በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ከቤት ግብር ነጻ እንዲሆኑ አሊያም መጠነኛ ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ ጥናት እያደረገ መሆኑን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። የከተማ አስተዳደሩ ከቤት ግብር እስካሁን ድረስ 600 ሚሊዮን ብር ገደማ ገቢ መሰብሰቡን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
አዳነች አቤቤ ይህንን ያስታወቁት ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ትላንት ሐሙስ ሰኔ 15፤ 2015 ምሽት የተላለፈው የከንቲባዋ ቃለ ምልልስ ዋነኛ ትኩረቱን ያደረገው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ የተመን ማሻሻያ ባደረገበት የቤት ግብር አፈጻጸም ላይ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ይህን ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ፤ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ጭማሪ መታየቱ እና አዲሱ ተመን “በነዋሪዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ያመጣል” መባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መነጋገሪያ ሆኖ ከርሟል።
የከተማይቱ ከንቲባ የግብር ተመን ማሻሻያው በራሱ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል ብሎ ለማመን እንደሚያስቸግራቸው ገልጸዋል። “እንዴት ነው የአዲስ አበባን ህዝብ እቺን ግብር በማሻሻል የኑሮ ውድነትን ጫና የምናመጣበት? አንደኛ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ላይ አይደለም ይሄ ሁኔታ እየታየ ያለው። የተሻለ ገቢ ያለው ነው የግብር አከፋፈሉን እየተቃወመው ያለው። ሚዲያም የመክፈል አቅም ያለው እርሱ ነው” ሲሉ “በርካታ የማህበረሰብ ክፍል” የግብር ተመኑ ላይ ተቃውሞ እንደሌለው ተናግረዋል።

ከንቲባዋ “በራሳቸው ከፍተኛ ገቢ ከማግኘት ውጪ አሳልፈው ማሰብ የማይችሉ” ሲሉ የጠሯቸው አካላት፤ በቤት ግብር አከፋፈል ሂደቱ ላይ “ተጽዕኖ ለማሳረፍ ጥረት እያደረጉ” መሆኑን ጠቅሰዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቤት ግብር ላይ ያደረገውን ማሻሻያ በሚያዝያ ወር ይፋ ካደረገ በኋላ 91 ሺህ የቤት ባለቤቶች በአዲሱ ተመን መሰረት ክፍያ መፈጸማቸውን የገለጹት አዳነች፤ ከዚህ ውስጥ ግብር የከፈሉ የንግድ ተቋማት ቁጥር አንድ በመቶ እንደማይሞላ አስታውቀዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት ግብር ከተከፈለባቸው ቤቶች ውስጥ 62 በመቶው የኮንዶሚኒየም ቤቶች መሆናቸውን ከንቲባዋ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ጠቅሰዋል። እስካለፈው ሚያዝያ ወር ድረስ በአዲስ አበባ የቤት ግብር ሲከፍሉ የቆዩ ቤቶች ብዛት 183 ሺህ ገደማ እንደሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ፋይናንስ ቢሮ ከአንድ ወር በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጾ ነበር። ግብር ከሚከፈልባቸው ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ 46 በመቶው የሚከፍሉት “ከአስር ብር በታች” እንደነበር ከቢሮው የተገኘ መረጃ አመልክቷል። በግብር ተመኑ ላይ ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት፤ 2,500 ያህል ቤቶች ከአንድ ብር በታች ይከፍልባቸው እንደነበርም መረጃው ጠቁሟል።
አዲሱ የቤት ግብር ተመን ማሻሻያ የኑሮ ውድነት የሚያመጣ ከሆነ “ተጽዕኖው የሚያርፈው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የከተማ ነዋሪዎች ላይ” እንደሚሆን የተናገሩት አዳነች፤ በዚህ ምክንያት ጫና ከተፈጠረ ከዚህ ግብር ነጻ መደረግ ያለበት ይህ የማህበረሰብ ክፍል መሆኑን በቃለ ምልልሳቸው አንስተዋል። እርሳቸው የሚመሩት የከተማዋ አስተዳደር ይህንን ለማድረግ ጥናት እያደረገ መሆኑን አዳነች አስታውቀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን አዲሱን የተመን ማሻሻያ መሰረት ባደረገበት የ1968ቱ የከተማ ቦታ ኪራይ እና የከተማ ቤት ግብር አዋጅ ላይም ይህ ሀሳብ የተካተተ መሆኑን ከንቲባዋ አስረድተዋል።

አዋጁ “የገቢ መጠናቸው ከ300 ብር ያልበለጠው [ከቤት ግብር] ነጻ ይሁኑ” የሚል ሀሳብ መያዙን ያስታወሱት፤ የእርሳቸው አስተዳደር ስህተት ላለመስራት ወደ ጥናት መግባቱን ጠቁመዋል። የትኛዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ግብር መክፍል እንደሌለባቸው የሚለይ ቡድን ተቋቁሞ ጥናት እያደረገ መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ “እስከ ስንት ፐርሰንት ድረስ ወይም ደግሞ እስከ ስንት የገቢ መጠን ነጻ እናድርገው የሚለውን እንደጨረስን ለህዝባችን ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ የከተማ አስተዳደሩን እቅድ አመልክተዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎችን፤ በምን መልኩ ዝቅተኛ ክፍያ ማስከፈል እንደሚቻል በጥናቱ እንደሚታይም አዳነች ተናግረዋል። “ዝቅተኛ ክፍያ መክፈል የሚችሉት፤ በመጠኑ ይክፈሉ። የተሻለ ገቢ ያላቸው ደግሞ የተሻለ መክፈል የሚችሉበትን፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸው መካከለኛ መክፈል የሚችሉበትን ሂደት መሄድ መቻል አለብን። ከዚህ ውጪ ግብር መክፈል ግዴታ ነው ተብሎ መከፈል መቻል አለበት” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲሱን ተመን ተግባራዊ ካደረገ በኋላም ቢሆን፤ ከቤት ግብር የሚያገኘው ገቢ “አነስተኛ” መሆኑን ከንቲባዋ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ 600 ሚሊዮን ብር ገደማ ከቤት ግብር መሰብሰቡን የተናገሩት አዳነች፤ ይህ የገንዘብ መጠን በከተማው በአጠቃላይ ከሚሰበስበው 100 ቢሊዮን ብር የግብር ገቢ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ ይህንን ቢሉም፤ በዚህ ዓመት ከቤት ግብር የተሰበሰበው ገቢ የተመን ማሻሻያ ከመደረጉ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ ያስመዘገበ ሆኗል። የከተማ አስተዳደሩ በሚያዝያ ወር ላይ ይህንን ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት፤ በአዲስ አበባ የቤት ግብር ከሚከፍሉ 183 ሺህ ገደማ መኖሪያ ቤቶች የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ 47.7 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የከተማይቱ ፋይናንስ ቢሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቆ ነበር። የከተማ አስተዳደሩ አሁን የሰበሰበው 600 ሚሊዮን ገደማ ብር ከዚህ ጋር ሲነጻጸር 1,157.8 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ይህ መጠን ያለው የቤት ግብር ገቢ ጭማሪ ያገኘው፤ ከተመን ጭማሪ ባሻገር ከዚህ ቀደም በግብር ስርዓቱ ውስጥ ያልተካተቱ ቤቶችም ክፍያ እንዲፈጸምባቸው ውሳኔ በማስተላለፉ ነው። ከንቲባ አዳነች፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙት አገልግሎት የሚሰጡ የመኖሪያ እና የንግድ ህንጻዎች ውስጥ 600 ሺህ ገደማው ከዚህ ቀደም የቤት ግብር የማይከፍሉ እንደነበር በቃለ ምልልሳቸው ላይ ጠቅሰዋል። ከሚያዝያው ማሻሻያ በፊት ይህንን ግብር ሳይከፍሉ ከቆዩት ቤቶች መካከል፤ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)