የመከላከያ ሚኒስትሩ በክልሎች በየደረጃው ያሉ አመራሮች “አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማጽዳት አልቻሉም” ሲሉ ወቀሱ

በተስፋለም ወልደየስ

በክልሎች በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አመራሮች “አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማጽዳት ባለመቻላቸው”፤ የመከላከያ ሰራዊት “የመንግስት መዋቅር ስራን ደርቦ እንዲሸፍን እየተገደደ ይገኛል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ወቀሱ። ሚኒስትሩ “የሽፍታ እንቅስቃሴ” ሲሉ የጠሩት ድርጊት እና በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ እገታዎች የሚከሰቱት፤ በክልሎች ባሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላት “መሰራት ያለበት ስራ ባለመሰራቱ” መሆኑን ገልጸዋል። 

የመከላከያ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት፤ ከዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹን የሶስት ወራት የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው። ዶ/ር አብርሃም ለተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ፤ በሩብ ዓመቱ ያጋጠሙ “ችግሮች እና ፈተናዎች” በሚል ከዘረዘሯቸው ውስጥ አንዱ የመከላከያ ሰራዊት ስምሪት በየአካባቢው እንዲሰፋ መደረጉን ነው።

“የመንግስት መዋቅር ላይ ያሉ አመራሮች ህዝባቸውን በማስተባበር አካባቢያቸውን ከሽፍቶች ማጽዳት ባለመቻላቸው፤ የሰራዊታችን ግዳጅ እንዲሰፋ እና የክልል መንግስት መዋቅር ስራን ደርቦ እንዲሸፍን እየተገደደ ይገኛል” ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አስፍረዋል። ዶ/ር አብርሃም ይህንኑ ጉዳይ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅትም በድጋሚ በአጽንኦት አንስተውታል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ከውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ፤ ከአዲስ አበባ በቅርበት ርቀት በሚገኙ ከተሞች ሳይቀር “የሰዎች እገታ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ መሆኑን” የተመለከተ ነው። ጥያቄውን ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ፤ እገታው “በተለይ ከክልሎች የሚያገናኙ ዋና ዋና መንገዶች ላይ” የሚፈጸም መሆኑን ገልጸዋል። 

“እዚህ አቅራቢያችን ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ሰዎች ይታገታሉ። ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት አልቻሉም። ከፍተኛ ብር ይጠየቃሉ። ይህ ሁኔታ ዜጎችን እጅግ እያማረረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዋና ከተማ፣ ከአፍሪካ መዲና፣ በአቅራቢያችን ካሉ ከተሞች ውስጥ የሚፈጠሩ፣ የሚሰሙ፣ በጣም የሚያሳዝኑ፣ የህብረተሰቡን ሰላም የሚያውኩ ተግባራት ሲከናወኑ እየሰማን ስለሆነ፤ መከላከያ ከሌሎች የክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ይሄንን ነገር ማስቆም ያልተቻለበት ምክንያት ምንድነው?” ሲሉ ዶ/ር ፈትሂ ጥያቄያቸውን ለሚኒስትሩ አቅርበዋል።

ለጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር አብርሃም፤ በመጀመሪያ ደረጃ ከመግባባት ላይ መደረስ ያለበት “የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞን፣ የሰፈሮችን ጸጥታ እና ደህንነት ማረጋገጥ ያለበት ማነው?” የሚለው ጥያቄ ላይ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል። በቀበሌ፣ በወረዳ አሊያም በሌሎች የመንግስት መዋቅሮች ያሉ አስተዳዳሪዎች፤ በየተመደቡባቸው ቦታዎች ያሉ “የጸጥታ እና የደህንነት” ጉዳይ ጭምር የሚመለከታቸው እንደሆኑ የመከላከያ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“አሁን እየሆነ ያለው፤ ቀበሌ የሚያስተዳድረው፣ ህዝቡን አስተዳድሮ፣ ሽፍታ እንዳይኖርበት መስራት እያለበት ‘መከላከያ ይምጣልኝ’ ይላል። መከላከያ የቀበሌ አስተዳደር አይደለም። የመከላከያ ተልዕኮም አይደለም። ቀበሌ ማስተዳደርም ሆነ፤ የቀበሌ ሽፍታ፣ ሌባ፣ ወንበዴ ማጽዳት የመከላከያ ስራ አይደለም። ሚሊሺያ ምን ይሰራል? ፖሊስ ምን ይሰራል? ካለፈ እንኳ ፌደራል ፖሊስ የት ይሄዳል?” ሲሉ ዶ/ር አብርሃም ጠይቀዋል። 

“በየመንደሩ ያለ የሌባ እና የወንበዴ እንስቃሴ መከላከያ መጥቶ ያጽዳ” የሚሉ ፍላጎቶች “እየሰፉ ከሄዱ ስራ መስራት አይቻልም” ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ፤ ይህ አይነት አስተሳሰብ መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል። የመከላከያ ሰራዊት ተልዕኮ “ሰፊ” መሆኑን እና “ብዙ ስራ ያለበት” መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር አብርሃም፤ ለዚህም ተቋሙ “ብዙ መዘጋጀት እንደሚጠበቅበት” አስገንዘበዋል። 

“ሀገር ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ፣ ቀጣይ ሊመጡ የሚችሉ ነገሮችን መመከት እና ማስቀረት የሚችል ሰራዊት ነው መገንባት ያለብን እንጂ በየመንደሩ ያለ ሌባ ማሳደድ አይደለም የመከላከያ ሰራዊት ስራ። ይሄ መሰረታዊ ጉዳይ መስተካከልም፤ መያዝም ያለበት ይመስለኛል” ሲሉም ሚኒስትሩ አክለዋል። የኢፌዲሪ ህገ መንግስት የመከላከያ መርሆዎችን ባሰፈረበት ክፍሉ፤ የመከላከያ ሰራዊት “የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የመጠበቅ” እንዲሁም “በህገ መንግስቱ መሰረት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚሰጡትን ተግባሮች” እንደሚያከናውን ይደነግጋል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ተሻሽሎ የጸደቀው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ በበኩሉ፤ ከሰራዊቱ ተልዕኮዎች አንዱ “የሀገርን ሉዓላዊነትም ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከውጭ ወራሪና ከውስጥ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ስጋትና ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል” መሆኑን አስቀምጧል። ሰራዊቱ “አግባብነት ካላቸው የፌደራልና የክልል መስተዳድሮች የደህንነትና የጸጥታ መዋቅሮች ጋር ተቀናጅቶ መስራት” እንዳለበትም አዋጁ ያትታል።   

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች “የሽፍታ እንቅስቃሴ” መኖሩን የተናገሩት ዶ/ር አብርሃም፤ ይህን “የማጽዳት ስራ” “እየሰፋ እና እየተተገበረ” የሚሄደው “የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት ወስደው ከሰሩ” መሆኑን ጠቅሰዋል። “ክፍተቱ ያለው በዋናነት በአስተዳደር አካላት፣ በሰፈር የጸጥታ አካላት፣ በክልል የጸጥታ አካላት መሰራት ያለበት ስራ ባለመሰራቱ ካልሆነ በስተቀር በስፋት ጠመንጃ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካላትን ከሰራዊታችን ጋር ፊት ለፊት ገጥመው ሊያሸንፉም፣ ለማሸነፍ ሊያስቡ እንደማይችሉ ማረጋገጫው በተግባር ታይቷል” ሲሉም የመከላከያ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገልጸዋል።

ዶ/ር አብርሃም ለዚህ በማረጋገጫነት የጠቀሱት፤ ከወራት በፊት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮችን በማነጻጸር ነው። “ከሶስት ወር በፊት የነበረው ሁኔታ እና አሁን ያለው ሁኔታ ጠቅላላ የተለያዩ ናቸው። በአማራ ክልልም የተለየ ነው። በአዲስ አበባ አካባቢም ይሁን በኦሮሚያ በስፋት ያሉ አካባቢዎች እጅግ በጣም የተለየ ነው። ቀንሰዋል ብቻ ሳይሆን መንግስት ያፈርሳሉ ብሎ የነበረው መንፈስም ጠፍቷል። ያንን ዕድል እንደማያገኙም በተግባር ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል። ማሰብ እንዳይችሉ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ።

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ዲማ ነገዎ በመከላከያ ሚኒስትሩ የተነሳውን ሀሳብ ያስተጋባ ሀሳብ ሰንዝረዋል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት “ወዲያ እና ወዲህ” “ለብዙ ግዳጅ እንደሚጠራ” ያስታወሱት ዶ/ር ዲማ፤ ለወደፊቱ በተቻለ መጠን “በሀገር ውስጥ በጸጥታ ማስከበር ስራ ውስጥ መሳተፍ ያለበት ተቋም አይደለም” ብለዋል።

“የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገር አለኝታ ነው። ሀገርን እና ህዝብን የመጠበቅ፤ ለወደፊቱም ደግሞ እንደ deterrence የሚሰራ ኃይል ሆኖ ነው እንጂ የሚሰራው፤ በሀገር ውስጥ ጥቃቅን ችግሮች ውስጥ ሁሉ ከተሳተፈ ተቋሙ ራሱ ችግር ውስጥ ይገባል። በተለይ የፖለቲካ ችግሮችን የፖለቲካ አመራሩ ነው መፍታት ያለበት። [ሰራዊቱ] በተቻለ መጠን ሀገር ውስጥ፣ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]