የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የዋና ጸሀፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን የስራ ዘመን ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢጋድ ዋና ጸሀፊነታቸው እንዲቀጥሉ የተወሰነው፤ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 5፤ 2015 በጅቡቲ በተካሄደው የድርጅቱ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው።
ከመሪዎቹ ውሳኔ በኋላ ዶ/ር ወርቅነህ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ጉባኤው በእኔ ላይ ሙሉ መተማመን አሳድሮ የስልጣን ዘመኔን ለሁለተኛ 4 አመት ስላራዘመልኝ ጥልቅ ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል። ዶ/ር ወርቅነህ ኬንያዊውን ማህቡብ ማሊምን በመተካት የኢጋድ ዋና ጸሀፊ ሆነው የተሾሙት በህዳር 2012 ዓ.ም ነበር።
በዛሬው የኢጋድ ስብሰባ፤ አባል ሀገራት በዙር በሚደርሳቸው የሊቀመንበርነት ኃላፊነት ስልጣን ላይም ለውጥ ተደርጓል። ላለፉት አራት ዓመታት ኢጋድን በሊቀመንበርነት ስትመራ የቆየችው ሱዳን የዛሬውን ጉባኤ ላስተናገደችው ጅቡቲ ኃላፊነቱን አስረክባለች። ኢትዮጵያ ይህን የኃላፊነት ቦታ ለሱዳን አሳልፋ ከመስጠቷ በፊት ለዘጠኝ ዓመታት ኢጋድን በሊቀመንበርነት መምራቷ ይታወሳል።
በጅቡቲ በተካሄደው በዛሬው የመሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል። በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ እና በሶማሊያ ጉዳዮች ላይ በዋነኛነት በመከረው በዚህ ጉባኤ ላይ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብቃት ኢጋድ የጀመረውን የማሸማገል ጥረት በይፋ ተቀላቅለዋል ተብሏል።
ሱዳን በዛሬው ጉባኤ የተወከለችው የሀገሪቱ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በቅርቡ በተሾሙት ማሊክ አካር ነው። ኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ኦስማን ሳለህን በጉባኤው ላይ አሳትፋለች። በዛሬው የጅቡቲ ጉባኤ፤ ኤርትራ የኢጋድ አባልነት እንቅስቃሴዋን በይፋ እንደጀመረች የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል አስታውቀዋል።
በጉባኤው ከኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተጨማሪ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አማካሪ የሆኑት የማነ ገብረ አብ ተሳትፈዋል። ኡጋንዳ በእንደዚህ አይነት ጉባኤዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ በሚሆኑት ፕሬዝዳንቷ ዩዌሪ ሙሴቬኒ ምትክ፤ ወደ ስፍራው የላከችው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኦዲንጎ ጄጄ አቡባካርን ነው።
የአምስት ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት የዛሬው መደበኛ ጉባኤ፤ ከ57 ዓመታት በፊት የተመሰረተበትን ስምምነት በአዲስ ተክቷል። በአዲሱ ስምምነት መሰረት ከአሁን በኋላ፤ አባል ሀገራት የኢጋድ ሊቀመንበርነትን ይዘው የሚቆዩት ለአንድ ዓመት ብቻ ይሆናል። አባል ሀገራቱ የሊቀመንበርነቱ ስልጣን በዙር የሚደርሳቸው እንደ ስማቸው ቅደም ተከተል እንደሚሆንም ተገልጿል።
ዋና መቀመጫውን በጅቡቲ ያደረገው ኢጋድ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት አባል ሀገራት አሉት። ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ የክፍለ አህጉራዊው ድርጅት አባል ሀገራት ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሏል]