ኢዜማ፤ የአመራሮች እና አባላት መልቀቅ ፓርቲውን “ለመሰንጠቅ” የሚዳርገው አይደለም አለ

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የአመራሮች እና አባላቱ መልቀቅ፤ ፓርቲውን “ለመሰንጠቅ ወይም ለመክፈል የሚችል አይደለም” አለ። ከፓርቲው አባልነት የለቀቁ ሰዎች ብዛት “ብዙ ቁጥር አይደለም” ሲልም ይህንኑ በተመለከተ የተሰራጩ መረጃዎችን አስተባብሏል። 

ኢዜማ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 29፤ 2015 በአዲስ አበባ ስቴድየም አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤  ከሰሞኑ ፓርቲውን በተመለከተ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያቀረቧቸውን ዘገባዎች ተከትሎ “ብዥታ” መፈጠሩን ገልጿል። ከጋዜጣዊ መግለጫው መጀመር በፊት፣ በመሃል እና ከተጠናቀቀ በኋላ ከጋዜጠኞች ጋር የተፈጠሩ ውጥረቶች በታዩበት በዛሬው መግለጫ፤ መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢዜማ አባላት መልቀቅ በሰሯቸው ዘገባዎች ላይ የፓርቲው አመራሮች ወቀሳዎችን አቅርበዋል። 

ፓርቲው በዛሬው መግለጫው “ጽንፈኛ” ሲል የጠራቸው “ዘውጌ ብሔርተኞች” እና “ሀገራዊ ኃይሎች”፤ ከምስረታው ማግስት ጀምሮ የ“ስም ማጥፋት” ሲያደርጉበት መቆየታቸውን ጠቅሷል። በፓርቲው ላይ የሚቀርቡ “ክሶች” በአሁኑ ወቅት በጎላ መልኩ” መሰማት መጀመራቸውን በመግለጫው ያነሳው ኢዜማ፤ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ግን በፓርቲው ባለፉት አራት ዓመታት በአመራርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ ግለሰቦች የመጣ መሆኑ ነው ብሏል። ይሄም ቢሆን ግን የሚቀርበው ክስ “የኢዜማን ስም ከማጠልሸት የተለየ” እንዳልሆነ አስታውቋል። 

ኢዜማ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫው ከፓርቲው አባልነት የለቀቁ ግለሰቦች፤ “በጋራ የተሰሩ እና የተወሰኑ ውሳኔዎችን ሁሉ” ለሚዲያ ፍጆታ እና “እርስ በእርስ ለመወቃቀስ አውለዋል” ሲል ተችቷል። ራሳቸውን ከኢዜማ አባልነት ያገለሉትን አመራሮች “ተሸናፊ” በሚል ቃል የገለጸው የፓርቲ መግለጫው፤ አመራሮቹ “ለአንድ አመት ያህል ድርጅቱ ቢሮ ደርሰው የማያውቁ [ናቸው]” ሲልም ወንጅሏል።

ፓርቲው እነዚህን ግለሰቦች በስም ባይጠቅስም መግለጫውን ያወጣው ግን፤ ከዚህ ቀደም በአመራርነት ጭምር ያገለገሉ አባላት ከኢዜማ መልቀቃቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው። ይህንን ውሳኔያቸውን የዛሬ ሁለት ሳምንት ይፋ ካደረጉ የኢዜማ የቀድሞ አመራሮች መካከል የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ ይገኙበታል። 

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በተካሄደው የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፓርቲው የምክትል መሪነት የኃላፊነት ቦታ ተወዳድረው የነበሩት አቶ ሐብታሙ ኪታባም በጋራ ይፋ በተደረገው የመልቀቅ ውሳኔ ላይ ተካትተዋል። የአቶ ሐብታሙ ተጣማሪ የነበሩት እና ለኢዜማ መሪነት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተፎካክረው የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌም ተመሳሳይ ውሳኔያቸውን ባለፈው ሚያዝያ ወር ለህዝብ አስታውቀው ነበር። 

ኢዜማን ከምስረታው ጀምሮ በምክትል መሪነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አንዷለም ውሳኔያቸውን ባሳወቁበት ደብዳቤ ላይ፤ ፓርቲው “የተሳከረ ሚና የሚጫወት” እና “የአገዛዝ ጡጫ እንዲፈረጥም” የሚያደርግ መሆኑን በማንሳት መተቸታቸው ይታወሳል። አቶ የሺዋስ አሰፋ የተካተቱበት የቀድሞው የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላት ስብስብም ግንቦት 17፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ሃሳብ አንጸባርቋል።   

እነዚህ ሰባት የቀድሞ የስራ አስፈጻሚ አባላት “የኢዜማ ከፍተኛ አመራር ሀገርን ለመታደግ ሕዝብንና ፓርቲዎችን አስተባብሮ ከማታገል ይልቅ፤ አገዛዙ እየፈጸመ ላለው ሀገር አቀፍ ግፍ ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል” ሲሉ በመግለጫቸው ወቀሳ አቅርበው ነበር። “ፓርቲውን ወደ ሃዲዱ ለመመለስ ትግል” ማድረጋቸው በመግለጫው የጠቀሱት አባላቱ፤ ሆኖም ጥረታቸው “ግቡን አለመምታቱን” አጽንኦት ሰጥተዋል።  “ኢዜማን ጠግኖ ለማዳን ያደረግነው ትግል ከንቱ ቀርቷል” ያሉት አባላቱ፤ በዚህ ምክንያት ከፓርቲው መልቀቃቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

ዛሬ መግለጫ የሰጠው የቀድሞ ፓርቲያቸው ግን የአባላቱ መልቀቅ ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ላይ ከተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ውጤት ጋር የሚገናኝ ነው ባይ ነው። ከአባልነት ከለቀቁት የፓርቲው አባላት ውስጥ “አንዳንዶቹ” በጠቅላላ ጉባኤው ላይ የኢዜማ አመራር ለመሆን ተወዳድረው የነበሩ መሆናቸውን የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ መመሪያ ዋና ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውሰዋል። እነዚሁ አባላት “በጉባኤው ድምጽ የተነፈጋቸው እና አመራር እንዳይሆኑ የፓርቲው የመጨረሻ ወሳኝ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ያሳለፈባቸው ሰዎች ናቸው” ሲሉም አክለዋል። 

ከቀድሞዎቹ የፓርቲው አባላት ጋር ያለው “ዋና ቅራኔ እና ልዩነት” የጠቅላላ ጉባኤውን ውጤት “በመቀበል እና ባለመቀበል” እንዲሁም “አመራር ከመሆን በመለስ በፓርቲው ውስጥ በመስራት እና ባለመስራት” መካከል ያለ መሆኑንም አቶ ዋሲሁን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ከፓርቲው ከለቀቁት ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ “እነርሱ ሲለቁ ፓርቲ የሚሰነጠቅ ሲመስላቸው [ታይቷል]” ሲሉም ወርፈዋቸዋል። 

በኢዜማ አደረጃጀት መሰረት ግለሰቦች አባል የሚሆኑት በፓርቲው የምርጫ ወረዳዎች ላይ መሆኑን ያስታወሱት የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ መመሪያ ዋና ኃላፊ፤ ከአባልነት ሲወጡም የሚለቅቁት ይህንኑ የምርጫ ወረዳ መሆኑን አስረድተዋል። ይህ የፓርቲው አደረጃጀት ግለሰቦች ከአባልነት ሲለቅቁ ፓርቲው “እንዲከፈል እና እንዲሰነጠቅ” የማያስችል ነው ብለዋል።  

“በተለመደው የፖለቲካ ሂደት” “አመራሮች ወይም ደግሞ የተወሰኑ አባላት” ሲለቁ ፓርቲዎች እንደሚሰነጠቁ ያነሱት አቶ ዋሲሁን፤ “ሚዲያውም ህዝቡም ይሄንን የሚያውቅ ስለሆነ ልክ የተወሰኑ ሰዎች ሲወጡ ፓርቲ የፈረሰ አድርጎ ይወስደዋል። የኢዜማ አፈጣጠር ግን ለዚያ የተመቸ አይደለም። በተግባር ይሄንን ማድረግ የሚቻል አይደለም” ሲሉ የፓርቲ መሰንጠቅ ኢዜማን የሚያሰጋው ነገር እንዳልሆነ አብራርተዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

በዛሬው መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ዋሲሁን እና የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉአለም ተገኝ፤ ከፓርቲው የለቀቁ አባላት ብዛትን አስመልክቶ በመገናኛ ብዙሃን የተጠቀሱ ቁጥሮችን አስተባብለዋል። የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ መመሪያ ዋና ኃላፊ “የምርጫ ወረዳ 2/14 ተብሎ ተጠቅሶ ‘41 አባላት ለቀቁ’ ተባለ። እኛ ይሄንን በዝርዝር አጣርተናል። እያንዳንዱን ማለት ነው። ከዚያ ውስጥ ከአራት አባላት ውጪ ሌሎቹ አባላት ያልነበሩ ወይም ከዚህ በፊት በዲሲፕሊን፣ በተለያዩ ምክንያት የታገዱ ናቸው” ብለዋል።

እንደ አቶ ዋሲሁን ገለጻ ከፓርቲው እስካሁን መልቀቃቸው የተረጋገጡ አባላት፤ “በጋራ መግለጫ የሰጡ” ሰባት ግለሰቦች እና “ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያየ ቦታ እና ምርጫ ክልል” ላይ የለቀቁ ሌሎች አባላት ናቸው። የኢዜማ የድርጅት ጉዳይ መመሪያ ዋና ኃላፊው፤ “በብዙ ቁጥር የሚባል የለቀቀ አባል የለም” በሚል በደፈናው ከመናገር ባሻገር በአጠቃላይ ከፓርቲው የለቀቁ አባላት ቁጥር ከመናገር ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)