አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅርቡ ውላቸው የተቋረጠ 68 ቦታዎችን ለሊዝ ጨረታ ሊያቀርብ ነው

በአማኑኤል ይልቃል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው” በቅርቡ ውላቸው እንዲቋረጥ የተደረጉ 68 ቦታዎችን ለሊዝ ጨረታ ሊያቀርብ ነው። እነዚህ ቦታዎች ለጨረታ የሚቀርቡት፤ ከዚህ ቀደም የጨረታ ሰነድ ከተዘጋጀላቸው 109 ቦታዎች ጋር መሆኑን የከተማው የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል።

የከተማው አስተዳደር ለጨረታ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸውን 68 ቦታዎች ውል በማቋረጥ፣ ካርታቸው እንዲመክን ያደረገው፤ ለግለሰቦች እና ለባለሀብቶች ከተላለፉ በኋላ “ለበርካታ ዓመታት ታጥረው” በመቀመጣቸው መሆኑን ከሁለት ሳምንት በፊት ገልጾ ነበር። የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከዚያ ወዲህ ባሉት ጊዜያት፤ ቦታዎቹን ለጨረታ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አዋቅሮ የማጣራት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን በመስሪያ ቤቱ የመሬት ማስተላለፍና ሊዝ ክትትል ዳይሬክተር አቶ ደስታ መርጋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ኮሚቴው እስካሁን 30 ያህሉን ቦታዎች አጣርቶ እንዳቀረበ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በመጪው ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከቀሪዎቹ ቦታዎች ውስጥ ለጨረታ መቅረብ የሚችሉትን በድጋሚ አጣርቶ እንዲያቀርብ የጊዜ ገደብ መሰጠቱን አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በኮሚቴው የተለዩትን እና በቀጣይ ማጣራት የሚደረግባቸውን ቦታዎች ለሊዝ ጨረታ ለማቅረብ ያቀደው፤ ባለፈው ዓመት የጨረታ ሰነድ ካዘጋጀላቸው 109 ቦታዎች ጋር አብሮ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። 

የከተማው አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ ቀደም ሲል የተዘጋጁት ቦታዎች ቁጥር እና ስፋት በከተማዋ ካለው ፍላጎት አንጻር አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ የአዲስ አበባ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የ109 ያህሉ ቦታዎች አጠቃላይ ስፋት “ከሶስት ሄክታር የማይበልጥ” እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ኃላፊው፤ በድጋሚ ለጨረታ እንዲቀርቡ የታቀዱት 68 ቦታዎች አጠቃላይ ስፋት በአንጻሩ  90 ሔክታር መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት የጨረታ ሰነድ ከተዘጋጀላቸው ቦታዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነው። ከእነዚህ ቦታዎች ውስጥ ለመኖሪያ እና ለንግድ ተብለው የተመደቡ ቢኖሩም፤ አብዛኛዎቹ “ለቅይጥ አገልግሎት” የሚውሉ መሆናቸውን የመሬት ማስተላለፍና ሊዝ ክትትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። አሁን በኮሚቴ በመለየት ላይ ያሉት ቦታዎች መገኛቸው የት እንደሆነ እና ለምን አገልግሎት እንደሚውሉ ጥያቄ የቀረበላቸው ዳይሬክተሩ፤ ይህን መናገር የሚቻለው በአጠቃላይ ማጣራቱ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። 

እነዚህ ቦታዎች “ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ” ቢሆኑም፤ ስራ የተጀመረባቸው እና ንብረት የሚገኝባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ አጣሪ ኮሚቴው ከዚህ ነጻ የሆኑትን ቦታዎች የመለየት ኃላፊነት እንደተጣለበት ገልጸዋል። የአዲስ አበባ የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊም “አንዳንድ ቦታዎች claim ሊኖርባቸው ይችላል። ጨረታ ሲወጣ ደግሞ ከማንኛውም ይገባኛል እንዲጸዳ ይደረጋል” ሲሉ የዳይሬክተሩን ገለጻ የሚያጠናክር ሀሳብ ሰንዝረዋል። 

የማጣራት ስራው ጊዜ ሳይወስድ በቶሎ ለመጨረስ ቢሯቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሲሳይ፤ ይህ እንደተጠናቀቀ በቢሮው ውስጥ የሚገኘው የጨረታ ኮሚቴ ቦታዎቹን ተረክቦ “በቀጥታ ወደ ጨረታ ሂደት” እንደሚገባ አብራርተዋል። በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የሊዝ ጨረታ፤ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ሲደረግ የመጀመሪያው ይሆናል።   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በከተማዋ የሚገኙ ቦታዎችን በመለየት ለግልጽ ጨረታ እንዲቀርቡ ውሳኔ ያስተላለፈው ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ነበር። ባለፉት ዓመታት ቦታዎች ለጨረታ ሳይቀርቡ መቆየታቸው በከተማው ውስጥ ያለውን መሬት የማግኘት ፍላጎት እንደጨመረው የሚገልጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በቅርቡ በሚወጣው ጨረታ ለሊዝ የሚቀርቡ መሬቶችም ቢሆን “ባለው ፍላጎት ልክ” አለመሆኑን ቢሯቸው እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ጨረታ በወጣ “ሶስት ወራት ገደማ” ጊዜ ውስጥ ሌላ ጨረታ የማውጣት እቅድ እንዳለው አቶ ሲሳይ አክለዋል። የከተማ አስተዳደሩ ቦታዎቹን ለጨረታ የሚያቀርበው፤ በጥር 2013 ዓ.ም ባጸደቀው የሊዝ መነሻ ዋጋና የቦታ ደረጃዎች መሰረት ነው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ጥናት ላይ ተመርኩዞ በተዘጋጀው በአዲሱ ደረጃ መሰረት፤ ለጨረታ የሚቀርቡ ቦታዎች በ18 የተለያዩ ደረጃዎች ይከፋፈላሉ። 

ለጨረታ የሚቀርቡ ቦታዎች የተለያየ ደረጃ የሚሰጣቸው፤ የሚገኙበት ስፍራ እና በዙሪያቸው ያለውን መሰረተ ልማት ከግምት በማስገባት ነው። በደረጃው በቀዳሚነት የሚቀመጥ ቦታ ለጨረታ የሚቀርብበት መነሻ ዋጋ፤ በካሬ ሜትር 2,213 ብር ነው። በምደባው የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚያርፍ ቦታ ደግሞ በካሬ ሜትር 748 ብር መነሻ ዋጋ ለጨረታ ይቀርባል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)