ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ31 ቢሊየን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ እንደገጠመው አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት አምስት ዓመታት ከ31 ቢሊየን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ እንደገጠመው የተቋሙ ዋና የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰግድ አየለ ተናገሩ። የኩባንያው ትርፍ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ12 በመቶ ወደ 22 በመቶ ቢደርስም፤ የዋጋ ንረት እና የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ እንደሚፈታተኑት አቶ አሰግድ ገልጸዋል። 

የተቋሙ ዋና የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ ይህን ያሉት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች የኩባንያውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ዛሬ አርብ ሰኔ 16፤ 2015 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው። በዛሬው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩን ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ዋና አስራ አስፈጻሚዋ የሚመሩት ተቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ዘጠኝ ወራት 52.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን እና 103 ሚሊዮን ዶላር ማስገባቱን ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ስራ ያስጀመረው “ቴሌ ብር” የተሰኘው የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር ከ30.5 ሚሊዮን በላይ መድረሱንም አስታውቀዋል። በዚህ አገልግሎት ባለፈው ዘጠኝ ወራት ብቻ 394.7 ቢሊዮን ብር ዝውውር መፈጸሙንም ተናግረዋል።   

በኢትዮ ቴሌኮም ትርፋማነት ላይ ማብራሪያ የሰጡት የተቋሙ ዋና የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ፤ ተቋሙ ባለፉት አምስት ዓመታት ትርፋማ ቢሆንም “በርካታ ተግዳሮቶች” እንዳሉበት አመልክተዋል። “ግብዓቶቻችን ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጫና አለብን” ያሉት አቶ አሰግድ፤ ኢትዮ ቴሌኮም “የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዳው ኩባንያ” እንደሆነም አስረድተዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም “ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ31 ቢሊየን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ አስተናግዷል” ያሉት የተቋሙ ዋና የፋይናንስ ስራ አስፈጻሚ፤ የስራ ቅልጥፍናውን በመጨመር እና ምርታማነቱን በማሳደግ ትርፋማ ሆኖ መቀጠል መቻሉን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል። ተቋሙ ባለፉት አስር ዓመታት ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ባልሆነ ታክስ ወደ 130 ቢሊዮን ብር ገደማ መክፈሉን የጠቆሙት አቶ አሰግድ፤ በትርፍ ክፍፍል (dividend) ደግሞ ከ50 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ለመንግስት “ፈሰስ” ማድረጉን አብራርተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ አመራሮች ለተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት እና ግጭት ምክንያት የወደሙ የተቋሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ተነስቷል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት “በርካታ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት” መድረሱን ያስታወሱት ፍሬሕይወት፤ ተቋሙ “የጸጥታ ሁኔታዎች በተረጋጉበት ጊዜ ከስር ከስር ጥገናዎች” ሲያከናውን እንደቆየ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። 

በጦርነት እና “አንዳንድ አካቢዎች ላይ በነበረ የጸጥታ ችግር” ምክንያት ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ 853 የሞባይል ጣቢያዎች እና ከ1,886 ኪሎ ሜትር በላይ የፋይበር መስመር ላይ ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ጥገና  ማከናወኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል። ኩባንያው ባከናወነው ጥገና 172 ከተሞች እና ወረዳዎች እንዲሁም 29 የፋይናንስ ተቋማት የተቋረጠባቸውን አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ፍሬሕይወት፤ “ይሁንና ግን አሁንም ያልተጠናቀቁ፤ ተዘዋውረን መስራት ያልቻልንባቸው አካባቢዎች አሉ” ብለዋል።

ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ አሉታዊ ተጽዕኖ ካሳደሩ ጉዳዮች መካከል፤ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄደው የዋጋ ግሽበት እና የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሚገኙበት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል። በክልሎች በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እና የነዳጅ እጥረት፤ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ጥራት እና የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩም ተገልጿል። የመሰረተ ልማት ስርቆት እና የቴሌኮም ማጭበርበር ደግሞ “በተቋሙ ገቢ እና በደንበኞች እርካታ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ” በሚል በዛሬው ስብሰባ የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)