የአቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት በፓርላማ ተነሳ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ አባል የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለን ያለመከሰስ መብት አነሳ። ምክር ቤቱ የፓርላማ አባሉን የህግ ከለላ ያነሳው በሁለት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዐቅቦ ነው።

አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር የዋሉት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ባሳለፈበት ዕለት ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር። ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ የሚገኙት የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው፤ የፍትህ ሚኒስቴር በፍርድ ቤት ክስ ሊመሰርትባቸው በመሆኑ ነው።

የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ በዛሬው ስብሰባ ለተገኙ 245 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ፤ አቶ ክርስቲያን በጸረ- ሽብር እና በወንጀል ህግ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ “የሚያስከስስ ከባድ ወንጀል” በመፈጸም መጠርጠራቸውን ገልጸዋል።  የፓርላማ አባሉ “ከጸረ- ሰላም ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር” በአማራ ክልል ቋሪት እና ደጋ ዳሞት አካባቢዎች “በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር ለታጣቂዎች መመሪያ መስጠታቸው” በምርመራ መዝገቡ መረጋገጡን ዶ/ር ጌዲዮን አስረድተዋል።

ጥቃቱ “የሰው ህይወት ያስከፈለ” እና “የንብረት ወድመት” ያስከተለ መሆኑንም የፍትህ ሚኒስትሩ አክለዋል። አቶ ክርስቲያን “ለታጣቂዎች መመሪያ ሰጥተውባቸዋል” ከተባለባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው ቋሪት፤ አብንን በመወከል ለፓርላማ መቀመጫ ተወዳድረው ያሸነፉበት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)