የፌደራል መንግስት ለዩኒቨርስቲ መምህራን እና አመራሮች፤ ከ125 እስከ 380 በመቶ የቤት አበል ጭማሪ አደረገ  

በአማኑኤል ይልቃል

በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን ተደጋጋሚ ጥያቄ ከሚያነሱባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ በሆነው የመኖሪያ ቤት አበል ክፍያ ላይ ከ125 እስከ 380 በመቶ ጭማሪ ተደረገ። በፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተደረገውን ይህን የአበል ጭማሪ፤ የዩኒቨርስቲ መምህራን “አነስተኛ ነው” ሲሉ ተችተውታል።

በፌደራል መንግስት ስር በሚተዳደሩ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራን ከሶስት ወር በፊት በከፊል አድማ ባደረጉበት ወቅት፤ የደመወዝ፣ የአበል እና የሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበው ነበር። የዩኒቨርስቲ መምህራን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ባለፈው ጥር ወር በተወያዩበት ወቅትም፤ በሚከፈላቸው ደመወዝ እና የመኖሪያ ቤት አበል ላይ ጭማሪ እንዲደረግ ጠይቀዋል። 

የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ትላንት ረቡዕ የካቲት 8፤ 2015 ለዩኒቨርስቲዎች በጻፈው ደብዳቤ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚያስተምሩ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች እንዲሁም አመራሮች በሚከፈለው የመኖሪያ ቤት አበል ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስታውቋል። በኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር በሆኑት በአቶ ፀጋ አራጌ ተፈርሞ የተላከው ይህ ደብዳቤ፤ የአበል ጭማሪው የተደረገው “የጥቅማ ጥቅም ጥያቄን” በተመለከተ ጥናት ከተደረገ እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ መሆኑን ያስረዳል። 

በአዲሱ የመኖሪያ ቤት አበል ማሻሻያ ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገላቸው የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ናቸው። በዚህም መሰረት እስካሁን በነበረው አሰራር 2,500 ብር የመኖሪያ ቤት አበል ሲያገኙ የነበሩት የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፤ 9,500 ብር ጭማሪ ተደርጎላቸዋል።   በዩኒቨርስቲዎች በምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚያገለግሉ አመራሮች ደግሞ፤ ቀደም ሲል ይከፈላቸው በነበረው የመኖሪያ ቤት አበል ላይ  ስምንት ሺህ ብር ጭማሪ ተደርጎላቸው አስር ሺህ ብር እንደሚያገኙ በደብዳቤው ዝርዝር ላይ ተቀምጧል። 

ከምክትል ፕሬዝዳንቶች ቀጥሎ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪ የተደረገላቸው ረዳት፣ ተባባሪ እና ሙሉ ፕሮፌሰሮች ናቸው። በእነዚህ ደረጃዎች ላይ የተቀመጡ የዩኒቨርስቲ መምህራን ከዚህ ቀደም ሲያገኙት የነበረው አንድ ሺህ ብር የቤት አበል ወደ ሶስት ሺህ ብር አድጓል። የ“ሌክቸረሮች” የቤት አበል ደግሞ በአንድ ሺህ ብር ጨምሮ 1,800 ደርሷል። በአዲሱ የሲቪል ሰርቪስ የመኖሪያ ቤት አበል ማሻሻያ መሰረት ዝቅተኛ የሆነውን 1,600 ብር የቤት አበል የሚያገኙት ረዳት ምሩቅ መምህራን እና ቴክኒካል ረዳቶች ናቸው። 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በትላንትናው ዕለት ለዩኒቨርስቲዎች በላከው ደብዳቤ፤ ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር አካላት ይከፈላቸው በነበረው የኃላፊነት አበል ላይም ማሻሻያ መደረጉን ገልጿል። በዚህም መሰረት የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ይከፈላቸው የነበረው ሶስት ሺህ ብር የኃላፊነት አበል፤ በእጥፍ ጨምሮ ስድስት ሺህ እንዲሆን ተደርጓል። ለዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንቶችም በተመሳሳይ በተደረገ እጥፍ ጭማሪ 5,000 ብር የኃላፊነት አበል ይከፈላቸዋል። 

በአዲሱ ማሻሻያ፤ ከዚህ በፊት የኃላፊነት አበል የማይከፈላቸው የነበሩት የኮሌጅ ምክትል ዲኖች እና የትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊዎች ተካተተዋል። በዚህም መሰረት የኮሌጅ ምክትል ዲኖች 2,000 ብር የኃላፊነት አበል የሚከፈላቸው ሲሆን የትምህርት ክፍል ምክትል ኃላፊዎች ደግሞ 1,600 ብር ያገኛሉ። 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ለዩኒቨርስቲ መምህራን እና አመራሮች ያደረገው የአበል ጭማሪ ከተያዘው የካቲት ወር ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ፀጋ አራጌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአበል ማሻሻያውን አስመልክቶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የዩኒቨርስቲ መምህራን ግን የተደረገው ጭማሪ “በቂ አይደለም” ሲሉ የጭማሪውን መጠን ተችተዋል።   

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ አንተነህ ገረመው “መንግስት ደመወዝ መጨመር ባይችል እንኳን በዚህ ያካክስልናል የሚል እምነት ነበረን” በማለት የተደረገው ማሻሻያ እንደተጠበቀው አለመሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የመኖሪያ ቤት አበል ጭማሪው መምህራን ለቤት ኪራይ የሚከፍሉትን “ግማሹን እንኳ” እንደማይሸፍን የገለጹት የህግ መምህሩ፤ የ“ሌክቸረሮች” የቤት አበል “ቢያንስ የተጣራ አምስት ሺህ ብር ይደርሳል” የሚል ግምት እንደነበራቸው አስረድተዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የእንጅባራ ዩኒቨርስቲ መምህር በበኩላቸው የአበል ጭማሪው “በቁጥር ብዙ የሆኑትን ሌክቸረሮች ችላ ያለ ነው” ባይ ናቸው። ለዚህም በመከራከሪያነት የሚያቀርቡት፤ ለዩኒቨርስቲ አመራሮች የተደረገው የጭማሪ መጠን ለመምህራን ከሚከፈለው ጋር ሲነጻጸር “ተመጣጣኝነት የለውም” የሚል ነው። የመኖሪያ ቤት አበል ታክስ የሚቆረጥበት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት መምህሩ፤ “አይደለም ታክስ ተደርጎ፤ ታክስ ባይደረግ እንኳን የመምህራንን የቤት ኪራይ የሚሸፍን አይደለም” ሲሉ መጠኑ አስተኛ መሆኑን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)