በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ሳይባባስ፤ ፓርላማው የሰላማዊ መፍትሔ አስፈላጊነትን ለመንግስት “በአስቸኳይ እንዲያሳስብ” ኢሰመኮ ጠየቀ  

በሃሚድ አወል

በአማራ ክልል እየተደረገ ባለው “የጸጥታ እርምጃ” የተፈጠረው ጉዳት ሳይባባስ፤ ፓርላማው የሰላማዊ መፍትሔ አስፈላጊነትን ለመንግስት የስራ አስፈጻሚ አካል “በአስቸኳይ እንዲያሳስብ” የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጥያቄ አቀረበ። ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ በተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት “የተዓማኒነት እና የአካታችነት” ጥያቄም ተነስቶበታል። 

ጥያቄው የተነሳው ኢሰመኮ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፤ ለፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነው። በኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አማካኝነት የቀረበው ሪፖርት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበሩ አዎንታዊ እርምጃዎች እና አሳሳቢ ሆነው የቀጠሉ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነበር። 

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በደቡብ አፍሪካ የተደረገው የሰላም ስምምነት፤ ኮሚሽነሩ በአዎንታዊ እርምጃነት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች በቀዳሚነት የተነሳ ነው። የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ በመንግስት በኩል የተጀመረውን ሂደትም “አበረታች እርምጃ” ሲሉ ገልጸውታል። 

ኮሚሽኑ የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በጣምራ ባደረገው ምርመራ፤ “ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ጽንሰ ሃሳብን ተግባራዊ ልታደርግ ይገባል” የሚል ምክረ ሃሳብ መቅረቡን ዶ/ር ዳንኤል አስታውሰዋል። ይህን ተከትሎ “በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጠያቂነትን የማረጋገጥ አበረታች እርምጃዎችን አይተናል” ሲሉም ተናግረዋል። 

ዶ/ር ዳንኤል በዛሬው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ማብራሪያ የሰጡት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ “አሳሳቢነታቸው የቀጠሉ” ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ነው። በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን “ወታደራዊ እንቅስቃሴ” በአሳሳቢነት ያነሱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ይህ ወታደራዊ እርምጃ የሰብዓዊ መብት አንድምታ ስላለው በቅርበት እየተከታተልነው ነው” ብለዋል። 

መንግስት በአማራ ክልል በማካሄድ ላይ ባለው “የጸጥታ እርምጃ” “በሲቪል ሰዎች ላይ የሞትም፣ የንብረት ውደመትም፣ የመፈናቀልም ጉዳት ደርሷል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ “እስካሁን ባለው መረጃም በመነሳት ከሰብዓዊ መብት አንጻር በጣም የሚያሰጋ” መሆኑን ገልጸዋል። “ጉዳዩ ከዚህ የበለጠ ሳይባባስ ፓርላማው የመንግስት አስፈጻሚ አካሉን፤ የውይይቶችን እና የሰላማዊ መፍትሔ አስፈላጊነትን አበክሮ በአስቸኳይ እንዲያሳሳብ” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ዶ/ር ዳንኤል በአሳሳቢነት ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ “በጋዜጠኞች፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በተቃውሞ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ” ነው ያሉትን “ጥቃት” የተመለከተ ነው። ጉዳዩ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መምጣቱን” ዋና ኮሚሽነሩ ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገልጸዋል። “አስፈጻሚው አካል ‘በጋዜጠኝነታቸው ወይም በሚዲያ ስራቸው አይደለም ለጥቃት የተጋለጡት’ ብሎ አበክሮ ይከራከራል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ ሆኖም መከራከሪያውን “ብዙም አሳማኝ ሆኖ አላገኘነውም” ብለዋል። 

“በታሰሩበት ጊዜ ሁሉ፤ እንደተፈጸመው ወንጀል ማስረጃ ተደርጎ ሲጠቀስ የምናየው [እና] የምናደምጠው፤ በሚሰሩበት ሚዲያ ተቋም አማካኝነት ጽፈዋል ወይም ተናግረዋል የተባሉት ነገር ነው” ሲሉ በመንግስት አካል የሚቀርበው መከራከሪያ አሳማኝ ያልሆነበትን ምክንያት አስረድተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት የወጣውን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ በመጥቀስም፤ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ተፈጸመ ለተባለ ወንጀል የቅድመ ክስ እስር መደረግ እንዳልነበረበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰት “የዘፈቀደ እስር እና በእስር ወቅት የሚፈጸም ተገቢ ያልሆነ አያያዝ”፤ በኢሰመኮ ሪፖርት ላይ “አሳሳቢ” በሚል የተነሳ ሌላኛው ጉዳይ ነው። ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ “የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦችም” እንዲሁ በአሳሳቢነት ተነስተዋል። ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት በሚፈልጉ ሰዎች ላይ የተከሰቱ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ዋና ኮሚሽነሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ዶ/ር ዳንኤል የሚመሩትን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፤ ከፓርላማው የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከሌሎች የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል፤ ከኮሚሽኑ “ተዓማኒነት እና አካታችነት” ጋር በተያያዘ የተነሳው ይገኝበታል። 

አቶ ከድር እንድሪስ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል “ ‘[ኮሚሽኑ] የሚያወጣቸው ዘገባዎች ምን ያህል ተዓማኒ ናቸው?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል መብራራት አለበት” ብለዋል። “የተወሰነ የማህበረሰብ ክፍል ላይ ትኩረት አድርጎ ነው ብዙ ስራዎችን የሚሰራው በሚል ተቋሙ ላይ የሚነሳ ቅሬታ አለ” ሲሉም አክለዋል። ከደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ ከድር፤ ኢሰመኮ በዕቅድ የሚመራ ተቋም መሆኑ ላይም ጥያቄ አንስተዋል።   

ኮሚሽኑ “ሚዲያን ይከተላል ይባላል” ያሉት አቶ ከድር፤ “እነዚያ ላይ ትኩረት አድርጎ እንጂ የራሱ ዕቅድ ኖሮት በራሱ ጊዜ የሚንቀሳቀስ ተቋም አይደለም” በሚል የሚነሳው ቅሬታ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። ኢሰመኮ “የሚመለከተው አካል ባላረጋገጠው ጉዳይ ላይ ‘እከሌ ነው አጥፊው’ የሚል ፍረጃ ለመስጠት ይቸኩላል ይባላል። ማብራሪያ ቢሰጥበት” ሲሉም ተጨማሪ ጥያቄ አቅርበዋል።

ሌላኛዋ የቋሚ ኮሚቴው አባል ሙሉነሽ ላሞሬ በበኩላቸው የኮሚሽኑ ሪፖርት “የሁሉንም አካባቢ ከማዳረስ” እና “አስፍቶ ከመመልከት አንጻር”  በየቦታው ያሉትን “የዜጎችን መብት ጥያቄዎች” ሊያካትት እንደሚገባ ተናግረዋል። የፓርላማ አባሏ ለዚህ አስተያየታቸው በምሳሌነት ያነሱት “የመኖሪያ ቤቶች በኃይል ማፍረስን እና ነዋሪዎችን ማፈናቀልን” በተመለከተ በዋና ኮሚሽነሩ የቀረበውን ገለጻ ነው። “ቤቶች መፍረስ ላይ ሪፖርቱ over all ትኩረት ያደረገው አዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ላይ ነው” ያሉት ሙሉነሽ፤ እርሳቸው ከመጡበት ሆሳዕና አካባቢ “መንገድ ለማስፋት እና ወደ ትክክለኛው ካርታ ለማስገባት ትላልቅ ህንጻዎች የሚፈርሱበት ሂደት” እንዳለ አስረድተዋል። 

የፓርላማ አባሏ በኢሰመኮ የሚወጡ መግለጫዎችን በተመለከተም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከኮሚሽኑ የሚወጡ መግለጫዎችን ሚዲያዎች በሚያሰራጩበት ወቅት፤ “ፋክቱ የቱ ጋር ነው? ጠቀሜታው የቱ ጋር ነው? የሚለውን ነገር ተንተርሰው ሳያዩ፣ መግለጫውን ይወስዱና በጣም circulate ተደርጎ፣ ህዝብ እንዲረበሽ፣ በህዝብ እና በመንግስት መካከል፣ በህዝቦች እና ህዝቦች መካከል ተግባቦት እንዳይኖር” የሚያደርጉ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ረገድ “ከሚመለከታቸው አካላት” ጋር ያለው “መናበብ” እና “መግለጫዎች ሳይወጡ በፊት ከመንግስት ስራ አስፈጻሚ ጋር በደንብ መነጋገሩ ላይ” ያለው አካሄድ ምን እንደሚመስል ማብራሪያ ጠይቀዋል። 

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ዳንኤል “ስለተዓማኒነታችን፣ ‘የተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል አገልግላችኋል’ በሚል የተለያዩ አይነት ትችቶች እና አስተያየቶች እንደሚሰጡን እናውቃለን” ብለዋል። “የተሰጠ አስተያየት እና የተባለ ነገር በሙሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ይህን ለህሊና ፍርድ ለእናንተ እተዋለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።

ከፍረጃ ጋር በተያያዘ በተቋማቸው ላይ ለተነሳው ጥያቄ ዶ/ር ዳንኤል ሲመልሱ “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ተቋም፤ ሳያጣራ የሚፈርጅ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። “ለማጣራት ከምንወስደው ጊዜ የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ‘ለምን ቶሎ አልተናገራችሁም?’ የሚል ቅሬታ ነው የሚቀርብብን” ሲሉ ተቋማቸው ላይ የሚቀርበው ቅሬታ በፓርላማ አባሉ ከተነሳው ትችት በተቃራኒ መሆኑን ገልጸዋል።

“ሚዲያ ይከተላሉ የሚለው አስተያየት ትክክል አይመስለኝም” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ “ነገር ግን የምንዘግባቸው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች አብዛኛውን ጊዜ የሚዲያ ትኩረት የሚስቡ መሆናቸው አይካድም” ብለዋል። “አንድም ሪፖርታችን ላይ ‘ይሄ ድምዳሜያችሁ ስህተት ነው’ ተብሎ ክርክር ሊቀርብበት የቻለ የለም” ሲሉም ዋና ኮሚሽነሩ በተቋማቸው ላይ ለተነሳው ቅሬታ እና ትችት በአጽንኦት ምላሽ ሰጥተዋል። 

ከመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካል ጋር መነጋገርን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም ዋና ኮሚሽነሩ ምላሻቸውን አስደምጠዋል። “እኛ ነጻ ብሔራዊ የሰብዓዊ  ተቋም ነን። ከመንግስት የስራ አስፈጻሚ ተጽዕኖ ወይም አቅጣጫ ነጻ ሆነን መስራት አለብን። ከመንግስት ጋር ለመስማማት ለመናበብ፣ አንድ አይነት አቋም ለመያዝ ብለን ግን አንሰራም” ብለዋል ዶ/ር ዳንኤል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[ከአዘጋጁ፦ በዚህ ዘገባ የተጠቀሱት ሙሉነሽ ላሞሬ የተባሉ የፓርላማ አባል ያቀረቧቸው አስተያየቶች ላይ መጠነኛ ማስተካከያ መደረጉን ለመግለጽ እንወዳለን]