በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “መንግስትን ለመጣል ከአንዳንድ ክልሎች ከፍተኛ ፍልሰት” እየተደረገ መሆኑን አስታወቀ። ወጣቶችን በማነሳሳት “ወደ ጥፋት ለመግባት” እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን ያስታወቀው፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 5፤ 2015 በተጀመረው የከተማዋ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ በቀረበ ሪፖርት ነው። የከተማ አስተዳደሩን የአፈጻጸም ሪፖርት በንባብ ያቀረቡት የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ አበባን “የሁከት አውድማ” ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከንቲባዋ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝብ የመረጠውን ህጋዊ መንግስት በመጣል በኃይል ስልጣን ለመቆጣጠር በማለም፤ ከአንዳንድ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ከፍተኛ ፍልሰት” የጸጥታ ስጋት መሆኑን ለምክር ቤት አባላቱ አስታውቀዋል። በከተማዋ ውስጥ የሚታየው “ጽንፈኝነት፣ ጥላቻ እና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት” የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፤ የከተማ አስተዳደሩን አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ እንዳይሆን ማድረጋቸውንም አዳነች በሪፖርታቸው ላይ ገልጸዋል።
በከተማዋ ውስጥ የሚታዩት እንቅስቃሴዎች “ስርዓት አልበኝነት እና የመሬት ወረራ” እንዲስፋፋ እያደረጉ መሆናቸውንም ከንቲባዋ አክለዋል። “ሰላማችንን ለማደፍረስ እንቅልፍ ያጡ የጥፋት ኃይሎች፤ ህዝብን በማደናገር እና በማወናበድ በተለይም ወጣቱን በውሸት ፕሮፓጋንዳ በማነሳሳት ወደ ጥፋት ለመማገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ ማንም የማይጠቅም ተቀባይነት የሌለው [ነው]” ብለዋል ከንቲባዋ።
ከንቲባ አዳነች ያቀረቡትን የከተማ አስተዳደሩን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ተከትሎ፤ ከምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ቀርበዋል። “ከአንዳንድ ክልሎች በከፍተኛ መጠን ወደ ከተማዋ ይገባሉ” የተባሉ “ፍልሰተኞችን” ጉዳይ ያነሱት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የተባሉት የምክር ቤት አባል፤ “አንዳንድ ክልሎች የሚለው አገላለጽ ምን ማለት ነው? ክልሎቹ ቢገለጹ” ሲሉ ጠይቀዋል። ሪፖርቱ ላይ “ከአንዳንድ ክልሎች የሚመጡ ሰዎች እንደዚሁ ሁከት እና ብጥብጥ ለመፍጠር አስበው ወይም ህጋዊውን መንግስት ለመገልበጥ አሲረው” በሚል የተቀመጠው ሃሳብ ያልተብራራ መሆኑንም የምክር ቤት አባሉ በጥያቄያቸው አንስተዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ በቅድሚያ ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ናቸው። ኮሚሽነሩ የአደባባይ በዓላትን “እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ረብሻ እና ሁከት” ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች መኖራቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። በአደባባይ በዓላት ላይ ለመፍጠር የሚፈለገው ችግር “በተቀናጀ መንገድ” የሚመራ መሆኑን ያስረዱት ኮሚሽነር ጌቱ፤ ለዚሁ ሲባል “ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ኃይሎች” መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
“ፍልሰቱ የተለመደ ነው ከሁሉም አካባቢ ሰው ይመጣል። ነገር ግን በዓላት ሲቃረቡ የተለያየ ተልዕም ተሰጥቷቸው የሚመጡ [አሉ]። ባሳለፍነው ሁለት እና ሶስት ዓመታት የምናውቃቸው ተጨባጭ የሆኑ መረጃዎች አሉ” ሲሉም ይህ ጉዳይ በዚህ ዓመት ብቻ የታየ አለመሆኑን ገልጸዋል። ከየትኞቹ ክልሎች የሚመጡ ሰዎች በብዛት ወደ አዲስ አበባ እንደሚገቡ ሲያስረዱም፤ “64 ፐርሰንት የሚሆኑ ከአማራ ክልል አካባቢ ነው የመጡት። 21 ፐርሰንት የሚሆኑት ከደቡብ አካባቢ ነው። 14 ፐርሰንት ከኦሮሚያ ነው” ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማም ተመሳሳይ ማብራሪያ አቅርበዋል። “በርከት ያሉ ኃይሎች ሰላም እና ጸጥታ ለማደፍረስ” ወደ ከተማ እንደሚገቡ የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ የመጀመሪያውን ስፍራውን የሚይዙት “ከአማራ ክልል የሚገቡ ኃይሎች” መሆናቸውን አስረድተዋል። ከደቡብ እና “ከኦሮሚያ አጎራባች ክልሎች አካባቢ” ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎች በተከታታይ ደረጃ እንደሚቀመጡም አክለዋል።

“ችግሩን በተደራጀ መልኩ ይዞ መጥቶ፤ ከተማዋን ለመበጥበጥ የሚፈልግ ኃይል አለ” ያሉት ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋ፤ የምክር ቤቱ አባላት “ተልዕኮ ይዞ የሚገባ ኃይል” እንዳለ ሊረዱ እንደሚገባ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ “ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ፖለቲካ እና መደበኛ ወንጀል መከላከልን ማዕከል ያደረጉ” የጸጥታ መደፍረሶች እንዳሉ የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ከእነዚህ የፀጥታ ችግር መነሻዎች ውስጥ “ከተማዋን በተደጋጋሚ እየፈተናት ያለው” በዓላትን መነሻ ባደረጉ እና “የፖለቲካ ፍላጎት” ባላቸው ኃይሎች የሚፈጸመው መሆኑን አብራርተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የቢሮ ኃላፊዎች እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ ከሰጧቸው ማብራሪያዎች በኋላ ከንቲባ አዳነች የማጠቃለያ ሀሳብ ሰጥተዋል። የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮችን በቅድሚያ ያነሱት ከንቲባዋ፤ በዓላትን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት በተመለከተ “ዳታው ቅድም የሰማችሁት ነው” ሲሉ በከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን የቀረበውን የቁጥር ገለጻ አስታውሰዋል። ወደ ከተማዋ የሚፈልሱት ሰዎች የሚመጡባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ “በጣም ከፍተኛ፣ አንጻራዊ ያልሆነ መበላለጥ” መኖሩንም ተናግረዋል።
ይሁንና በከተማዋ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች በሙሉ ከከተማዋ ውጪ በሚመጡ ሰዎች የተፈጸሙ እንዳልሆኑ ከንቲባዋ በዛሬው የምክር ቤቱ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ አንስተዋል። “ሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው ‘ሁሉም ከከተማው ውጪ ነው’ የሚል አይደለም። ከተማው ውስጥ ባለው ኔትወርክ ነው ወደ ከተማው ውስጥ የመጡት” ያሉት አዳነች፤ “የተለያየ ጥቅም እና የፖለቲካ ትርፍን” ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ለዚሁ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ገልጸዋል።

“የመንግስት ስልጣንን በህጋዊ መንገድ ያላገኙ አካላት፤ በተለያየ መንገድ እነኚህን በተለየ ሁኔታ በመቀስቀስ እና ተልዕኮ በመስጠት ወጣቶችን ወደ ጥፋት በመማገድ” ላይ ተሰማርተው መታየቱን ጠቅሰዋል። እንደዚህ አይነት ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ የምክር ቤቱ አባላት በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ላይ “ጥንቃቄ” እንዲያደርጉም ከንቲባዋ በማጠቃለያቸው ላይ አሳስበዋል።
“ችግሮች በሚፈጸሙበት ሰዓት በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች በመጻፍ፣ አነቃቂ ንግግር በሚመስል፣ በተለያየ መንገድ፤ እኛ ልንሞገስበት ህዝቡ ግን ዋጋ ሊከፍልበት የሚደረገው ድርጊት መታረም ያለበት ነው” ሲሉ አዳነች ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። የምክር ቤቱ አባላት “የሚያደርጓቸው፣ የሚናገሯቸው እና የሚፈጽሟቸው” ነገሮች “የህዝብን ሰላም እና ደህንነትን ያገናዘበ” መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።
በዛሬው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ውሎ ላይ የተነሳው “ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ” የተባሉ “ፍልሰተኞች” ጉዳይ፤ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተቃውሞ ገጥሞታል። ፓርቲው ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ በከተማዋ ከንቲባ የቀረበውን ሪፖርት “አደገኛ፣ ከፋፋይ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ” ሲል ነቅፎታል።

የቀረበው ሪፖርት “አገረ መንግስቱን አደጋ ላይ የሚጥል” መሆኑን የገለጸው አብን፤ “በማናቸውም መመዘኛ ተቀባይነት የሌለው የዓለም አቀፍ ወንጀል ጥሪ ነው” ሲልም አውግዞታል። የዜጎች በነፃነት ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብቶች “ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥምምነቶች ድንጋጌዎች እና በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግስት ጭምር የተረጋገጡ ተፈጥሯዊ መብቶች” መሆናቸውን አብን በዚሁ መግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ፓርቲው “ከክልሎች የሚመጡ ፍልሰተኞችን” በተመለከተ በምክር ቤቱ የቀረበውን ሪፖርት፤ “እስካሁን ሲፈጸሙ ለነበሩ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች እና እየታወጀ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከለላ የሚሆን አሳፋሪ የወንጀል ድርጊት ጥሪ ነው” ሲል ኮንኖታል። የፌደራል መንግስት እና ገዢው ብልፅግና ፓርቲ “ይኼንን አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ያደረጉትን ግለሰብ ከስልጣን እንዲያነሳ እና ለፍርድ እንዲያቀርብ” አብን ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ዝርዝር መረጃዎች ከቆይታ በኋላ ታክለውበታል]