በአማኑኤል ይልቃል
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አምሃራ ሳይንት ወረዳ ስብሰባ በማካሄድ ላይ በነበሩ የዞን፣ የወረዳ እና ቀበሌ አመራሮች ላይ ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 22፤ 2015 የቦምብ ጥቃት ሙከራ መደረጉ ተነገረ። በብልጽግና ፓርቲ የተዘጋጀን ድርጅታዊ ኮንፍረንስ ሲሳተፉ የነበሩትን እነዚህን አመራሮች ኢላማ በማድረግ የተወረወረው ቦምብ ቢፈነዳም፤ በሰው ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የወረዳ አስተዳደሩ አስታውቋል።
በአምሃራ ሳይንት ወረዳ መቀመጫ በሆነችው አጅባር ከተማ ይካሄድ በነበረው በዚህ ስብሰባ ላይ ቦምብ የተወረወረው፤ ትላንት ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል ገደማ እንደሆነ የወረዳው የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፉ ቦጋለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቦምቡ ስብሰባው ይካሄድበት በነበረው የአምሃራ ሳይንት ወረዳ ምክር ቤት አዳራሽ የውጪያኛው ክፍል ላይ ማረፉንም ኃላፊው አስረድተዋል።
“[ቦምቡ] ወደ አዳራሹ ለመግባት አንድ 50 ሴንቲ ሜትር ርቀት ነበር የቀረው። ተፈናጥሮ ግንቡን እና መስታወቱን መትቶታል” ያሉት አቶ ሰይፉ፤ ይህን ተከትሎ በተከሰተው ፍንዳታ የወረዳው ምክር ቤት አዳራሽ መስታወት መሰባበሩን እና የአጥሩ ቆርቆሮ መበጣጠሱን ገልጸዋል። በትላንቱ የጥቃት ሙከራ “በሰው ህይወትም ሆነ በሌላ አካል ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ያሉት የወረዳው ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ሆኖም ግን ቦምቡ የአካባቢው አመራሮች ስብሰባ እያካሄዱ ባሉበት የተወረወረ በመሆኑ ኮንፍረንሱን “ታላሚ እና ታሳቢ ተደርጎ የተፈጸመ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

“[ኮንፈረንሱ] በዞን ከተካሄደ በኋላ በወረዳ ይካሄዳልና፤ ጥቃት የደረሰው ይሄንን በደንብ በሚያውቁ አካላት ነው ተብሎ ነው የሚገመተው” የሚሉት አቶ ሰይፉ፤ ድርጊቱ “እጅግ በጣም በተጠና አግባብ” ለመፈጸሙ ያሉት ሁኔታዎች አመላካች መሆናቸውን ያስረዳሉ። በአምሃራ ሳይንት ወረዳ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ተጀምሮ በትላንትናው ዕለት የተጠናቀቀው የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊ ስብሰባ፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ በክልል ደረጃ ተካሄዶ የነበረው የአመራሮች ኮንፍረንስ ተከታይ ነው።
በባህር ዳር ከተማ ተካሄዶ የነበረው የአማራ ክልል ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ኮንፍረንስ፤ በክልሉ “ወቅታዊ ሁኔታዎች እና የቀጣይ መፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ” የመከረ እንደበረ በወቅቱ ተገልጿል። በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የተካሄደው ይህ ኮንፈረንስ፤ ወደ ዞኖች ደረጃ ወርዶ ባለፉት ሳምንታት ሲካሄድ ቆይቷል። በተያዘው ሳምንት ደግሞ በክልሉ የሚገኙ ወረዳዎች ተመሳሳይ አጀንዳ የያዘውን ኮንፍረንስ በየአካባቢቸው እያካሄዱ ይገኛሉ።
ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የአምሃራ ሳይንት ወረዳ ድርጅታዊ ኮንፍረንስ የመሩት የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ደመቀ አድማሱ፣ የአምሃራ ሳይንት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸው አበሩ እና የወረዳው ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋው አለባቸው ናቸው። በዚህ ኮንፍረንስ ላይ በወረዳው ከሚገኙ 35 ቀበሌዎች የተወጣጡ አመራሮች፣ የወረዳ መሰረታዊ ድርጅት እና የኦዲት ኮሚቴ አመራሮች፣ የወጣት ሊግ ስራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የቀበሌ ስራ አስኪያጆች እንደተሳተፉ ከአምሃራ ሳይንት ወረዳ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በኮንፍረንሱ 190 ሰዎች እንደተሳተፉ የሚገልጹት የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የትላንቱ የቦምብ ውረወራ የተፈጸመው “ኮንፈረንሱ በሰላማዊ መንገድ እንዳይካሄድ” እና “በወረዳው ሞት እና ግድያ እንዲፈጸም” ታስቦ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቦምብ ጥቃት ሙከራውን የፈጸመው አካል እስካሁን አለመታወቁን የጠቆሙት አቶ ሰይፉ፤ የወረዳው የጸጥታ አካል በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ስምሪት መሰጠቱን አክለዋል።
የትላንቱ ጥቃት አስመልክቶ በሚደረገው ምርመራ እስካሁን የተገኘ ውጤት ስለመኖሩ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጌታቸዉ፤ “ቢገኝም፣ ባይገኝም ስንጨርስ ነው የምንነግራችሁ። አሁን ለሚዲያ መስጠት የምንችለው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ሰይፉ በበኩላቸው ከቦምብ ውርወራው ጋር በተያያዘ “የተጠረጠሩ አካላት” ቢኖሩም እስካሁን ግን በቁጥጥር ስር የዋሉ እንደሌሉ አስረድተዋል።
በአማራ ክልል በቀናት ልዩነት ውስጥ የቦምብ ጥቃት ሙከራ ሲደረግ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 19፤ 2015 በተፈጸመ የቦምብ ጥቃት 23 ሰዎች መቁሰላቸውን የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። በዚሁ ጥቃት የተጎዱት የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ በሀዋሳ ከተማ የሚያደርገውን ጨዋታ ለመከታተል ወደ ስፍራው ለመጓዝ የተዘጋጁ ደጋፊዎች እንደነበሩ ከንቲባው በወቅቱ ገልጸዋል። ከንቲባው እርሳቸው በሚመሩት ዳር ከተማ “ከጊዜ ወደ ጊዜ” እየተፈጸመ ነው ያሉትን “የቦምብ ጥቃት እና ግድያ” በዚሁ ጊዜ አውግዘዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)