የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በቦሌ አየር ማረፊያ በቁጥጥር ስር ዋሉ

በተስፋለም ወልደየስ

በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው ከስልጣናቸው የተነሱት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር ዋሉ። አቶ ጸጋዬ በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የተያዙት፤ ለተወሰኑ ጊዜያት “ተሰውረው ከቆዩበት” አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ነው ተብሏል። 

አቶ ጸጋዬ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 13፤ 2016 ረፋድ አምስት ሰዓት ገደማ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመያዛቸውን የሲዳማ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እያሱ ዳዊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የቀድሞው ከንቲባ ለሶስት ዓመት ገደማ በኃላፊነት ሲያስተዳድሯት ወደቆዩት ሀዋሳ ከተማ፤ በሲዳማ ክልል እና በፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ታጅበው ዛሬ ምሽት 12 ሰዓት ገደማ መድረሳቸውንም ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ አቶ ጸጋዬ በሀዋሳ ከተማ ወደ “የእስረኛ ማቆያ” መወሰዳቸውን አስታውቋል። የሲዳማ ክልል የጸጥታ ግብረ ኃይል፤ የቀድሞውን ከንቲባን በቁጥጥር ስር ለማዋል “ያልተቋረጠ ክትትል ሲያደርግ እንደነበርም” ቢሮው በመግለጫው ጠቁሟል። 

አቶ ጸጋዬ በክልል ደረጃ ሲካሄድ የነበረን “የአመራር ግምገማ ረግጠው በመውጣት ተሸሽገው እንደነበር” የጠቀሰው የቢሮው መግለጫ፤ ይህንን ያደረጉትም “ከተጠረጠሩበት ወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ” እንደሆነ አመልክቷል። የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደ የክልሉ መንግስት እና ገዢ ፓርቲ የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” መገምገማቸው ይታወሳል።

ይኸው ግምገማ ሲጠናቀቅ አቶ ጸጋዬ “ከስልጣናቸው ተነስተው በህግ ይጠየቁ” የሚል ውሳኔ ተላልፎ እንደነበር በስፍራው የነበሩ አንድ ምንጭ በወቅቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸው ነበር። የነሐሴው ግምገማ ሲጀመር ተሳታፊ እንደነበሩ የተነገረላቸው አቶ ጸጋዬ፤ እርሳቸው በሌሉበት ከተላለፈው ውሳኔ በኋላ ግን “ተሰውረው መቆየታቸውን” አንድ የክልሉ ኃላፊ ያስረዳሉ። 

በዚህ ግምገማ ከቀድሞው ከንቲባ በተጨማሪ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው የሚሰሩ ከፍተኛ አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲነሱ በመደረጉ፤ የከተማይቱ መንግስታዊ ስራዎች ለሁለት ሳምንት ያህል “በኮሚቴ ሲሰሩ” ቆይተዋል። የሲዳማ ክልል የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት ባለፈው ነሐሴ ወር ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሀዋሳ ከተማን እንዲያስተዳድሩ ሾሟል።

አቶ መኩሪያ ወደ ክልል የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው በፊት፤ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በሲዳማ ክልል የዳዬ ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል። በቀደሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስርም እስከ ምክትል ቢሮ ኃላፊነት ባሉት ቦታዎች ሰርተዋል። አዲሱ ከንቲባ ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ፤ 12 አዳዲስ ተሿሚዎችን የያዘ አዲስ ካቢኔ አዋቅረው ወደ ስራ መግባታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)