በዘንድሮው ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያህል የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት ማቀዷን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ገለጹ። ሀገሪቱ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 350 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሏንም አስታውቀዋል።

በ2013 የተዘጋጀው የኢትዮጵያ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በዋናነት ኤክስፖርት መር ቢሆንም “ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየወጣባቸው ያሉ ነገር ግን በትንሽ ጥረት ንጽጽራዊ አቅም ሊፈጠርባቸው የሚችሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የመተካት ስትራቴጂን” ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል። በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከሚውሉ ምርቶች ውስጥ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት 38 ከመቶ ብቻ መሆኑን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

ኢትዮጵያ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ በጀመረችው የተኪ ምርት (import substitute) ስትራቴጂ መሰረት 96 ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ማቀዷ ተገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ ቀዳሚው ትኩረት የሚሰጣቸው፤ በሀገር ውስጥ ግብዓት መመረት የሚችሉ የምርት አይነቶች መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 26፤ 2016 ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

“አብዛኛው የኢንዱስትሪ ችግር የግብዓት [ነው]። ግብዓት ከውጪ ነው የምናመጣው። ስለዚህ የመጀመሪያውን ትኩረት የሚያገኙት የሀገር ውስጥ ግብዓትን ተጠቅመው ማምረት የሚችሉ ኢንዱስትሪዎችን ነው” ሲሉ አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት “መቶ ፐርሰንት የመተካት ዕድል አላት” ከተባሉ ምርቶች ውስጥ የጨርቃ ጨርቃ እና የቆዳ ውጤቶች ናቸው። 

“ቆዳ አንዱ ተወዳዳሪ ሊያደርገን የሚችል ነገር ግን ያልተጠቀምንበት ነው። አሁን የቆዳው ኢንዱስትሪ እየተጎዳ ነው። ለምንድነው? አንደኛ የጸጥታም ችግር ኢንዲስትሪም ላይ ጉዳት አለው። ሌላው በዕዝ ሰንሰለት [ምክንያት] ቆዳው እየተለቀመ ወደ ገበያ በሚገባ እየቀረበ አይደለም” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር አብራርተዋል። 

የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች እነዚህን መሰል ችግር ቢያጋጥማቸውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ግን አሁንም በዘርፉ ትልቅ ስኬት ለማስመዘገብ ወጥኗል። ይህ የመንግስት ውጥን፤ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ 30 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች በሀገር ውስጥ የተመረተ ጫማ እና ቦርሳን በዩኒፎርም መልክ እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያለመ ነው። 

ፎቶ፦ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት

በአዲስ አበባ ከተማ በመንግስት ትምህርት ቤቶች የተጀመረው ይህ ተነሳሽነት፤ በግል ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንዲደረግ እና ወደ ክልሎችም እንዲሰፋ መንግስት ይሻል። የተማሪዎች ጫማ እና ቦርሳን በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የተያዘው እቅድ ግን አሁን ያሉት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱም እንኳ “ሊያሳኩት” እንደማይችሉ አቶ ታረቀኝ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ “አዳዲስ የቆዳ ኢንቨስትመንቶች፣ የቆዳን ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች” እንደሚያስፈልጉ ሚኒስቴር ዲኤታው ጠቁመዋል። “በአንድ በኩል ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ የማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብ የማበረታቻ ስርዓት በመዘርጋት ወደ ምርት እንዲገቡ መደረግ አለበት” ሲሉ አቶ ታረቀኝ በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል ሊደረግ የሚገባውን አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)