በሃሚድ አወል
በኢትዮጵያ በሚቀጥለው ዓመት ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የሽግግር ፍትሕ፤ አጠቃላይ ሂደቱ “የተወሰኑ ዓመታት” ሊወስድ እንደሚችል የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተናገሩ። ለሽግግር ፍትሕ በአማራጭነት የቀረበው “ልዩ ፍርድ ቤቶችን” የማቋቋም ሃሳብ፤ ተጨማሪ ችግር እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ በህግ ባለሙያዎች ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከሁለት ወራት በፊት ታህሳስ መጨረሻ ይፋ ያደረገው እና “በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጮችን” የያዘው ሰነድ ላይ በ54 ከተሞች ብሔራዊ ምክክር እንደሚደረግ ተገልጿል። በዚህም መሰረት የማስጀመሪያው መርሃ ግብር ዛሬ ሰኞ የካቲት 27፤ 2015 በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል ተካሄዷል። በዛሬው መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ጌዲዮን፤ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችልበትን እና ሊወስድ የሚችለውን ጊዜ በተመለከተ ጥቆማ ሰጥተዋል።
“የተመረጠው የሽግግር ፍትህ አማራጭ፤ በሚጸድቀው ፖሊሲ መሰረት ከፊታችን ባለው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ብለን እናስባለን” ያሉት የፍትሕ ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ ሂደቱ “የተወሰኑ ዓመታት መውሰዱ የሚቀር አይመስለንም” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ሂደቱ ምን ያህል ዓመት እንደሚወስድ ግን ሚኒስትሩ ያሉት ነገር የለም።
የሽግግር ፍትሕን በተመለከተ የሚደረገውን ምክክር ባስጀመረው በዛሬው መርሃ ግብር፤ የፍትሕ ሚኒስቴር ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን ያዘጋጀው የፖሊሲ ማዕቀፍ አማራጭ ሰነድ ላይ ገለጻ ተደርጓል። ይህ ሰነድ ስለ ወንጀል ምርመራ፣ ክስ አመሰራረት፣ አጥፊዎችን ተጠያቂ ስለማድረግ፣ ስለ ምህረት፣ እርቅ እና ለተጎጂዎች የሚሰጥ ማካካሻ አማራጮች የቀረቡበት ነው።
ለፌደራል እና ለክልል የመንግስት ኃላፊዎች በቀረበው በዚህ ሰነድ ላይ ገለጻ ያደረጉት፤ ሰነዱን ያዘጋጁት የባለሙያዎች ቡድን አባላት እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባልደረቦች ናቸው። የሽግግር ፍትህ ባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ማርሸት ታደሰ፤ ስለ ሽግግር ፍትህ ጽንሰ ሃሳብ እና በኢትዮጵያ ስለተሞከሩ የሽግግር ፍትህ ሂደቶች ገለጻ አድርገዋል።
ከኢሰመኮ የተወከሉት ገለጻ አድራጊዎች በበኩላቸው፤ በኢሰመኮ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በኩል በሽግግር ፍትህ ዙሪያ ከተደረጉ የማህበረሰብ ምክክሮች የተሰበሰቡ ግኝቶችን አቅርበዋል። ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተቋማት፤ የሽግግር ፍትህ ሂደቶች አውድ ተኮር፣ ስርዓተ ጻታን ያማከለ እና ሁሉንም ህብረተሰብ የሚለውጥ መሆን እንደሚጠበቅበት በምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።
ከገለጻዎቹ በኋላ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄ እና አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል። ከእነዚህ ተሳታፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት አዲሱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ ተጠያቂነት ከማስፈን አንጻር በሰነዱ የተመላከተው ልዩ ፍርድ ቤቶችን የማቋቋም አማራጭ “ሌላ ችግር እንዳይፈጠር” ስጋታቸውን አጋርተዋል። “ልዩ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም ከተጀመረ መጨረሻው የት ይሆናል የሚል ስጋት ስላለ፤ አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላ እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ይደረግ” ሲሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
የፖሊሲ አማራጭ ሰነዱ “የፍርድ ሂደት በማን ይከናወን?” በሚለው ጉዳይ ላይ ሁለት አማራጮችን አቅርቧል። ቀዳሚው አማራጭ፤ በፌደራል ከፍተኛ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ውስጥ “ልዩ ችሎት በማቋቋም” ክሶቹን መስማት የሚለው ነው። በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት “በጥንቃቄ እንዲታይ” የተባለው ሁለተኛው አካሄድ፤ “ልዩ ፍርድ ቤት በማቋቋም ክሶችን መስማት እና ውሳኔ መስጠት” የሚል አማራጭ ይዟል።
ዛሬ ገለጻ የተደረገበት የፖሊሲ ሰነድ ራሱ፤ ልዩ ፍርድ ቤት ማቋቋም “ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ሊነሱበት ይችላል” ሲል አማራጩን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ያለውን ተግዳሮት አስፍሯል። ሰነዱ አማራጭ ባቀረበባቸው በዚህ እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙትን ሰባት ከተሞችን ጨምሮ በ54 ከተሞች የህዝብ ውይይቶች እንደሚደረጉ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)