ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ቀድመው በቁጥጥር ከዋሉ ፖለቲከኞች ጋር በአንድ ክፍል መታሰራቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ 

በትላንትናው ዕለት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ ከእርሳቸው ቀደም ብለው ከታሰሩ የተወካዮች እና የክልል ምክር ቤት አባላት ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አቶ ደሳለኝ በቤታቸው ከተደረገ ፍተሻ በኋላ ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ወደሚገኘው የእስረኞች ማቆያ መመለሳቸውንም እማኞቹ ገልጸዋል። 

ከአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ምርጫ ክልል ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ትላንት ረቡዕ ጥር 22፤ 2016 ዓ.ም. ምሽት ሶስት ሰዓት ተኩል ገደማ እንደሆነ አንድ የቤተሰባቸው አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ወደሚገኘው የዶ/ር ደሳለኝ መኖሪያ ቤት የመጡት የጸጥታ ኃይሎች በቁጥር አራት መሆናቸውንም አስረድተዋል። 

ከጸጥታ ኃይሎቹ ውስጥ ሁለቱ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ እና የጦር መሳሪያ የያዙ መሆናቸውን እኚሁ የቤተሰብ አባል ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹ ሁለቱ የሲቪል ልብስ የለበሱ ቢሆኑም ሽጉጥ ይዘው እንደነበርም አክለዋል። የጸጥታ ኃይሎቹ “ከህግ አካል መምጣታቸውን” በመግለጽ የዶ/ር ደሳለኝን የአፓርትመንት መኖሪያ ለማስከፈት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም፤ ዶ/ር ደሳለኝ እና ቤተሰቦቻቸው “ማንነታችሁን ሳናውቅ አንከፍትም” በማለታቸው በበሩ ላይ ለደቂቃዎች መቆየታቸውን በስፍራው የነበሩት የዓይን እማኝ ተናግረዋል።  

የፌደራል ፖሊሶቹ በዶ/ር ደሳለኝ አፓርትመንት ያለን የጥበቃ ሰራተኛ ጭምር ይዘው በመምጣት በሩን ለማስከፈት ተጨማሪ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን የቤተሰብ አባሉ ጨምረው ገልጸዋል። ይህ በሚከናወንበት ወቅት በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን የባለቤታቸውን፣ የልጃቸውን እና ሌሎች የቤተሰባቸውን አባላት “ጭንቀት” የተመለከቱት ዶ/ር ደሳለኝ፤ በስተመጨረሻ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ለመነጋገር ወስነዋል ብለዋል። 

ወደ ፓርላማ አባሉ መኖሪያ ቤት የዘለቁት የጸጥታ ኃይሎች፤ “ፈልገንህ ነው። ወደ ህግ ቦታ እንሂድ” በማለት ዶ/ር ደሳለኝን ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መውሰዳቸውን የቤተሰብ አባሉ አመልክተዋል። የጸጥታ ኃይሎቹ ዶ/ር ደሳለኝ የታሰሩበትን ምክንያት ሲጠየቁ “መግለጽ አልፈለጉም” ሲሉም የዓይን እማኙ ተናግረዋል። በዚህ ወቅት ዶ/ር ደሳለኝ “ሰላማዊ ፖለቲከኛ” መሆናቸውን ደጋግመው ሲያስረዱ ነበር” ብለዋል። 

የአብን የመጀመሪያው ሊቀመንበር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ፤ ዛሬ ረፋድ ሶስት ሰዓት ተኩል ገደማ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በድጋሚ ወደ መኖሪያ ቤታቸው መጥተው እንደነበር የቤተሰብ አባሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ሁለት ሰዓት ገደማ ከፈጀው ከዛሬው የቤት ፍተሻ በኋላ፤ የጸጥታ ኃይሎቹ ዶ/ር ደሳለኝ ማስታወሻ የሚይዙባቸው “አጀንዳዎች”፣ የተለያዩ ወረቀቶች፣ ፍላሽ ዲስክ፣ የሞባይል ስልክ እንዲሁም ለፓርላማ አባላት የሚሰጠውን “ታብሌት” እንደወሰዱ በስፍራው የነበሩት የቤተሰብ አባል የዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ በፖሊስ ከመያዛቸው በፊት በነበሩት ቀናት፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ሲያዘጋጁ መመልከታቸውን የቤተሰብ አባሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አራት ገጾች የፈጁትን ጥያቄዎች ለፓርላማ ማስገባት አለማስገባታቸውን ግን እንደማያውቁ አክለዋል። ዶ/ር ደሳለኝ ባለፈው ሰኔ ወር በነበረ የፓርላማ ስብሰባ፤ ጠንከር ያለ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ በተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባዎች መሳተፍ አቁመው ነበር።  

የአብኑ የፓርላማ አባል በሰኔው የፓርላማ ስብሰባ ላይ፤ በኢትዮጵያ ተስተውሏል ላሉት “ሁለንተናዊ ሀገራዊ ምስቅልቅል፣ ቀውስ፣ ውድመት” እና “ሀገራዊ መክሸፍ” የመንግስትን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን “የወደቀ አመራር” “ዋነኛ” ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል። በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስትም ሆነ ፓርላማው፤ ኢትዮጵያን “ከገባችበት የፖለቲካ ቅርቃር ማውጣት አይችሉም” ሲሉ በወቅቱ የተደመጡት ዶ/ር ደሳለኝ፤ በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲያስረክቡ እና ፓርላማው እንዲበተን ሃሳብ አቅርበው ነበር።

ከዚህ ስብሰባ በኋላ እምብዛም ድምጻቸው ሳይሰማ የከረመው ዶ/ር ደሳለኝ፤ ከእርሳቸው አስቀድመው ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ በቁጥጥር ስር የዋሉትን የአብን የፓርላማ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለን ተቀላቅለዋል። በአዋሽ አርባ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ለወራት የቆዩት አቶ ክርስቲያን፤ በአዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተዘዋወሩት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር። 

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዮሃንስ ቧያለው፤ ከአቶ ክርስቲያን ጋር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ መደረጋቸውም ታውቋል። በትላንትናው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ከሌሎች እስረኞች ተለይተው በአንድ ክፍል ከታሰሩት ከፓርቲ አጋራቸው አቶ ክርስቲያን፣ ከቀድሞው ከፍተኛ ባለስልጣን ከአቶ ዮሃንስ እና ከአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር ጋር በአንድ ላይ እንዲሆኑ መደረጋቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዶ/ር ደሳለኝ ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት ለምርመራ ሲወሰዱም የዓይን እማኞች ተመልክተዋቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)