በሃሚድ አወል
ኢትዮ ቴሌኮም በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የደንበኞቹ ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ በ10 በመቶ ያድጋል የሚል ትንበያ እንዳለው የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ አስታወቁ። በተመሳሳይ ወቅት የተቋሙ ገቢም ከ17 እስከ 22 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል የሚል ትንበያ ማስቀመጡን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ፍሬህይወት ይህን ያሉት፤ የሚመሩትን ተቋም የሶስት ዓመት የዕድገት ስትራቴጂ እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ ዛሬ ሰኞ መስከረም 16 ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው። ፍሬህይወት በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ “ወድድር ቢኖርም፤ የሰራነው ትንበያ በሶስቱም አመት በደንበኞች ቁጥርም እንደዚሁም በገቢ [ረገድ] በዕድገት የሚጠናቀቅ ነው” ብለዋል።

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ዛሬ ይፋ ያደረገው የዕድገት ስትራቴጂ “መሪ” የተሰኘ እና ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ነው። ተቋሙ የዕድገት ስትራቴጂውን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚተገብርበት የ2015 በጀት ዓመት፤ የደንበኞቹን ቁጥር 73.5 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ አለው።
ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት የደንበኞቹ ብዛት 44.6 ሚሊዮን ነበር። የተቋሙ ደንበኞች ቁጥር በተከታዩ ዓመት የ10 ሚሊዮን ጭማሬ አሳይቶ 56.2 ሚሊዮን ደርሷል። ይህ የደንበኞች አሃዝ ከ2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ22 በመቶ እድገት ያሳየ ነው።
ተቋሙ የ2014ን በጀት ዓመት ያጠናቀቀው የደንበኞቹን ቁጥር በ18 በመቶ በማሳደግ፤ 66.59 ሚሊዮን ማድረሱን በማስታወቅ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ፤ ይህን የደንበኞች ቁጥር 10.3 በመቶ የማሳደግ ዕቅድ ይዟል። ይህ የደንበኞች ዕድገት፤ አዲሱ የኢትዮ ቴሌኮም ስትራቴጂ በቀጣይነት በሚተገበርባቸው መጪ ሁለት ዓመታትም በተመሳሳይ መጠን “እያደገ ይቀጥላል” የሚል ትንበያ እንዳላቸው ፍሬህይወት በዛሬው መግለጫቸው ጠቁመዋል።

የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያው በገቢ ረገድም እድገት ለማስመዘገብ ወጥኗል። ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 በጀት ዓመት ያገኘው 61.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ በተያዘው በጀት ዓመት ይህን መጠን ወደ 75.05 ቢሊዮን ብር የማሳደግ ዕቅድ አለው። “በገቢ [ረገድ] በዚህኛው በጀት ዓመት የያዝነው 22 በመቶ ለማሳደግ ነው። የሁለቱን ዓመት ደግሞ እስከ 17 በመቶ እንዲያድግ አድርገን ስትራቴጂውን ቀርጸነዋል” ሲሉ ፍሬህይወት ተናግረዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተቋማቸው የሶስት ዓመት ስትራቴጂ “በዕድገት የሚጠናቀቅ ሆኖ መነደፉን” በመግለጫቸው ቢያሳውቁም፤ ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ የሙከራ አገልግሎት መስጠት ከጀመረው ሌላኛው የቴሌኮሚዩኒኬሽን ኩባንያ ሳፋሪኮም ውድድር እንደሚጠብቀው አልሸሸጉም። ባለፈው ነሐሴ ወር የኔትወርክ የሙከራ አገልግሎቱን በድሬዳዋ ከተማ የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፤ በሶስት ሳምንት ብቻ አገልግሎቱን የሚያገኙ ከተሞችን ወደ ስምንት አሳድጓል።
የኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ኬንያ ሰፊ የገበያ ድርሻ ያለው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተከትሎ፤ ኢትዮ ቴሌኮም የሚገጥመውን የደንበኞች ፍልሰት ለመቆጣጠር ምን ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ለተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ፍሬህይወት በምላሻቸው “ዝርዝር ስትራቴጂውን ለመናገር ብቸገርም፤ ደንበኞቻችንን ማቆያ ስትራቴጂ አለን” ብለዋል።

ለረዥም ጊዜ ብቸኛው የቴሌኮም አቅራቢ ሆኖ የቆየው ኢትዮ ቴሌኮም “የደንበኞች ማቆያ ስትራቴጂውን” ተግባራዊ የማድረግ ስራ መጀመሩንም ፍሬህይወት በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ዝርዝር ስትራቴጂውን ይፋ ከማድረግ ቢቆጠቡም፤ ተቋሙ ባለፉት አራት ዓመታት ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ የዚሁ ስትራቴጂ አንድ አካል መሆኑን በገደምዳሜ ተናግረዋል።
“አንዱ አማራጭ ዋጋ ቀንሶ በመግባት ደንበኛን ማግኘት ነበር” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ፍሬህይወት፤ “ኢትዮ ቴሌኮም የሰራው ስራ ዋጋ ቀንሶ ለመግባት የማይቻልበትን ሁኔታ ፈጥሯል” ብለዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ከ2011 እስከ 2014 ድረስ ለአራት ዓመታት በቆየውና “ድልድይ” በተሰኘው ስትራቴጂው እስከ 86 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ አድርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ቅናሽ በማድረግ በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት ቢችልም፤ ሳፋሪኮም የተሻለ በሆነበት የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ዕድል ግን ተግዳሮቶች እንዳሉበት ፍሬህይወት አልሸሸጉም። መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ በተያዘው በጀት ዓመት 153 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት አቅዷል። ይህ የተቋሙ ዕቅድ ባለፈው ዓመት ካገኘው የ146.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር፤ የሶስት በመቶ ብልጫ አለው።

“የኢትዮጵያን የቴሌኮም ገበያ የተቀላቀለው፤ ኢትዮ ቴሌኮምን face ለማድረግ ወይም challenge ለማድረግ የመጣው አንድ ኩባንያ አይደለም። በጥምር አምስት ኩባንያዎች ናቸው አንድ ላይ ሆነው የመጡት። [እነርሱ] የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ያላቸው እንደመሆናቸው፤ ለእኛ የውጭ ምንዛሬ ውስን እንደመሆኑ፤ ይህንን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅፋት እንዳይሆንብን [የተለያዩ] የፋይናንስ አማራጮችን እንጠቀማለን” ሲሉ ፍሬህይወት ተቋማቸው የሚከተለውን አካሄድ አስረድተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በስትራቴጂ ዘመኑ እንደ ዋና “ስጋት እና ተግዳሮት” ከወሰዳቸው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት እጥረት እና የገበያ ውድድር ባሻገር በሀገሪቱ ካለው የጸጥታ ችግር ጋር በተገናኘ “አገልግሎት መስጠት አለመቻል” ፈተና ሊደቅንበት እንደሚችል አስታውቋል። የገበያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ግሽበት እንዲሁም የመሰረተ ልማት ውድመት በተመሳሳይ ተቋሙ “ስጋት እና ተግዳሮት” ይሆናሉ ያላቸው ሌሎች ጉዳዮች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)