በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት “ስርዓት አልበኝነት” (anarchy) የተበራከተው፤ በሀገሪቱ “ዲሞክራሲን የመለማመድ” እና “ነጻነትን የማስተዳደር ችግር” በመኖሩ ምክንያት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በኢትዮጵያ እንዳለው “ስድብ እና ጥፋት” መጠን “ብዙ ሰዎች መታሰር የሚገባቸው” ቢሆንም፤ “በየቀኑ እንደሚታለፉ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አብይ ይህን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 28፤ 2016 ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ነው። በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ 17 የፓርላማ አባላት ውስጥ አብዛኞቹ በሀገሪቱ ያለውን የሰላም እና ጸጥታ የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለእነዚሁ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ምላሽ ሰጥተዋል።
በዛሬው ስብሰባ ጥያቄ ካቀረቡ የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት አቶ ወልደየስ ደበበ የተባሉ ተወካይ፤ መንግስት “የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና በሃሳብ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ፉክክር እንዲኖር” የተለያዩ የህግ እና የአሰራር እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ገልጸዋል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ከመንግስት ጋር የሃሳብ ልዩነት ባላቸው አካላት እና የተለያዩ የፓርቲ እና የሚዲያ አካላት ላይ መንግስት ወከባ እያደረሰ እንዲሁም እስር እያካሄደ መሆኑ” በአንዳንድ አካላት እንደሚገለጽ ጠቅሰዋል።
“ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት አምባገነን እየሆነ ነው?” ለሚሉ አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያላቸው ምላሽ ምን እንደሆነም የፓርላማ አባሉ ጠይቀዋል። አብይ ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ የጀመሩት፤ “በመጀመሪያ ዲሞክራሲ ከሌለ የሚታየው ይሄ ሁሉ anarchy [ስርዓት አልበኝነት] ከየት መጣ?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ ነው። ስርዓት አልበኝነትን እኮ የሚወልደው ዲሞክራሲ ነው። ዲሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት እኮ ሰው በሀገሩ ብቻ ሳይሆን ከሀገሩ ውጪም ሆኖ ትንፍሽ አይልም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌሎች ሀገራት ይስተዋላል ያሉትን አካሄድ በማሳያነት አንስተዋል።
“እንደዚህ ስርዓት አልበኝነት የተበራከተው ዲሞክራሲውን መለማመድ፣ ነጻነትን የማስተዳደር ችግር ስለገጠመን አይደለም ወይ? እንደዚያ አይታሰብም ወይ?” ሲሉም አብይ በተጨማሪነት ጠይቀዋል። ዲሞክራሲ “ወጥ ትርጓሜ እና አሰራር” እንደሌለው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው የሚደግፈው “የትብብር ዲሞክራሲ” (concessional democracy) የሚባለውን አካሄድ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በህዝብ ብዛት አብላጫ የሆነው “ይግዛ”፤ አነስተኛ የህዝብ ብዛት ያላቸው ደግሞ “መብት ያግኙ” የሚለው ጥቅል የዲሞክራሲ እሳቤ፤ ብዝሃ ህዝብ ባለበት ኢትዮጵያ “አይሰራም” ሲሉም ተደምጠዋል። እሳቤው አነስተኛ የህዝብ ብዛት ላላቸው “በቂ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች “ውክልና ስለሚያስፈልግ” “መግባባት እና ሰጥቶ መቀበል” አካሄድ መከተል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
እርሳቸው የሚመሩት ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ “ቢያሸንፍም”፤ ሌሎች ፓርቲዎች ወደ አስተዳደሩ እንዲገቡ ያደረገው ይህን አካሄድ በመከተል መሆኑን ጠቁመዋል። በብልጽግና ፓርቲ ውስጥም ቢሆን በመደበኛ “የኮታ” ክፍፍል ቢኬድ “የማይታሰቡ” ውክልናን የማረጋገጥ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። “እነዚህን ካላበረታታን በስተቀር የምናስበውን ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ማየት እንቸገራለን” ሲሉ አብይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አለ ያሉትን “የዲሞክራሲ ልምምድ ማነስ” በሀገሪቱ ከሚስተዋለው “ስርዓት አልበኝነት” (anarchy) ጋር በመያያዝ በድጋሚ በማብራሪያቸው ላይ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አሁን እንዳለው anarchy፣ ስድብ እና ጥፋት፣ እስር ቢበዛ ኖሮ፤ ፓርክ ሳይሆን እስር ቤት ነው የምንገነባው” ሲሉ ተደምጠዋል። “በጣም ብዙ መታሰር የሚገባቸው ሰዎች በየቀኑ ይታለፋሉ” ሲሉም አብይ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከጽህፈት ቤታቸው አቅራቢያ በቅርቡ በተገነባ መንገድ ላይ ተፈጸመ ያሉትን ተግባር፤ ለዚህ አባባላቸው በምሳሌነት አንስተዋል። “እዚህ ሸራተን ጀርባ፤ አንድ በኢትዮጵያ ደረጃ ውብ የሚባል መንገድ ሰርተናል። ስራ ከጀመረ አስራ አምስት ቀናት ገደማ ቢሆነው ነው። በብዙ ልፋት ነው የተሰራው። ተመርቆ ሳምንት ሳይሞላ፤ ሰዎች እዚያ መተላለፊያ ላይ ቆመው ሽንት ይሸናሉ። በስንት መከራ የተሰራ ስራ ነው። እነዚህ ሰዎች ቢታሰሩ አግባብ አይደለም?” ሲሉ ላቀረቡት ጥያቄ የፓርላማ አባላቱ በሳቅ አጅበዋቸዋል።
“ለማጥፋት ነው እንጂ ካልጠፋ ቦታ እንደዚያ አይነት ቦታ ላይ ሄዶ እንደዚያ አይደረግም። ግን እኛ እስር ቤት ሳይሆን ፓርክ ነው እየገነባን ያለነው” ሲሉ አብይ አክለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ንግግር ከዚህ ቀደም በፓርላማ በተመሳሳይ ማብራሪያ ለመስጠት በቀረቡበት ወቅት፤ በቦሌ መንገድ እርሳቸው ያስተከሏቸውን አበባዎች “ሆን ብለው የሚሰርቁ ሰዎች አሉ” በሚል የሰጡትን ገለጻ ያስታወሰ ሆኗል።
የፓለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን እስር በተመለከተ የቀረበው ጥያቄ፤ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ ከሆነ የተነሳው” በሚልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ ከታሰሩ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ “ተምረው መውጣታቸውን” የገለጹት አብይ፤ “አሁን እስር ቤት ያሉት በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው” ብለዋል። እነርሱም እየተጣሩ፣ እየተማሩ፣ ሊፈቱ ይገባል” ሲሉም አክለዋል።
“የታሰሩ ሰዎች እዚህም እዚያም አሉ። ተስፋ የማደርገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚመራው ኃይል እየመረመረ፣ እያወያየ፣ እያሰለጠነ፣ አብዛኞቹን ይፈታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። መሆን ያለበትም እንደዚያው ነው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸው ላይ ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመው እና በዋነኛነት በአማራ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት የሚከታተለው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት በባህር ዳር፣ በጎንደር እና በኮምቦልቻ ከተሞች በሚገኙ “የማቆያ ስፍራዎች” ከታሰሩ ተጠርጣሪዎች ውስጥ የ706ቱ “የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ” ተመርምሮ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ዕዝ መቅረቡን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ባለፈው ሳምንት ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠቅሰው ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የሚመራው፤ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ ነው።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት የተያዙ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ “የተፈጠረ ስህተት ካለ” መንግስት “እየመረመረ ማስተካከል እንዳለበት” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው ማብራሪያቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። “ሀገር ሲፈርስ ዝም ብለን አናይም። ስራችን መጠበቅ ስለሆነ። ሀገር ጠባቂ ነን ብለን ደግሞ ጥፋት የምናመጣ ከሆነ ደግሞ መጠየቅ አለብን” ያሉት አብይ፤ መንግስት ካጠፋ “ይቅርታ መጠየቅ አለበት” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)