ የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሊያጨናግፍ እንደማይገባም” አሳስበዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በተመሳሳይ በዛሬው ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር የተፈጠረው መካረር እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። ሁለቱ ሀገሮች “ውጥረቱን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ” በዛሬው መግለጫቸው ጥሪ ያቀረቡት ዶ/ር ወርቅነህ፤ ለጉዳዩም “በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ” አሳስበዋል።
በሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል አዲስ ውጥረት የተቀሰቀሰው፤ በአወዛጋቢው አል-ፋሽጋ አካባቢ ሰባት የሱዳን ወታደሮች እና አንድ ሰላማዊ ሰው ባለፈው ሳምንት መገደላቸውን ተከትሎ ነው። በአል-ፋሽጋ አካባቢ ከተከሰተው ኩነት በኋላ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርኻን አካባቢውን ጎብኝተዋል። ከአል-ቡርኻን ጉብኝት አስቀድሞ ሱዳን በካርቱም የሚገኙትን የኢትዮጵያ አምባሳደርን በመጥራት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ጠይቃለች።
ሱዳን ወታደሮቹ የተገደሉት “በኢትዮጵያ ጦር ነው” ብትልም፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግን ከሱዳን በኩል የቀረበውን ክስ አስተባብሏል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “የሱዳን ወታደራዊ ኃይል፤ ከአሸባሪው እና ሰራዊታችንን በተለያየ ጊዜ ከከዱ አመራር እና አባላት ጋር ተቀናጅቶ የኢትዮጵያን ድንበር አልፎ እና ሰርጎ በመግባት በአካባቢው ሚሊሺያ እና ነዋሪ ላይ ጥቃት ፈጽሟል” ሲሉ ትላንት ማክሰኞ በሰጡት መግለጫ ወንጅለዋል።
ሱዳን ባወጣችው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “የሱዳን ወታደሮችን እና ሲቪል እንደገደለ፤ ምርኮኞችንም መቀጣጫ አድርጎ፤ ክብር ያልጠበቀ አያያዝ መያዙን” እንደገለጸች በመግለጫቸው ያስታወሱት ኮሎኔል ጌትነት፤ ክሱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “ባልነበረበት” የቀረበ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። በጥቃቱ ከሁለቱም ወገኖች ጉዳት መድረሱን በመግለጫቸው ያረጋገጡት ኮሎኔል ጌትነት፤ “ይህንን ሐቅ ገልብጦ ሰራዊታችን ባልነበረበት ቀድሞ ከሳሽ ሆኖ ቀርቧል” ሲሉ ሱዳንን ተችተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት እርምጃ እንዲወስድ ካዘዘ “በቂ ምክንያት ስላለን በመግለጫቸው እንዳሉት እንደ ሽፍታ ተደብቀን ሳይሆን፤ እንደመደበኛ እና ዘመናዊ ጦር፤ በግልጽ በታወጀ እና በታወቀ መልኩ፤ በኃይል ከተያዘ ግዛታችን አስወጥተን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና እንዳለን ለመግለጽ እንወዳለን” ሲሉም ኮሎኔል ጌትነት አስጠንቅቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)