መስከረም አበራ “በጥላቻ ንግግር” እና “በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት” ክስ ተመሰረተባት

በሃሚድ አወል

የፌደራል ዐቃቤ ህግ የ“ኢትዮ ንቃት” የዩ-ቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት በሆነችው መስከረም አበራ እና አምሀ ደገፋ በተባሉ የስራ ባልደረባዋ ላይ “በጥላቻ ንግግር” እና “በሐሰተኛ መረጃ ስርጭት” ሁለት ክሶች መሰረተ። ክሱ የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ መስከረም ክሷን በውጭ ሆና እንድትከታተል የ50 ሺህ ብር ዋስትና ፈቅዷል።

ዐቃቤ ህግ ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 27፤ 2015 በዋለው ችሎት፤ በመስከረም ላይ ክስ የመሰረተው በባለቤትነት በምታስተዳድረው “ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን ባስተላለፈቻቸው ፕሮግራሞች መሆኑን አስረድቷል። መስከረምን ወክለው በችሎት የተገኙት ሁለት ጠበቆች “ክሱ አሁን ነው የደረሰን ዝርዝር ክርክር ለማቅረብ ጊዜ ያስፈልገናል” በሚል የዋስትና ክርክር ማንሳታቸውን ጠበቃዋ ሄኖክ አክሊሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይር” ተናግረዋል።

ጠበቆቹ በክስ መዝገቡ ላይ ምስክሮች አለመጠቀሳቸውን በማንሳት፤ ደንበኛቸው “በዋስትና ብትወጣ ልታበላሸው እና ችግር ልትፈጥርበት የምትችለው ማስረጃ አለመኖሩን” ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ተከሳሿ “ቋሚ አድራሻ ያላት እና በዋስትና ብትወጣ ግዴታዋን አክብራ የምትቀርብ” መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቷ እንዲጠብቅላት ጠይቀዋል።

የጠበቆችን የዋስትና ጥያቄ በተመለከተ ዐቃቤ ህግ “የተለየ የማቀርበው ክርከር የለኝም” ማለቱን ተከትሎ፤ ፍርድ ቤቱ መስከረም በ50 ሺህ ብር ዋስትና ጉዳዩዋን በውጭ ሆና እንድትከታተል መወሰኑን ጠበቃዋ አቶ ሄኖክ አስረድተዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ችሎት የዛሬውን የችሎት ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት፤ የዐቃቤ ህግን ክስ ለተከሳሽ ለማንበብ ለመጪው ጥር 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም፤ በክስ መዝገቡ በሁለተኛነት ለተጠቀሱት ለአቶ አምሃ ደገፋ የፌደራል ፖሊስ መጥሪያ አድርሶ በቀጠሮው ቀን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ አምሃ ክስ የተመሰረተባቸው በሌሉበት ነው። 

ራሷ በባለቤትነት በምታስተዳድረው እና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች የምትታወቀው መስከረም አበራ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ከሶስት ሳምንት ገደማ በፊት በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነው። መስከረም በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የዛሬውን ጨምሮ ሶስት ጊዜ ችሎት ፊት ቀርባለች።

በመጀመሪያው የችሎት ውሎ፤ በመርማሪ ፖሊስ የቀረበውን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14 የምርመራ ቀናትን ፈቅዶ ነበር። ፍርድ ቤቱ በሁለተኛው የችሎት ውሎ፤ ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረት ይችል ዘንድ ሰባት ቀናት መፈቀዱ ይታወሳል። 

የሁለት መጽሐፍት ደራሲ የሆነችው መስከረም አበራ፤ ለእስር ስትዳረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)