የነዳጅ ግብይትን፤ ከ“ቴሌ ብር” በተጨማሪ በሌሎች የክፍያ አማራጮች ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኑ ተገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ ለሚፈጸመው የነዳጅ ግብይት፤ ከ“ቴሌ ብር” በተጨማሪ ሌሎች የክፍያ አማራጮችን ለማካተት በሂደት ላይ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ። የነዳጅ ግብይት “ሙሉ ለሙሉ” ወደ ኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት እንዲገባ የሚደረገው በመጪዎች “ጥቂት ቀናት” ውስጥ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

አሁን ባለው አሰራር፤ የነዳጅ ግብይታቸውን በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ ብቻ ሲፈጽሙ የቆዩት የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ናቸው። የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች ይህን የክፍያ ዘዴ እንዲከተሉ የተደረገው፤ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ በከፊል ብቻ እየተተገበረ በሚገኘው የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ በመሆናቸው ነው። 

በዚህም መሰረት የህዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ግብይታቸውን፤ የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በሆነው “ቴሌ ብር” አማካኝነት በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። “ቴሌ ብር” ለነዳጅ ግብይት አገልግሎት መዋል የጀመረው፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር በመሆን ከመንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ጋር በሰኔ 2014 ባደረጉት ስምምነት ነው። 

ይህን ስምምነት ተከትሎ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ 1,120 ገደማ ነዳጅ ማደያዎች ውስጥ፤ 91 በመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ዘዴን ባለፉት ሰባት ወራት ሲጠቀሙ መቆየታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ 130 ሺህ ገደማ ተሸከርካሪዎችም፤ የ“ቴሌብር” የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን በመጠቀም የነዳጅ ግብይታቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሁለት የፌደራል መንግስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ዛሬ አርብ የካቲት 24፤ 2015 በጋራ በሰጡት መግለጫ ደግሞ፤ ሁሉም ተሽከርካሪዎች በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት ብቻ የነዳጅ ግብይት እንዲያከናውኑ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቀዋል። መግለጫውን የሰጡት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሮች ናቸው። 

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አቶ አለሙ ስሜ፤ ባለፉት ሰባት ወራት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎች “በብርም፤ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴም” ክፍያ በመፈጸም የነዳጅ የግብይት እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። የግብይት ስርዓቱ የተለያየ አሰራር የሚጠቀም መሆኑ፤ የነዳጅ ድጎማው “ህብረተሰቡ ጋር መድረስ አለመድረሱን የምንቆጣጠርበት ስርዓት ላይ የራሱ ተጽእኖ አለው” ሲሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

“ለህዝብ የተመደበው ድጎማ ግለሰቦች ኪስ ሲገባ እና ተሳፋሪው ቅሬታ ሲያሰማ ይታያል” ያሉት አቶ አለሙ፤ ይህም በተለይ በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ላይ ጎልቶ የሚስተዋል መሆኑን አስረድተዋል። ይህን አይነቱን ችግር ለመቅረፍ አንደኛው መፍትሔ፤ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጀመረውን የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ግብይት በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ መተግበር እንደሆነ ሁለቱ ሚኒስትሮቹ በዛሬው መግለጫ አስታውቀዋል። 

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ይህንን ስርዓት የመዘርጋትን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፤ “በኤሌክትሮኒክስ ግብይት የፈጸመውን መልሶ ‘በካሽ የመሸጥ ወይም ደግሞ ሳይሰራ ይህንን ድጎማ የሚበላበት አሰራር ስላለ፤ አሁን ሁሉም ማደያ የሚጠቀም ባለተሽከርካሪ በኤሌክትሮኒክስ [ዘዴ ግብይት] ሲፈጸም የተወሰነ ያህል ለቁጥጥር የሚያመች ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል። በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ስርዓት የሚጀመረው፤ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች ሲጠቀሙበት በቆዩት “ቴሌ ብር” ነው።

ስርዓቱ መተግበር ከጀመረ በኋላ ግን ሌሎች የክፍያ አማራጮችን ለማካተት መታሰቡን በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የነዳጅ ድጎማ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አብዲልበር ሸምሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ከቴሌ ብር ውጪ ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ። Monopolization እንዳይኖር፣ ተደራሽነት እንዲኖር አማራጮችን ማብዛት ግዴታ ነው” ያሉት አቶ አብዲልበር፤ ወደፊት የነዳጅ ግብይት የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች የሚያመቻቸውን የክፍያ ዘዴ እንደሚመርጡ ገልጸዋል። 

የነዳጅ ድጎማ ስርዓትን ለማስተዳደር የሚያስችል ስርዓት በኢትዮ ቴሌኮም መበልጸጉን ያስታወሱት የፕሮጀክት አስተባባሪው፤ ሌሎች አማራጮች የክፍያ ቴክኖሎጂያቸውን ከዚህ ስርዓት ጋር እንዲያዋህዱ እንደሚደረግ አስረድተዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እነዚህን የክፍያ አማራጮች፤ በነዳጅ ግብይት ስርዓቱ ውስጥ ለማካተት በሂደት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)