የጋምቤላ ክልል የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር እና ምክትላቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ

በአማኑኤል ይልቃል

የጋምቤላ ክልል የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር እና ምክትላቸውን ጨምሮ 12 የጸጥታ ዘርፍ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ። የክልሉ መንግስት እነዚህን የጸጥታ አካላት እና ሲቪሎች በቁጥጥር ስር ያዋለው፤ “በዜጎች ላይ ያልተገባ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እና ግድያ ፈጽመዋል” በሚል ነው።

የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡባንግ እና በወቅቱ ምክትላቸው የነበሩት ቱት ኮር ለእስር የተዳረጉት፤ የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) እና የ“ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በጋምቤላ ከተማ የሰነዘሩትን ጥቃት ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎች “እጃቸው አለበት” በሚል ነው። ሁለቱ ታጣቂ ቡድኖች በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ባደረሱት በዚሁ ጥቃት፤ ቢያንስ ሰባት ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው መስከረም ላይ ባወጣው ሪፖርት አስታውቆ ነበር።

ኢሰመኮ በዚሁ ሪፖርቱ፤ ከጥቃቱ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ሁለት ቀናት፤ 50 ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ ይፋ አድርጓል። መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ ካደረገው ምርምራ በኋላ ባወጣው በዚሁ ሪፖርት፤ በሲቪል ሰዎች ላይ የተፈጸሙት ግድያዎች “በተናጠል እና በጅምላ”፣ “ከፍርድ ውጪ” የተደረጉ እንደነበር አጋልጧል። እነዚህን ግድያዎች “በዋናነት የፈጸሙት” የጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መሆናቸውን ከዓይን እማኞች ማረጋገጡንም ኮሚሽኑ በመስከረሙ ሪፖርት አስታውቆ ነበር። 

ይህንን የኢሰመኮ ሪፖርት ተከትሎ የጋምቤላ ክልል መንግስት መስከረም 22፤ 2015 ባወጣው መግለጫ፤ በሪፖርቱ የተጠቀሱ ወንጀላዎችን “መሰረት ቢስ” ሲል አጣጥሏል። የኮሚሽኑ ሪፖርት “ሚዛናዊነት እና ኃላፊነት የጎደለው”፣ “ለጠላት የወገነ” እና የጋምቤላ ህዝቦችን “ራሳቸውን የመጠበቅ ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የደፈረ” በመሆኑ፤ የክልሉ መንግስት “እንደማይቀበለው እና እንደሚያወግዘው” በዚሁ መግለጫው አመልክቷል።

የጋምቤላ ክልል መንግስት ይህን መግለጫ ካወጣ ከሁለት ቀናት በኋላ፤ በጋምቤላ ከተማ በሚገኘው የኢሰመኮ ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት መፈጸሙ ተነግሯል። በቡድን ሆነው በመጡ ሰዎች ተፈጸመ የተባለው ይህ ጥቃት፤ “በብሔራዊው የሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና ሰራተኞቹ ላይ ያነጣጠረ” መሆኑን ኢሰመኮ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ጥቃቱ በጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ “ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል” መሆኑን በመግለጫው የጠቀሰው ኮሚሽኑ፤ የክልሉ ጸጥታ አካላት ድርጊቱን “በአፋጣኝ ሊያስቆሙ እንደሚገባ” አሳስቦ ነበር።

ከዚህ ክስተት በኋላ ሻክሮ የቆየው የጋምቤላ ክልል እና የኢሰመኮ ግንኙነት፤ ጉልህ መሻሻል ያሳየው ባለፈው የካቲት መጨረሻ ላይ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ጋምቤላ ከተማ የተጓዘው የኢሰመኮ አመራሮች ልዑክ፤ የመስከረሙን ሪፖርት በተመለከተ ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጓል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ኡመድ ኡጅሉ በተገኙበት በዚሁ ውይይት፤ ከሰኔ 2014 ክስተት ጋር በተያያዘ በክልሉ በተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ሊኖረው የሚገባው ተጠያቂነት ተነስቶ ነበር ተብሏል።  

ይህ ውይይት ከተካሄደ ከሁለት ሳምንት በኋላ፤ በጋምቤላ ክልል “የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ኃላፊነት የነበራቸው” 13 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው ኢሰመኮ መረጃ እንደደረሰው የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ ስራ ክፍል ዳይሬክተር ታሪኳ ጌታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በጸጥታ ዘርፍ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ እና ከእነዚህ ውስጥም የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነር እንደሚገኙበት አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 15፤ 2015 በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡባንግ፤ በሰኔ ወር ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ ከዚህ ኃላፊነታቸው ተነስተው የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ነበር። በሰኔው ጥቃት የክልሉ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት ቱት ኮር፤ በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን በሌላ ኃላፊነት ላይ ተሹመው ነበር። 

ከፖሊስ ኮሚሽነሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ከዋሉት የጸጥታ አካላት ውስጥ ሶስቱ በኮሎኔል ደረጃ ላይ ያሉ ሲሆን፤ አምስቱ ሌተናል ኮሎኔል ደረጃ ያላቸው መሆናቸውን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ዋና ኢንስፔክተር እና ረዳት ኢንስፔክተር ደረጃ ያላቸው የጸጥታ አባላትም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ ይገኙበታል። የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባለፈው አርብ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉትን 13 ግለሰቦች “የጸጥታ አካላት አመራሮች እና ሲቪሎች ናቸው” ብሎ ነበር።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር | ፎቶ፦ የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ጽህፈት ቤቱ የጠቀሳቸው የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰናይ አኩዎር፤ የጸጥታ አካላቱ በቁጥጥር ስር የዋሉት “በዜጎች ላይ ያልተገባ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እና ግድያ ፈጽመዋል” በሚል እንደሆነ አስታውቀዋል። የቀድሞው የፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የጸጥታ አባላቱ፤ እነዚህን እርምጃዎች የወሰዱት በሰኔ ወር ታጣቂ ቡድኖቹ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ “የህግ ማስከበር ስራ ሲያከናውኑ በነበረበት ወቅት ነው” ብለዋል። የፖሊስ ኮሚሽነሩ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩባቸው ጉዳዮች የተለያየዩ መሆናቸውን አንስተዋል። 

የፖሊስ አመራሮቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት “የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው” መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ሰናይ፤ ሌሎቹ የጸጥታ ዘርፍ አካላት እና ሲቪሎቹ ደግሞ “ድርጊቱን ፈጽመዋል” በሚል መጠርጠራቸውን አብራርተዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉትን እነዚህን የጋምቤላ ጸጥታ መዋቅር አባላት የእስር ሁኔታን በተመለከተ፤ ኢሰመኮ “ክትትል እንደሚያደርግ” የኮሚሽኑ የሕግና ፖሊሲ ስራ ክፍል ዳይሬክተር  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነሮች እና የጸጥታ አባላትን በቁጥጥር ስር መዋል በተመለከተ፤ ከክልሉ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)