የ“ሸኔ” ታጣቂ ቡድንን በተመለከተ፤ “የተለያዩ ሃሳቦችን ለመንግስት የሚያቀርብ” ቡድን መቋቋሙ ተነገረ 

⚫ “በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ላይ ተጀምሮ ውጤት ያስመዘገበው የሰላም አካሄድ፤ ለማንም የተነፈገ አይደለም” – በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ

 በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድን በተመለከተ፤ “የተለያዩ ሃሳቦችን ለመንግስት የሚያቀርብ” ቡድን መቋቋሙን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ተናገሩ። የፌደራል መንግስት የ“ሸኔ” ታጣቂ ቡድንን በተመለከተ ከያዛቸው ሶስት  አማራጮች መካከል፤ “ችግሮችን በንግግር መፍታት” የሚለው አንዱ መሆኑን በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው ገልጸዋል። 

አቶ ተስፋዬ ይህን የገለጹት፤ የፓርላማ አባላት ከአስፈጻሚ አካላት አመራሮች ጋር ዛሬ ሰኞ መጋቢት 18፤ 2015 ባደረጉት ውይይት ላይ በሰጡት ማብራሪያ ነው። የዛሬው ውይይት የተዘጋጀው፤ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባለፈው አንድ ወር የእረፍት ጊዜያቸው ወቅት ወደ ምርጫ ክልሎቻቸው ተጉዘው ባሰባሰቧቸው ጥያቄዎች ላይ ለመምከር ነበር።

በተወካዮች ምክር ቤት ረዳት የመንግስት ተጠሪ የሆኑት ወይዘሮ መሰረት ኃይሌ፤ የፓርላማ አባላቱ በ347 መድረኮች ከመራጮቻቸው ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል። ወይዘሮ መሰረት፤ መራጩ ህዝብ በእነዚህ መድረኮች አንስቷቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች፤ “በሰላም እና ጸጥታ፣ ኢኮኖሚ፣ መሰረተ ልማት እና ፕሮጀክቶች፣ ማህበራዊ እና መልካም አስተዳደር” በሚሉ ዘርፎች ከፋፍለው በሪፖርት መልክ አቅርበዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በዚሁ ሪፖርት ቅድሚያ የተሰጠው፤ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳይ ነው። “ዲግሪው ይለያያል እንጂ፤ ሰላም እና ጸጥታ ያልተነሳበት የምርጫ ቦታ የለም” ሲሉ ጉዳዩ በህዝቡ ዘንድ ያገኘውን ከፍተኛ ትኩረት ረዳት የመንግስት ተጠሪዋ አስረድተዋል። የፓርላማ አባላቱ ከመራጮቻቸው ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፤ “የዜጎች ከቦታ ቦታ በነጻነት የመዘዋወር ሕገ መንግስታዊ መብታቸው እየተጠበቀ አይደለም” የሚል ጥያቄ መነሳቱንም ገልጸዋል።

በእነዚሁ ውይይቶች፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ የጸጥታ ችግሮችን በሰላም መፍታትን የተመለከቱ ጥያቄዎች መቅረባቸውን ወይዘሮ መሰረት በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። “በሰሜን የተከሰተውን ግጭት በሰላም እንደተፈታ ሁሉ፤ ከሌሎች ኃይሎችም ጋር ለምንድነው በሰላም እንዲፈታ ጥረት የማይደረገው?” የሚል ጥያቄ በውይይቶቹ ላይ መቅረቡንም አመልክተዋል።

ግጭቶችን በንግግር የመፍታት ጉዳይ ይበልጥኑ “በርከት ብሎ” የተነሳው በኦሮሚያ ክልል መሆኑን በተወካዮች ምክር ቤት የክልሉ ተመራጮች አስተባባሪ አቶ ብዙአየሁ ደገፋ በዛሬው ስብሰባ ላይ ጠቅሰዋል። አቶ ብዙአየሁ “ህዝቡ ያተኮረው መፍትሔው ላይ” መሆኑን ተናግረዋል። “ኦሮሚያ ውስጥ ያለው ችግር ትግራይ ውስጥ ከነበረው ችግር በታች አይደለም” ያሉት የክልሉ ተመራጮች አስተባባሪ፤ “ስለዚህ ይሄ መፍትሔ ይፈልጋል፤ እርቅ ይፈልጋል” ሲሉ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን ስሜት አንጸባርቀዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በኦሮሚያ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት፤ የህዝብ ውይይት ያላደረጉ የፓርላማ ተመራጮች መኖራቸውን አቶ ብዙአየሁ ገልጸዋል። “በሁለት አመት ውስጥ ምንም ከህዝብ ጋር ያልተገናኘን አለን። እስካሁን ህዝባችን እየተሰቃየ ነው” ያሉት የኦሮሚያ ክልል የፓርላማ ተመራጮች አስተባባሪው፤   “ምክር ቤቱም፣ አስፈጻሚ አካላትም፣ እዚህ ያላችሁ የኦሮሚያ ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል” ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የተመረጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሰውን “ታጣቂ ኃይል” እና መንግስትን የአፍሪካ ህብረት እንዲያደራድር ባለፈው ሳምንት ይፋዊ ጥያቄ አቅርበው ነበር። የፓርላማ አባላቱ ጥያቄውን ያቀረቡት፤ መጋቢት 11፤ 2015 ለአፍሪካ ህብረት ባስገቡት ደብዳቤ ነው። በዛሬው የፓርላማ የምክክር መድረክ ላይ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎች ሰጥተዋል።  

“ሸኔን በተመለከተ፤ ሀገራዊ የሆነ፣ ይሄንን ስራ የሚከታተል፣ ከዚህ ተግዳሮት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሃሳቦችን ለመንግስት የሚያቀርብ፤ በፌደራል መንግስትም፣ በመሪው ፓርቲም የተቋቋመ አንድ ሀገራዊ ቡድን አለ። ይሄ ቡድን ስራውን ጀምሯል። በጣም የተደራጀ ስራ እየተሰራ ነው ያለው” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል። ቡድኑ ዝርዝር ሪፖርቱን “ሌላ ጊዜ” ለፓርላማው እንደሚያቀርብም የመንግስት ተጠሪው አክለዋል። 

“ሁለተኛ በየአካባቢው ህብረተሰቡን በኃይል በማንበርከክ፤ መንግስትን፣ ሀገርን በኃይል በማንበርከክ፤ አላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት ይሄ እንደማይቻል ጸጥታ ኃይሉ ተሰማርቶ ስራ እየሰራ ነው ያለው። በሶስተኛ ደረጃ፤ ከሁሉም በላይ ‘ከማንም ጋር፣ ከሰላም አኳያ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ችግር መፍታት አለብን’ የሚል ጥሪ ለሁሉም አካል ቀርቧል”

አቶ ተስፋዬ በልጅጌ – በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ

በፌደራል መንግስት እና በገዢው ብልጽግና ፓርቲ እንደተቋቋመ ከተነገረው ከዚህ ቡድን “የተደራጀ ስራ” በተጨማሪ፤ በመንግስት በኩል ሶስት አማራጮች መያዛቸውን አቶ ተስፋዬ ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል። “በአንድ በኩል ህዝቡን በማስተባበር እና ወደ ዘላቂ ሰላም ለመግባት የተጀመረ ስራ አለ። ሁለተኛ በየአካባቢው ህብረተሰቡን በኃይል በማንበርከክ፤ መንግስትን፣ ሀገርን በኃይል በማንበርከክ፤ አላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ አካላት ይሄ እንደማይቻል ጸጥታ ኃይሉ ተሰማርቶ ስራ እየሰራ ነው ያለው። በሶስተኛ ደረጃ፤ ከሁሉም በላይ ‘ከማንም ጋር፣ ከሰላም አኳያ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ችግር መፍታት አለብን’ የሚል ጥሪ ለሁሉም አካል ቀርቧል” ሲሉ ሶስቱን አማራጮች የመንግስት ተጠሪው ዘርዝረዋል። 

አቶ ተስፋዬ በዚሁ ማብራሪያቸው “በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ላይ ተጀምሮ ውጤት ያስመዘገበው የሰላም አካሄድ ለማንም የተነፈገ አይደለም። ለሁሉም የቀረበ ነው”  ብለዋል። የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር ካደረገው  የሰላም ስምምነት በኋላ “ኢትዮጵያ ከጦርነት ድባብ እየወጣች ነው” ሲሉም ተደምጠዋል። 

አምስት ሰዓታት ገደማ በወሰደው በዛሬው የፓርላማ የምክክር መድረክ፤ ከሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች በተጨማሪ በመሰረተ ልማት፣ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝብ ተነሱ የተባሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል። ለእነዚህ ጥያቄዎች ሚኒስትሮች እና ሌሎች የአስፈጻሚ አካላት ኃላፊዎች ምላሽ እና ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። በዛሬው የውይይት መድረክ ላይ ከተገኙ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች መካከል፤ የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ይጠቀሳሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)