የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “በአስቸኳይ” ምርጫ እንዲካሄድ ጠየቀ

በሃሚድ አወል

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች በዚህ ዓመት “በአስቸኳይ” ምርጫ እንዲካሄድ ጥያቄ አቀረበ። ፓርቲው ምርጫ ማካሄድ ካልተቻለ “ሌሎች ህገ-መንግስታዊ አማራጭ መፍትሔዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ” አሳስቧል።

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቦዴፓ ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 24፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ያልተካሄደው ምርጫ፣ የክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እና ከታጣቂዎች ጋር የተደረጉ የሠላም ስምምነቶች በፓርቲው መግለጫ ትኩረት ያገኙ ጉዳዮች ናቸው።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ “በጸጥታ ችግር ምክንያት” ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ያስታወሰው ፓርቲው፤ አሁን በስራ ላይ ያለው የክልሉ መንግስት “የስራ ዘመኑን ያጠናቀቀ” መሆኑን ገልጿል፡፡ በክልሉ “አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት” መስፈኑን የጠቆመው ቦዴፓ በክልሉ “ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ” አለ የሚል ግምት አለው፡፡ የቦዴፓ የፖለቲካ ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ በክልሉ ከ80 እስከ 90 በመቶ አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ይህን ቢሉም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ ግን የተለየ ሃሳብ አላቸው፡፡ አቶ ታደሰ “በምርጫ ቦርድ [በኩል] የክልሉ ሰላም ተሻሽሏል፤ አልተሻሻለም የሚለውን አልገመገምነውም” ይላሉ፡፡ የክልሉ መንግስት ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ከታጣቂዎች ጋር ያደረጋቸው ስምምነቶች “ውጤታቸው ገና አልታየም” የሚሉት አቶ ታደሰ፤ “አሁንም በክልሉ ያለ እጀባ መንቀሳቀስ አይቻልም” ሲሉ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያብራራሉ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካሉት 99 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊዎች የታወቁባቸው 28ቱ ብቻ ናቸው። እነዚህን የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው። ነገር ግን  በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተገኘው ይህ ውጤት መንግስት ለመመስረት በቂ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን የክልሉ ምክር ቤት እና ክልሉን እያስተዳደረ ያለው መንግስት የተመረጡት በ2007 በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ነው።

“በክልሉ አሁን ያለው መንግስት የስልጣን ጊዜው ያበቃ እና ከህዝብ ጋር ያለው ውል የተቋረጠ ነው” የሚሉት አቶ ዮሐንስ ፓርቲያቸው ሶስት አመራጮች ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ዮሐንስ ቦዴፓ ያቀረበው የመጀመሪያው አማራጭ፤ “የፌደራል መንግስት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያደራጅ” የሚጠይቅ ነው። ይህ ካልሆነ ፓርቲው “የሽግግር መንግስት በክልል ደረጃ ይደራጅ” የሚል ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን አቶ ዮሐንስ አክለዋል፡፡ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስቱ አካል መሆን አለባቸው የሚል አቋም  ቦዴፓ እንዳለው አቶ ዮሐንስ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሶስተኛው እና በቦዴፓ የቀረበው የመጨረሻ አማራጭ ደግሞ “ባለ አደራ መንግስት” እንዲቋቋም የሚጠይቅ ነው።

ፓርቲው በክልሉ የሽግግር፣ ጊዜያዊ ወይም ባለ አደራ መንግስት እንዲቋቋም ሲጠይቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው አይደለም። ቦዴፓ በመስከረም 2014 ባወጣው መግለጫ ተመሳሳይ ጥያቄን አቅርቦ ነበር፡፡ ፓርቲው በወቅቱ ጥሪውን ያቀረበው፤ በክልሉ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ ባለመኖሩ “የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር” በማሰብ እንደሆነ አስታውቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦዴፓ ጥያቄውን ካቀረበ አስራ ሰባት በኃላም በክልሉ ምርጫ አልተካሄደም፤ የሽግግር መንግስትም አልተመሰረተም፡፡

አቶ ዮሐንስ የቦዴፓ ጥያቄ እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ሰኔ 30 ድረስ ምላሽ ካላገኘ “ጉዳዩን ወደ የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ እና የፌደሬሽን ምክር ቤት እንወስደዋለን” ሲሉ ፓርቲው በቀጣይ የሚከተለውን ሂደት ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ታደሰ ግን “ሰው እንደከዚህ በፊቱ ያለ እጀባ መንቀሳቀስ ሲችል ነው ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው፡፡ ለምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ነው የሚንቀሳቀሰው ስለዚህ ሰላሙ ሳይረጋገጥ ወደ ምርጫ መሄድ አይቻልም” ሲሉ በቦዴፓ ጥያቄ መሰረት ምርጫ በቅርቡ እንደማይካሄድ ተናግረዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)