በአማኑኤል ይልቃል
የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎች የደንበኞቻቸውን ማንነት ለመለየትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችን እንዲያዘጋጁ እና “አጠራጣሪ ግብይቶች” ሲያጋጥሟቸው ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተቋም ሪፖርት እንዲደርጉ የሚያዝ መመሪያ ተዘጋጀ። በመመሪያው መሰረት፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች ስለደንበኞቻቸው የሰበሰቧቸውን መረጃዎች ለ10 ዓመታት የማከማቸት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
በፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተቋም የተዘጋጀው ይህ መመሪያ፤ “በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በ2008 ዓ.ም. የወጣውን አዋጅ መሰረት አድርጎ ነው። መንግስታዊው ተቋም መመሪያውን ያወጣው፤ “የባለሞተር ተሽከርካሪዎች” ግዢን በመጠቀም በአዋጁ የተጠቀሱ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል መሆኑን በአገልግሎቱ የሱፐርቪዥን ቡድን መሪ የሆኑት ሙሉጌታ ተመስገን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

መመሪያው “የባለሞተር ተሽከርካሪዎች” በሚል ምድብ ውስጥ የሚያስቀምጣቸው፤ የግል አውቶሞቢል፣ የሕዝብ ማመላለሻ፣ የጭነት ማመላለሻ፣ ጎታች መኪና፣ ባለሞተር ብስክሌት እና ልዩ ተንቀሳቃሽ መሳሪያዎችን ነው። እነዚህ ተሽከርካሪዎች በመካኒካል ወይም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀኑ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመመሪያው ሰፍሯል።
አዲሱ መመሪያ የሚመለከታቸው “የተሽከርካሪ ነጋዴዎች”፤ የባለሞተር ተሽከርካሪዎችን የሚያመርቱ፣ ከውጭ ሀገራት የሚያስመጡ፣ ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ፣ የሚያከፋፍሉ፣ የሚቸረችሩ፣ የሚያከራዩ፣ ለሽያጭ የሚደለድሉ እና ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸው በመመሪያው ተቀምጧል። በ2008 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ መሰረት፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ፤ የተሰየሙ የንግድ እና የሙያ ስራዎች” ዘርፍ ውስጥ የሚወድቁ ናቸው።
የ2008ቱ አዋጅ እነዚህን የንግድ እና የሙያ ስራዎች የመሰየም ኃላፊነት፤ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ተቋም ሰጥቶ ነበር። የባለሞተር ተሽከርካሪዎች የንግድ ዘርፍን ስያሜ በመስጠት መመሪያ ማውጣት ያስፈለገው፤ የንግድ ስርዓቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለሚፈጽሙ ግለሰቦች “መደበቂያ ዘርፍ በመሆኑ ምክንያት ነው” ሲል በተቋሙ የተዘጋጀው ማብራሪያ ያትታል።

ተቋሙ የተሽከርካሪ ነጋዴዎችን በዚህ ስያሜ ውስጥ የማካተት እቅድ የያዘው ከአምስት ዓመት በፊት እንደነበር የሚናገሩት የሱፐርቪዥን ቡድን መሪው አቶ ሙሉጌታ፤ እስካሁን የዘገየው በመስሪያ ቤቱ በነበረው የኃላፊዎች መቀያየር፣ በኮሮና ወረርሽኝ እና በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ መሆኑን አብራርተዋል።
የተሽከርካሪ ነጋዴዎችን “ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ የንግድ ስራዎች” ዘርፍ የሚሰይመው መመሪያ ለፍትህ ሚኒስቴር ተላልፎ ይፋዊ ምዝገባውን ያጠናቀቀው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር። መመሪያው በፍትህ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ላይ ከተመዘገበ በኋላ የጸና እንደሚሆን ተደንግጓል። በሶስት ክፍሎች እና በ16 አንቀጾች በተዋቀረው በዚህ መመሪያ ከተካተቱ “አስገዳጅ መስፈርቶች” መካከል፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች የደንበኞቻቸውን ማንነት ለማወቅ የሚያስችሉ “የጥንቃቄ እርምጃዎችን” መውሰድ እንዳለባቸው የሚገልጸው ይገኝበታል።
ከእነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች ውስጥ አንዱ፤ “የተሽከርካሪ ነጋዴዎች ስለ ደንበኞቻቸው መረጃ መያዝ ይገባቸዋል” ይላል። በአገሪቱ ውስጥ ያለው የመኪና ግብይት እንቅስቃሴ “ከፍተኛ” መሆኑን የሚናገሩት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ፤ የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “በተደጋጋሚ ግዢ የሚፈጽሙ ደንበኞች ካሏቸው” ስለ እነሱ መረጃ መያዝ፣ መረጃውንም ለቁጥጥር ክፍት እንዲያደርጉ በመፈለጉ ምክንያት ይህ አንቀጽ በመመሪያው መካተቱን ያስረዳሉ።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የክትትል ባለሙያዎች፤ በግብይት ወቅት የሚሰበሰቡትን እነዚህን መሰል መረጃዎች በተለያዩ ጊዜያት በመውሰድ ፍተሻ እንደሚያደርጉ አቶ ሙሉጌታ ያስረዳሉ። የተሽከርካሪ ነጋዴዎቹ የተቋሙ ሰራተኞች ለሚያከናውኑት የቁጥጥር ስራ ከሚያቀርቡት መረጃ ባሻገር፤ “ጥርጣሬን የሚያጭር” ግብይት ሲያጋጥማቸውም ለተቋሙ ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት በመመሪያው እንደተጣለባቸው ጨምረው ገልጸዋል።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት “ጥርጣሬን የሚያጭር ግብይት” የሚባለው፤ ነጋዴው “ለግብይት የቀረበለት ገንዘብ የወንጀል ፍሬ ስለመሆኑ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዘ ወይም የተገናኘ አሊያም ለዚሁ ተግባር ሊውል የሚችል ስለመሆኑ ለመጠርጠር በቂ ምክንያት ሲኖረው” ነው። አንድ ደንበኛ ከፍተኛ በሆነ የገንዘብ መጠን ባለሞተር ተሽከርካሪን ለመግዛት ከሞከረ እንዲሁም ማንነቱን የሚገልጹ ሰነዶችን እንዲያቀርብ ሲጠየቅ ከተቃወመ፤ ግብይቱን “በጥርጣሬ” ለመመልከት “ጠቋሚ” እንደሚሆን በመመሪያው ላይ ተቀምጧል።
ደንበኛው ግዢውን ለመፈጸም ኢኮኖሚያዊ አቅም ከሌለው አሊያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዛት ያላቸው ተሸከርካሪዎችን ከገዛ “በጥርጣሬ ግብይትነት” ሊታይ እንደሚቻል በመመሪያው ሰፍሯል። “ደንበኛው ከፍተኛ የሆነ ቅድመ ክፍያ በጥሬ ገንዘብ የከፈለ እንደሆነ” አሊያም “የወንጀል የኋላ ታሪክ ያለው መሆኑ የሚታወቅ ከሆነ” ግብይቱን በጥርጣሬ ለመመልከት ጠቋሚ እንደሆነ በመመሪያው ተገልጿል።

በእነዚህ ጠቋሚዎች መነሻነት ነጋዴው ግብይቱ “የጥርጣሬ ግብይት ነው” ብሎ ሲያምን፤ ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ይኖርበታል። ይሁንና ግብይቱን በተመለከተ ለተቋሙ ሪፖርት ሊቀርብ መሆኑን “በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ በማንኛውም ሁኔታ ወይም መንገድ፤ ለማንኛውም ሰው፣ ድርጅት ወይም ሚዲያ መግለጽ የተከለከለ” መሆኑ በመመሪያው ተደንጓል።
የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “የጥርጣሬ ግብይትን” ከማሳወቅ በተጨማሪ፤ ደንበኞቻቸውን የተመለከቱ “የስጋት ዳሰሳ ጥናት ማድረግ” እንደሚጠበቅባቸው በአዲሱ መመሪያ ተመላክቷል። የተሽከርካሪ ነጋዴዎች “ደንበኞቻቸው የሚደቅኑትን የስጋት ልክ ለመለየት ያስችላቸው ዘንድ ከደንበኞቻቸው አስፈላጊ መረጃዎችን መቀበል” እንዳለባቸውም ያክላል። የደንበኞችን ማንነት የማጣራት ስራው የሚከናወነው “ተዓማኒ፣ ከገለልተኛ ምንጭ የተገኙ ሰነዶችን፣ ዳታዎችን ወይም መረጃዎችን” በመጠቀም እንደሆነ በመመሪያው ሰፍሯል።
የባለሞተር ተሽከርካሪ ነጋዴዎች በዚህ መልክ ስለደንበኞች የሰበሰቧቸውን መረጃዎችን፤ ለ10 ዓመታት የማከማቸት ግዴታም በአዲሱ መመሪያ ተጥሎባቸዋል። በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን ድንጋጌዎች የሚተላለፉ ግለሰቦች የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚኖርባቸው በድንጋጌው ላይ ቢሰፍርም፤ የሚከተሉት ቅጣቶች ግን ምን እንደሆኑ በግልጽ አልተቀመጠም። ይህን እና ሌሎችንም በመመሪያው ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ጥያቄ ብናቀርብም፤ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)