በሃሚድ አወል
በአማራ ክልል የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር፤ በከተማይቱ ያሉትን ተፈናቃዮች ማስተናገድ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት አስታወቀ። ከሁለት ሳምንት ወዲህ ወደ ከተማይቱ የሚገቡ አዲስ ተፈናቃዮችን መቀበልም ሆነ ወደ መጠለያ ማስገባት ማቆሙንም የከተማይቱ አስተዳደር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የደብረ ብርሃን ከተማ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ባሉት ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ አራቱም የወለጋ ዞኖች እንዲሁም ከአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች። በአሁኑ ወቅት በከተማይቱ በሚገኙ በስድስት ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ 26 ሺህ ገደማ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ከከተማይቱ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ከምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ሲቡ ሲሪ ወረዳ ተፈናቅለው ለአንድ ዓመት ያህል በከተማይቱ ተጠልለው የሚገኙት አቶ አህመድ መሐመድ፤ ባለፉት 15 ቀናት ወደ ደብረ ብርሃን የመጡ ተፈናቃዮች መጠለያ ሳያገኙ መቅረታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የከተማይቱ ኃላፊዎች “ህዝቡ ሲጨምር አንመዘግብም ብለዋል” ሲሉም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ካሉበት መጠለያ ጣቢያ ሆነው የታዘቡትን አስረድተዋል።
አቶ አህመድ ከተፈናቀሉበት ምስራቅ ወለጋ ዞን፤ ጉቡ ሰዮ ወረዳ የመጡት አቶ አስናቀ ጋሻው ይህንኑ አረጋግጠዋል። በግብርና ስራ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ አስናቀ፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት የመኖሪያ ቀያቸውን ለቅቀው ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ ከመጡ ሁለተኛ ሳምንት ገደማ ቢያስቆጥሩም መጠለያ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ከሶስት ልጆቻቸው እና ባለቤታቸው ጋር “በረንዳ” ላይ እያደሩ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አስናቀ፤ “ወደ መጠለያ ሄደን ‘እኛ አንመዝግበም፤ እዚህ ሞልቷል’ አሉን” ሲሉ በመጠለያ ጣቢያ ካሉ ኃላፊዎች ያገኙትን ምላሽ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 7፤ 2015 በመጠለያ ጣቢያዎች በር ላይ በለጠፈው ማስታወቂያ፤ ከነባር ተፈናቃዮች ውጭ አዲስ ተፈናቃዮችን እንደማያስተናግድ እና እንደማይቀበል አስታውቋል። የከተማ አስተዳደሩ ተፈናቃዮችን መቀበል ያቆመው፤ “በመንግስትም ሆነ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፤ በቋሚነት ወሩን የጠበቀ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩ” መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቁሟል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ በየነ ማስታወቂያው በመጠለያ ጣቢያዎች እንዲለጠፍ የተደረገው፤ ለተፈናቃዮች የሚያስፈልጉ አገልግሎቶቹን ማቅረብ “ከአስተዳደሩ አቅም በላይ ስለሆነ ነው” ይላሉ። “የመጠለያ ቦታ የለንም። እየተጠቀምን ያለነው የግለሰቦችን የፋብሪካ ሼድ ነው። የሚመጡ ድጋፎችም በጣም ተቀዛቅዘዋል። እነዚህ ሁሉ ተደምረው ነው ማስታወቂያው እንዲለጠፍ የተደረገው” ሲሉም አክለዋል።
“ተፈናቃዩ በመንግስት ካዝና ብቻ ኑሮውን እንዲገፋ እና እንዲቀጥል ማድረግ አልቻልንም” የሚሉት አቶ ጸጋዬ፤ “ያሉትን ተፈናቃዮች የተወሰነ ቦታ ማስቀመጥ ባልቻልንበት፤ የምግብ ፍጆታቸውን ማረጋገጥ ባልቻልንበት አዲስ ለመቀበል እንቸገራለን” ሲሉ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ የደረሰበትን ምክንያት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከተማይቱ የሚገኙ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው ቦታዎች ከባለሃብቶች በጊዜያዊነት የተገኙ ሼዶች መሆናቸውን የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል። “የሼዶቹ ባለቤቶች ‘ማሽን እያመጣን ነው። ወደ ምርት አገልግሎት ልንገባ ነው። ተፈናቃዮቹን አስወጡልን’ የሚል ጥያቄ አላቸው” ሲሉም ነባር ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ጣቢያ እጣ ፈንታ ጭምር አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለተፈናቃዮች ቋሚ መጠለያ ለመስራት የሚሆን 6.5 ሄክታር መሬት ለዓለም አቀፉ ስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) መስጠቱን የሚጠቅሱት አቶ ጸጋዬ፤ ሆኖም በድርጅቱ በኩል የቀረበው ምክረ ሃሳብ በቁጥር አነስተኛ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን የሚያስተናግድ ጣቢያን መገንባት እንደሆነ አስረድተዋል። “እነሱ ‘ፕሮፖዝ አድርገው ያመጡልን መጠለያ ሁለት ሺህ ሰው የሚይዝ መጠለያ ነው። እኛ ግን ያለን 26 ሺህ ነው” ሲሉም አነጻጽረዋል።
የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መሆኑ ያሳሰበው የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር፤ ወደ ከተማይቱ የሚገቡ አዲስ ተፈናቃዮች “ወደ ሌሎች ወረዳዎች እና ዞኖች በመሄድ የራሳቸውን አማራጭ እንዲወስዱ” ባለፈው ሳምንት ባወጣው ማስታወቂያ አሳስቧል። የከተማ አስተዳደሩ ይህን ቢልም የደብረ ብርሃን ከተማን የሚያጎራብቱ ቦታዎችን በስሩ የያዘው የሰሜን ሸዋ ዞንም አዲስ ተፈናቃዮችን ማስተናገድ ከ“አቅሙ በላይ” መሆኑን አስታውቋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው መለሰ፤ “የመጠለያ እጥረት አለብን በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለነው” ሲሉ ይህንኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “[ተፈናቃዮችን] የምንመልሳቸው፤ አንቀበልም የምንላቸው የማስተናገድ አቅም ስለሌለን ብቻ ነው” ሲሉም በዞኑ ያለውን የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን ተፈናቃዮችን ከተጠለሉባቸው ቦታዎች ውስጥ ምንጃር፣ መራቤቴ፣ ሜታ፣ እንሳሮ፣ መንዝ እና ጌራ ወረዳዎች ይገኙበታል። ደብረ ብርሃን እና ሸዋሮቢት ከተሞችን ጨምሮ በአጠቃላይ በዞኑ የሚገኙ ተፈናቃዮች ብዛት 77 ሺህ ገደማ እንደሆነ አቶ አበባው ገልጸዋል። “መጠለያ ጣቢያዎች የሉንም። ወረዳዎች ከአቅማቸው በላይ ሆኗል። አሁንም ያሉትን ማስተናገድ ለእኛ ከአቅማችን በላይ ነው” ሲሉ የሰሜን ሸዋ ዞን አዳዲስ ተፈናቃዮችን ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም እንደሌለው ኃላፊው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)