በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፋለሙ ሁሉም ኃይሎች “የጦር ወንጀል” መፈጸማቸውን አሜሪካ ይፋ አደረገች

አሜሪካ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉ ሁሉም ኃይሎች “የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሷን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ። በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች፤ የአማራ ኃይሎች “የዘር ማጽዳት” እና “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል” መፈጸማቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው አስታውቀዋል።   

ብሊንከን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በተመለከተ ሀገራቸው የደረሰችበትን መደምደሚያ ያስታወቁት፤ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሀገራት በ2022 የነበረውን የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ የሰነደ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዓመታዊ ሪፖርት ዛሬ ሰኞ መጋቢት 11፤ 2015 ይፋ ሲደረግ ነው። ይህ የአሜሪካ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ይዞታ ሪፖርት፤ በስድስት ጎራ የተከፋፈሉ 198 አገሮች እና ግዛቶችን የተመለከተ ነው።

የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪፖርቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ በኢራን፣ አፍጋኒስታን፣ በርማ፣ ቻይና እና ኩባ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ቢጠቃቅሱም፤ ሰፊ ጊዜ የሰጡት ግን የኢትዮጵያን ጉዳይ ነበር። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች ፈጽመውታል ያለው ድምዳሜ ላይ የደረሰው፤ “ሕጉን እና እውነታውን በጥንቃቄ ካጠና በኋላ” መሆኑን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት፣ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች እና የአማራ ኃይሎች፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት የጦር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሼያለሁ” ሲሉ ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው ወቅት ተናግረዋል። “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ኃይሎች፤ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች እና ማሰቃየትን ጨምሮ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል” ሲሉም  አክለዋል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው፤ የአማራ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ፈጽመዋቸዋል ያሏቸውን ወንጀሎችንም በተጨማሪነት አንስተዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የአማራ ኃይሎች በምዕራብ ትግራይ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ “በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ ማፈናቀል ወይም በግዳጅ ማዛወር እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ፈጽመዋል።” 

ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት ብሊንከን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት ህወሓትን በመወከል ፊርማቸው ካኖሩት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ተገናኘተው ተወያይተዋል። ከብሊንከን ጉብኝት ጥቂት ቀናት በኋላ፤ አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በህወሓት መታጨታቸው ይፋ ተደርጓል። 

ብሊንከን በኢትዮጵያ የነበራቸውን ጉብኝት ከማጠቃለላቸው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከቆመ በኋላ ታይተዋል ያሏቸውን አዎንታዊ መሻሻሎች አድነቀው ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው በአዲስ አበባ መግለጫቸው ያነሷቸውን አበይት ነጥቦች በድጋሚ አስተጋብተዋል። “ውጊያ ቆሟል። የሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበ ነው። አገልግሎቶች ስራ እየጀመሩ ነው” ያሉት ብሊንከን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት “እጅጉን መቀነሱን” ተናግረዋል።

“የኤርትራ ወታደሮች እየወጡ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለሽግግር ፍትህ የመጀመሪያዎቹን እርምጃዎች እየወሰደ ይገኛል” ያሉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሆኖም የሚቀሩ ጉዳዮች መኖራቸውን አልሸሸጉም። “ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በሁሉም ወገኖች ለተፈጸሙ የጭካኔ ተግባራት እውቅና መስጠት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና እርቅ ማውረድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

“የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አውዳሚ ነበር። ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ተገድለዋል። ሴቶች እና ልጃገረዶች ለአሰቃቂ ወሲባዊ ጥቃቶች ተጋልጠዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። ማህበረሰቦች በሙሉ በብሔራቸው ምክንያት ኢላማ ሆነዋል” ያሉት ብሊንከን፤ ድርጊቶቹ “ታቅዶ” እና “ሆን ተብሎ” የተፈጸሙ መሆናቸውንም ገልጸዋል። “አብዛኞቹ እነዚህ እርምጃዎች የዘፈቀደ ድርጊቶች ወይም የጦርነት ውጤቶች አይደሉም” ሲሉም አክለዋል።

በፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች፤ በጦርነቱ ወቅት ለተፈጸሙ ግፎች እና ላስከተሏቸው መዘዞች “እውቅና መስጠታቸውን” ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበጎ እርምጃነት ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የሽግግር ፍትህ ስርዓት ለመጀመር እያደረገ የሚገኘውን ዝግጅት በአዎንታዊነት የጠቀሱት ብሊንከን፤ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ “ቁልፍ ጉዳይ” እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት እንዲሁም ህወሓት “እነዚህን ግፎች የፈጸሙትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ” ጥሪ አቅርበዋል። ለተፈጸሙት ግፎች እውቅና መስጠት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና እርቅ ማውረድ “ኢትዮጵያ ካልተገደበ አቅሟ እንዳትደርስ ለረዥም ጊዜ አግደው ያቆዩዋትን የብሔር እና የፖለቲካ ግጭት አዙሪት ለመስበር ቁልፍ ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢትዮጵያ “ለተጎጂዎች እና ተጽዕኖ ለደረሰባቸው ማኅበረሰቦች የሚጠቅም ተአማኒ የሽግግር ፍትሕ ሒደት” ስትዘረጋ አሜሪካ አጋር እንደምትሆንም ብሊንከን ቃል ገብተዋል። አገሪቱ “ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ በደሎችን ፊት ለፊት ስትጋፈጥ፣ በዜጎቿ ላይ ለተፈጸሙ ጉዳቶች ተጠያቂነትን ስታረጋግጥ እና ወደ ዘላቂ ሰላም ስትገሰግስ ከኢትዮጵያ ጋር እንቆማለን” ሲሉ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)