በአዲስ አበባ ካሉ ሹፌሮች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚያሽከረክሩ መሆናቸውን አንድ ጥናት አመለከተ  

በአማኑኤል ይልቃል

በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ አሽከርካሪዎች ውስጥ 59 በመቶው ከፍጥነት ወሰን በላይ እንደሚያሽከረክሩ አንድ ጥናት አመለከተ። ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር ባለፉት ዓመታት እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን ጥናቱን ያካሄዱት ባለሙያዎች ገልጸዋል።

ይህ የተገለጸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ደህንነት አደጋ መንስኤዎችን በተመለከተ የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ግኝት ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 12፤ 2015 ይፋ በተደረገበት መርሃ ግብር ላይ ነው። በተሽከርካሪ ፍጥነት፣ ጠጥቶ ማሽከርከር እንዲሁም የደህንነት ቀበቶ እና የራስ ቆብ (helmet) አጠቃቀም ላይ ትኩረት ያደረገው ይህ ጥናት፤ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱ ተገልጿል።

የአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር ባከናወነው በዚህ ጥናት ግኝት መሰረት፤ በ2010 ዓ.ም. 39 በመቶ የነበረው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መጠን ባለፈው ዓመት በ20 በመቶ ጨምሯል። ከአሽከርካሪዎች መካከል ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር ከፍተኛውን መጠን ያስመዘገቡት፤ የጭነት ወይም ከባድ መኪና ሹፌሮች ናቸው።

ከጭነት ወይም ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ውስጥ 80 በመቶ ገደማው፤ ከፍጥነት ወሰን በላይ እንደሚያሽከረክሩ በጥናቱ እንደተደረሰበት በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል። ከአውቶብስ አሽከርካሪዎች መካከል 70 በመቶ ገደማ ያህሉ ከተቀመጠው የፍጥነት ወሰን በላይ እንደሚነዱ ጥናቱ አመልክቷል። የአነስተኛ መኪና ሹፌሮች ከፍጥነት ወሰን በላይ የማሽከርከር መጠን፤ 50 በመቶ ገደማ መሆኑም በጥናቱ ተጠቅሷል። ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎች ቁጥር በእረፍት ቀናት በእጥፍ እንደሚጨምርም በጥናቱ ተደርሶበታል። 

ጥናቱን ካከናወኑት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዋጋሪ ደሬሳ፤ በአሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶ እና የራስ ቆብ አጠቃቀም ላይ የተገኘው የጥናት ውጤት “የተሻለ የሚባል” መሆኑን ተናግረዋል። የደህንነት ቀበቶ የመጠቀም ምጣኔ በአሽከርካሪዎች ዘንድ 99 በመቶ እንደደረሰ የጥናቱ ግኝት ማሳየቱን ፕሮፌሰር ዋጋሪ ገልጸዋል። ከሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ውስጥ 90 በመቶው የራስ ቆብ (helmet) እንደሚያደርጉም ዋና ተመራማሪው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)