የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው ላይ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቀደ 

በሃሚድ አወል

በጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና ቴዎድሮስ አስፋው ላይ ለሁለተኛ ጊዜ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት በፍርድ ቤት ተፈቀደ። የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው ዛሬ አርብ ግንቦት 4፤ 2015 የዋለው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ የ“አራት ኪሎ ሚዲያ” የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና “ኢትዮ ሰላም” የተሰኘው የዩ ቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች ቴዎድሮስ አስፋውን ጉዳይ መመልከት የጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው። ባለፈው ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ሲታይ የነበረው፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነበር።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመጀመሪያ የችሎት ውሎው ለፖሊስ አስር የምርመራ ቀናት ከፈቀደ በኋላ፤ በሁለተኛው ቀጠሮ ለእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎጭ የ20 ሺህ ብር ዋስትና መፍቀዱ ይታወሳል። በችሎቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው ፖሊስ፤ በማግስቱ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ሆኖም አቤቱታው የቀረበለት ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማጽናት የተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲጠበቅ ወስኗል። 

ፖሊስ ይግባኙ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ዳዊት እና ቴዎድሮስን “በሽብር ፈጠራ” ወንጀል እንደጠረጠራቸው በመግለጽ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፊት አቅርቧቸዋል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል፤ “በህዝብ የተመረጠን መንግስት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ” በመንቀሳቀስ የሚል ነበር። 

የፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኛ ዳዊትን እና ቴዎድሮስን ሌላ ወንጀል በመጥቀስ ፍርድ ቤት ባቀረበበት የችሎት ውሎ ደግሞ፤ ተጠርጣሪዎቹ “ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መሆናቸውን በምርመራ መነሻ መረጃዎቻችን ተረጋግጧል” ብሏል። ሚያዝያ 20፤2015 በተካሄደው በዚሁ ችሎት፤ ፖሊስ 14 የምርመራ ቀናትን እንዲፈቅድለት መጠየቁ እና ፍርድ ቤቱም ይህንኑ መቀበሉ አይዘነጋም።

ይኸው ችሎት ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ ፖሊስ ባለፈው ቀጠሮ በተፈቀዱለት 14 የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ነበር። የፌደራል ፖሊስ በዛሬው ዕለት ለችሎቱ በጽሁፍ ባቀረበው ሁለት ገጽ ማመልከቻ፤ ያከናወናቸውን እና የሚቀሩትን ስራዎች ዘርዝሯል። ፖሊስ ባለፉት ቀናት ተሰሩ በሚል ከዘረዘራቸው ሰባት ተግባራት መካከል በቀዳሚነት የጠቀሰው፤ የምርመራ ቡድን በማቋቋም “በተለያዩ ቦታዎች ጉዳት የደረሰባቸውን [ግለሰቦች] የምስክርነት ቃል እንዲቀበል” መላኩን ነው።

የተጠርጣሪዎቹን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለማረጋገጥ ባንኮች ማስረጃ እንዲሰጡ በፖሊስ በኩል ቀረበ የተባለው ጥያቄም እንደዚሁ በፖሊስ ማመልከቻ ተጠቅሷል። በዚህ ጥያቄ መሰረትም፤ ፖሊስ በስም ካልተጠቀሱ አስር ባንኮች ማስረጃ ማስመጣቱን በማመልከቻው ጠቁሟል። ከተጠርጣሪዎች እጅ የተያዙ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን “እንዲመረመር የመላክ ስራ” እና የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ ለፎረንሲክ ምርመራ መላክ፤ በፖሊስ ተሰሩ የተባሉ ሌሎች ተግባራት ናቸው።  

“ከሚመለከተው ተቋማት የተጠየቁትን ማስረጃዎች በከፊል የማስመጣት ስራ ተሰርቷል” ያለው ፖሊስ፤ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበል እንዲሁም የቤት እና የስራ ቦታ ብርበራ መከናወኑን በማመልከቻቸው አስረድቷል። ፖሊስ “ግብረ አበሮችን የመያዝ ስራ” ማከናወኑንም ለችሎት በጹሁፍ ባቀረበው ማመልከቻ ላይ አስፍሯል። ፖሊስ በዚሁ ማመልከቻው፤ ምርመራውን ለማጠናቀቅ “ይቀሩኛል” ያላቸውን ሰባት ስራዎችን ዘርዝሯል። 

የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ ከባንኮች ቀሪ ማስረጃዎችን ማምጣት እና “የሽብር ወንጀሉን የፋይናንስ ምንጭ ማወቅ” ፖሊስ በቀጣይነት የሚያከናውናቸው ስራዎች መሆናቸው በማመልከቻቸው ተጠቅሷል። ፖሊስ የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን በማስመጣት፤ “የምርመራ ስራዎችን አስፍቶ መስራት” እና “ከሚመለከታቸው ተቋማት” የሰነድ ማስረጃዎችን ማስመጣት እንደሚቀሩትም ለችሎቱ በጹሁፍ አስረድቷል። 

ከዚህ በተጨማሪም ወንጀሉ ወደ ተፈጸመበት አካባቢ የሄደው የፖሊስ ምርመራ ቡድን፤ “በደረሰው የንብረት፣ የሰው ሞትና አካል ጉዳት ላይ የተጎጂዎችን የምስክርነት ቃል መቀበል” እንደሚቀረው በጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ማመልከቻ ላይ ተቀምጧል። “በተደረገው ህዝባዊ የአመጽ ቅስቀሳ” የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ፤ ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልሉ ተቋማት የሰነድ ማስረጃቸውን ማስመጣትም በቀጣይነት የሚያከናወነው ስራ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል። ያልተያዙ የተጠርጣሪዎቹን “ግብረ አበሮች በቁጥጥር ስር መዋል” የሚለው እንዲሁ በፖሊስ የቀሪ ስራዎች ዝርዝር ተካትቷል።  

የፌደራል ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት “የሽብር ወንጀል ድርጊት” “ውስብስብ እና ሀገርን የሚያፈርስ” መሆኑን በማንሳት፤ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት ችሎቱን ጠይቋል። ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ “ከሀገር ሊሸሹ እና ውጭ ሀገር ሆነው የሽብር ድርጊቱን ለማስፈጸም የሚችሉ” መሆናቸውን በመገልጽ ዋስትና እንዳይፈቀድም ጠይቋል። መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ማከናወኑን የገለጻቸው እና “ይቀሩኛል” ያላቸው ተግባራት የተቹት የተጠርጣሪ ጠበቆች፤ በፖሊስ የቀረቡት ምክንያቶች ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት በቂ ምክንያት አለመሆናቸውን በማንሳት ዋስትና ጥያቄ አቅርበዋል። 

ከተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ቤተማርያም አለማየሁ፤ “ምርመራው ምንም አይነት እድገት እያሳየ አይደለም” ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። “ከመጀመሪያው ቀን፣ እዚህ ችሎት ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ ጥቅል ነገር ነው በፖሊስ በኩል እየቀረበ ያለው” ያሉት ጠበቃው፤ “እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች ምን አደረጉ የሚለው ተለይቶ አልቀረበም። ምርመራው ድርሻን በለየ መልኩ እየተደረገ አይደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ፖሊስ ምርመራውን እያከናወነ ያለው “ትጋትን በሚጠይቅ መልኩ አይደለም” ሲሉም ተችተዋል። 

ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝም በተመሳሳይ፤ “የምርመራ መዝገቡ ትንሽም ቢሆን እድገት አላሳየም” ሲሉ ከባልደረባቸው ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል። ጠበቃ ሰለሞን አክለውም፤ “ግብረ አበር መያዝ ነበረባቸው አንድም አልያዙም” ብለዋል። ተጠርጣሪዎቹን ከሚወክሉት ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ አበበ መስፍን፤ “ተጠርጣሪዎቹን በእስር ለማቆየት ካልሆነ በስተቀር የሚሰራ ስራ ስላለ አይደለም ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቀው” ሲሉ ለችሎቱ ተናግረዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ በዋስትና ቢወጡ “ከአገር ሊሸሹ ይችላሉ” በሚል ፖሊስ ያቀረበውን መከራከሪያ፤ እኚሁ ጠበቃ “በቂ ምክንያት አይደለም፣ በማስረጃም አልተደገፈም” ሲሉ ነቅፈዋል። “ፖሊስ ከአሁን በኋላ ተጨማሪ ቀን ሊፈቀድለት አይገባም። አሳማኝ ምክንያትም እያቀረበ አይደለም” ያሉት አቶ አበበ፤ የተጠርጣሪዎች የዋስትና መበት እንዲጠበቅ ጠይቀዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ሰለሞንም “ቀሪ ስራዎች ማስረጃ ማምጣት ናቸው። ከመንግስት የሚመጡ ማስረጃዎችን [ተጠርጣሪዎቹ] ቢወጡ ጣልቃ ገብተው ሊያሰናክሉ አይችሉም” ሲሉ ተመሳሳይ የዋስትና ጥያቄ ለችሎቱ አቅርበዋል።

የፌደራል ፖሊስን ወክለው ችሎት የተገኙት ሁለት መርማሪ ፖሊሶች በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል። በቅድሚያ የመናገር ዕድል የተሰጣቸው መርማሪ ፖሊስ፤ በጠበቆች በኩል የምርመራውን ሂደት በተመለከተ ለተነሳው መከራከሪያ “የምርመራ መዝገቡ እዚህ ስላለ እድገቱን ማየት ይቻላል” ሲሉ የመልስ መልስ ሰጥተዋል። 

ከግብረ አበሮች መያዝ ጋር በተያያዘ ለተነሳውም አስተያየት፤ “የተያዘ ሰው አለ። የተያዘ ሰው እዚህ አይገለጽም። የሚቀረን ግብረ አበር አለ” ብለዋል። የተጠርጣሪዎች የወንጀል ተሳትፎን በተመለከተም፤ ፖሊስ ሁለተኛ ተጠርጣሪ የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት ያደረጋቸውን የስልክ ልውውጦች ማስረጃ ማግኘቱን መርማሪው ገልጸዋል። አቶ ዳዊት “በአማራ ክልል የነበረውን አመጽ በስልክ ሲመሩ ነበር” ሲሉም ጋዜጠኛውን ወንጅለዋል። 

ሌላኛው መርማሪ ፖሊስ በበኩላቸው ተጠርጣሪዎቹ ዋስትና ቢፈቀድላቸው “ተመሳሳይ ድርጊት ላይ ተሳትፎ ሊያደርጉ የሚችሉበት አጋጣሚ እና ሰፊ ዕድል ስላላለቸው የዋስትና ጥያቄው ውድቅ ቢደረግ” ሲሉ ዋስትናውን ተቃውመዋል። ፖሊስ በጽሁፍ ያቀረበው ማመልከቻም ይኼንኑ የመርማሪ ፖሊሱን አስተያየት የሚያስተጋባ ሃሳብ አስፍሯል። ማመልከቻው ተጠርጣዎቹ ዋስትና ቢፈቀድላቸው “የሚፈለጉ በህቡዕ የተደራጁ የቡድናቸውን መረብ በስውር በመምራት፣ የተጀመረውን የሽብር ድርጊት ለማስቀጠል የሚችሉ እና ሌሎች ማስረጃዎችን በማሸሽ” የተጀመረውን  ምርመራ “ሊያደናቅፉ” የሚችሉ መሆናቸውን ገልጿል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል። ትዕዛዙን ያነቡበት ዳኛ “ችሎቱ ምርመራው ስፋት ያለው መሆኑ ተረድቷል” ሲሉ ለፖሊስ ከተፈቀደው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጀርባ ያለውን አመክንዮ አስረድተዋል። ዳዊት እና ቴዎድሮስ በፖሊስ በተጠረጠሩበት ወንጀል ተሳታፊ መሆናቸውን “አመላካች የሆነ በቂ ጥርጣሬ” ችሎቱ ማየቱን ዳኛዋ ገልጸዋል። ፖሊስ ይህንኑ የሚያሳይ “በሲዲ የተደገፈ ማስረጃ” ማቅረቡንም አክለዋል። 

ችሎቱ በጠበቆች በኩል የቀረበውን “ተገቢውን ትጋት አላደረገም” በሚል የቀረበውን መከራከሪያ፤ በፖሊስ “ተገቢው ትጋት መደረጉን ፍርድ ቤቱ ተመልክቷል” በሚልም ሳይቀበለው ቀርቷል። ፍርድ ቤቱ የችሎት ውሎውን ከማጠናቀቁ በፊት፤ የምስክር ቃል መቀበልን የመሰሉ “ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገቡ” ስራዎች እንዲሰሩ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስ የምርመራ ስራውን ጨርሶ እንዲያቀርብም ለግንቦት 18፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። በጽህፈት ቤት በኩል በተስተናገደው በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ሁለቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአካል ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)