በተስፋለም ወልደየስ
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በሎስ አንጀለስ ከሚገኙ የኢትዮ-አሜሪካ ማህበረሰብ አባላት ጋር ሊነጋገሩ ነው። ልዩ ልዑኩ በሎስ አንጀለስ ቆይታቸው፤ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ እና የትግራይ ማህብረሰብ ተወካዮችን እንደሚያነጋግሩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ማይክ ሐመር ከዛሬ ጀምሮ ለዘጠኝ ቀናት በሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ በሚያደርጉት ቆይታ፤ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ ያደረገውን የደቡብ አፍሪካ የግጭት ማቆም ስምምነትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዮች እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ገልጿል። የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ ከአሜሪካ ኢትዮጵያውያን ጋር በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚያደርጉት ውይይት፤ “ሰላምን በማስፈን እና የሴቶችን አቅም በማጎልበት” የሚያተኩር ነው ተብሏል።
“ዩናይትድ ውመን ኦፍ ዘ ሆርን” በተባለ የሲቪክ ድርጅት የተዘጋጀው ይህ ውይይት የሚካሄደው፤ 500 የሚጠጉ ሰዎችን ማስተናገድ በሚችለው በቦብ ሆፕ ፓትሪዮቲክ አዳራሽ ነው። የውይይቱ አዘጋጅ የሆነው ድርጅት፤ በምስራቅ አፍሪካ የዳያስፖራ ሴቶች ጥምረት የተቋቋመ መሆኑን በድረ-ገጹ አስፍሯል። ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና የተባበረ የአፍሪካ ቀንድ እንዲኖር ስራዎችን የማከናወን ዓላማ እንዳለው የሚገልጸው ይህ ድርጅት፤ ኢትዮጵያን የተመለከተ ውይይት ሲያዘጋጅ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም።
በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ግንባታ ላይ ሴቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ባዘጋጀው ውይይት ላይ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን በመጋበዝ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ አድርጓል። በወቅቱ በኬንያ ናይሮቢ ይገኙ የነበሩት ማይክ ሐመር በዚህ ውይይት ላይ በመሳተፍ፤ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን እያደረገች ስላለችው ጥረት እና ስለ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ገለጻ አድርገው ነበር።
አምባሳደር ሐመር በአሁኑ የሎስ አንጀለስ ቆይታቸው፤ ከከተማይቱ ከንቲባ ካረን ባስ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል። የኮንግረስ አባል በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያራምዷቸው ጠንካራ አቋማቸው ይታወቁ የነበሩት ካረን ባስ፤ የመጀመሪያዋ የሎስ አንጀለስ ሴት ከንቲባ ሆነው የተመረጡት ባለፈው ህዳር ወር ላይ ነበር።
በአሜሪካ ኮንግረስ የአፍሪካን ጉዳይ የሚመለከተውን ንዑስ ኮሚቴ በሊቀመንበርነት ይመሩ የነበሩት ባስ በሐምሌ 2013 ከኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት፤ “የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካ ጦሯን ለምን እንደማትልክ” ጥያቄ እንደቀረበላቸው መናገራቸውን ተከትሎ በወቅቱ መነጋገሪያ ሆነው ነበር። አሜሪካ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ መላኳን “ማየት እንደማይፈልጉ” እና “ተገቢ ነው” ብለው እንደማያምኑ መግለጻቸውም ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዳስገኘላቸው ይታወሳል።
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ድርድር እንዲፈታ ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው አምባሳደር ማይክ ሐመር፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ነበሩ። የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሆነው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ከተሾሙ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ የተመላለሱት ሐመር፤ በሚያዝያ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ማይክ ሐመር የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በተዘጋጀ የሽልማት እና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እጅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ከሽልማቱ ስነ ስርዓት በኋላ ወደ መቐለ በመጓዝም፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑት ጌታቸው ረዳ እና ምክትላቸው ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)