በሃሚድ አወል
እናት ፓርቲ ዛሬ እሁድ የካቲት 26፤ 2015 ሊያደርገው የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ እንዳያካሄድ ተከለከለ፡፡፡ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው፤ “ ‘ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ መሰብሰብ አትችሉም’ ተብለናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች እና ለጠቅላላ ጉባኤው አባላት ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው አባላት እና የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ዛሬ እናት ፓርቲ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ፤ ጠቅላላ ጉባኤው ይካሄድበታል በተባለው እና በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የቅድስተ ስላሴ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተገኝተው ነበር፡፡ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ የዩኒቨርሲቲውን ህንጻ የሚጠብቁት ግለሰቦች፤ ጉባኤተኞቹን ወደ ህንጻው እንዳይገቡ ሲከለክሉ ተመልክቷል፡፡
ክልከላውን በዋናነት በህንጻው የጥበቃ ባለሙያዎች ቢደረገም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎችም በስፍራው ተገኝተው ሁኔታውን ሲከታተሉ ነበር፡፡ የፖሊስ አባላቱ ከህንጻው የጥበቃ ባለሙያዎች ጋር ሲነጋገሩም ተስተውለዋል፡፡
እናት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ከዩኒቨርሲቲው አዳራሽ መከራየቱን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ክልከላውን ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የጥበቃ ባለሙያዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ዛሬ ይካሄዳል የተባለውን የእናት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ለመታዘብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባልደረቦች እና የካሜራ ባለሙያ በቦታው ተገኝተው ነበር፡፡ የምርጫ ቦርድ ታዛቢዎች፤ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ለታዳሚዎች ያደረጉትን ንግግርም ተከታትለዋል።
የፓርቲውን ቀጣይ እርምጃ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ሰይሰፈስላሴ፤ “ለጠቅላላ ጉባኤው ተበድረን ሁሉ ከፍተኛ ወጪ ነው ያወጣነው። ይህን ክልከላ ካደረጉት አካላት ጋር እንካሰሳለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በየካቲት 29፤ 2012 ጠቅላላ ጉባኤውን አድርጎ የተመሰረተው እናት ፓርቲ፤ ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ዕጩዎችን በማቅረብ ከገዢው ብልጽግና እና ከኢዜማ በመቀጠል በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠ ነው፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)