የተመድ መርማሪ ኮሚሽን ስራ እንዲቋረጥ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገው ጥረት ውድቅ እንዲደረግ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ

በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለመመርመር የተቋቋመው ኮሚሽን ኃላፊነት እንዲያበቃ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት የሚያደርገው ጥረት ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ። አምነስቲ ዛሬ አርብ የካቲት 24፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ጥሪውን ያቀረበው፤ መቀመጫውን በጄኔቫ ላደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ነው።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ፍላቪያ ምዋንጎቭያ፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው ኮሚሽን ስራ እንዲያበቃ ኢትዮጵያ መፈለጓ “እጅግ አሳሳቢ ነው” ብለዋል። “የኢትዮጵያ መንግስት ጥረት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ጨምሮ፤ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ለደረሰባቸው ሚሊዮኖች ፍትህ ለመስጠት ቁርጠኝነት እንደሌለው ያሳያል” ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሯ ነቅፈዋል። 

መርማሪ ኮሚሽኑ “ሙሉ ተልዕኮውን እንዲወጣ ሊፈቀድለት ይገባል” ያሉት ፍላቪያ ምዋንጎቭያ፤ “በርካታ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ይፈጸሙበታል” የሚባለው የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሁሉንም የአገሪቱ ክፍሎች ማዳረስ ሊፈቀድለት እንደሚገባም አሳስበዋል። የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት የመርማሪ ኮሚሽኑን ኃላፊነት የሚያሰጋ ማናቸውም የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ ለማድረግ ሊተባበሩ እንደሚገባ ምክትል ዳይሬክተሯ በመግለጫው ጥሪ አቅርበዋል።

የመርማሪ ኮሚሽኑ የስራ ዘመን ስድስት ወራት ቀደም ብሎ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ የኢትዮጵያ መንግስት ማዘጋጀቱን አምስት ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከቀናት በፊት ዘግቦ ነበር። ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ፤ ኮሚሽኑ የምርመራ ውጤቶቹን ይፋ እንዳያደርግ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለውይይት እንዳይቀርብ ጭምር የሚጠይቅ ነው።

በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ይቀርባል የተባለው ይህ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ያሰሙት ንግግር፤ ጉዳዩን ከሚከታተሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ብርቱ ትችት ገጥሞታል። ከ60 በላይ የሲቪክ እና የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች በዚህ ሳምንት በጥምረት ባወጡት ጥሪ፤ የመርማሪ ኮሚሽኑ ስራ እንዲቋረጥ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገው ግፊት ውድቅ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበው ነበር። 

ድርጅቶቹ በዚሁ ጥሪያቸው፤ የመርማሪ ኮሚሽኑ የስራ ዘመን ቀድሞ እንዲቋረጥ የሚጠይቅ ማንኛውንም የውሳኔ ሃሳብ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ቋሚ እና ታዛቢ አባላት “ውድቅ እንዲያደርጉ” ጠይቀዋል። የምክር ቤቱ አባላት ለኮሚሽኑ እና ለሚያከናውነው ምርመራ ድጋፋቸውን እንዲገልጹም የጋራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን፤ ጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ምክር ቤቱ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በመጪው መጋቢት 12፤ 2015 ሪፖርት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል። መቀመጫውን በኡጋንዳ ኢንቴቤ ያደረገው እና ሶስት አባላት ያሉት ይኸው መርማሪ ኮሚሽን፤ የስራ ዘመኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት የተራዘመለት ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግስት የስራ ዘመኑ ያላበቃውን የመርማሪ ኮሚሽን ስራ እንዲቋረጥ የሚያደርገው ጥረት “ከዚህ ቀደም ያልተደረገ” ሲሉ የሲቪክ ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾቹ ተችተዋል። ይህ የኢትዮጵያ መንግስት አካሄድ፤ መንግስታት ከገለልተኛ ምርመራ እና ተጠያቂነት ለማምለጥ፤ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔዎችን በፖለቲካዊ መንገድ ለመሻገር እንደሚችሉ መንገድ የሚሳይ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።  

የመርማሪ ኮሚሽኑ የስራ ዘመን በኢትዮጵያ መንግስት ጎትጓችነት ቢቋረጥ “በሌሎች ቦታዎች የሚፈጸሙ ጥሰቶች እንዳይመረመሩ እና ተጠያቂነት እንዳይረጋገጥ” “አደገኛ ምሳሌ” ሊሆን እንደሚችል ጭምር ድርጅቶቹ ያስጠነቅቃሉ። ስጋት እና ማስጠንቀቂያ አዘሉን ጥሪ ባለፈው ማክሰኞ በጋራ ካቀረቡት 63 ድርጅቶች ውስጥ፤ ዓለም አቀፍ የትግራይ ልሂቃን እና ባለሙያዎች ህብረተሰብን (GSTS) ጨምሮ መቀመጫቸውን በአውሮፓ፣ ብሪታኒያ እና በአውስትራሊያ ያደረጉ የትግራይ የሲቪክ ድርጅቶች ይገኙበታል። 

ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅቶቹ፤ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) ጥሪውን ካቀረቡ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾቹ ሂውማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዲሁም የኬንያ፣ ዚምባብዌ፣ ሱዳን፣ ሴኔጋል እና ሩዋንዳ የሲቪክ ድርጅቶች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የጥሪው አካል ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)