የኢትዮጵያ መንግስት ለ2017 ባዘጋጀው ረቂቅ በጀት፤ 139.3 ቢሊዮን ብር ያህሉን ለዕዳ መክፈያ እንዲውል መደበ። ከዕዳ ክፍያ በመከተል ከፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት መንገድ፣ ትምህርት፣ መከላከያ፣ ጤና እንዲሁም ፍትህ እና ደህንነት ዘርፎች ናቸው።
ለፌደራል መንግስት ለቀጣዩ ዓመት የተመደበው በጀት አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋ መሆኑን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይፋ የተደረገው ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 30፤ 2016 ባደረገው መደበኛው ስብሰባው ለ2017 በጀት ዓመት 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁንም አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በፓርላማ በመገኘት ማብራሪያ የሚያቀርቡበት ይህ የበጀት መጠን፤ ከዘንድሮው በጀት በ21.1 በመቶ ወይም 169.56 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ነው። ከሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር “በተጣጣመ መልኩ መዘጋጀቱ” የተነገረለት የ2017 በጀት፤ በዋናነት “አሁን የሚታየውን የተዳከመ የፊሲካል አቋም አስተማማኝ ደረጃ ላይ የማድረስ” ግብ እንዳለው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የበጀት ማብራሪያ ሰነድ ያትታል።
“የ2017 በጀት ዋነኛ ዓላማ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቀውሶች እንዲሁም ቀደም ባሉ ዓመታት መንግስት የልማት ፕሮጀክቶቹን ፋይናንስ ለማድረግ የተከተለው አካሄድ ያስከተለውን የፊሲካል መዛባት በማስተካከል የፊሲካል ጤናማነትን እውን ማድረግ ነው”
– የ2017 በጀትን ለማብራራት ለፓርላማ የቀረበ ሰነድ
“የ2017 በጀት ዋነኛ ዓላማ ባለፉት ዓመታት የተከሰቱት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቀውሶች እንዲሁም ቀደም ባሉ ዓመታት መንግስት የልማት ፕሮጀክቶቹን ፋይናንስ ለማድረግ የተከተለው አካሄድ ያስከተለውን የፊሲካል መዛባት በማስተካከል የፊሲካል ጤናማነትን እውን ማድረግ ነው” ሲል በጀቱን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ አጽንኦት ይሰጣል።
በረቂቅ በጀቱ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው መደበኛ ወጪ ሲሆን፤ ከ2016 ጋር ሲነጻጸር በ81 ቢሊዮን ብር ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። ለፓርላማ በቀረበው ረቂቅ በጀት መሰረት የመደበኛ ወጪ መጠን 451 ቢሊዮን ብር ደርሷል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 30 ቢሊዮን ብር ያህሉ ሊሰጥ የታቀደው፤ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ዕዳ ለተረከበው የዕዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ነው።
ከረቂቅ በጀቱ ዳጎስ ያለ ድርሻ በመያዝ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የካፒታል በጀት፤ ዘንድሮ ከነበረበት 203.44 ቢሊዮን ብር ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። የካፒታል ወጪ ከአጠቃላይ ረቂቅ በጀቱ 29.2 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን፤ ወደ 283.2 ቢሊዮን ብር ከፍ ብሏል። ከዘንድሮው የ2016 በጀት ጋር ጋር ሲነጻጸር የ79.76 ቢሊዮን ብር ወይም 39.21 በመቶ ልዩነት አለው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበሩት በጀቶች እንደተስተዋለው ሁሉ፤ ከፌዴራል የመደበኛ እና ካፒታል ወጪ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በመጀመሪያው ረድፍ የተቀመጠው ለዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን ነው። በ2017 በጀት ለመደበኛ ወጪ ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ 52 በመቶውን የያዘው ዕዳ ክፍያ ነው።
የበጀት ማብራሪያ ሰነዱም “ባለፉት ሶስት ዓመታት የአገር ውስጥ እና የውጭ ዕዳ ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት ለመደበኛ ወጪው ድርሻ መጨመር ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል” ሲል ይህንኑ ያጠናክራል። ለዕዳ ክፍያ የተመደበው የገንዘብ መጠን፤ የፌደራል መንግስቱ ለዋና ዋና ወጪዎች ከያዘው 734.51 ቢሊዮን ብር ውስጥም 18.97 በመቶ ድርሻ አለው።
የዕዳ ክፍያን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የመንገድ ግንባታ፤ በቀጣዩ በጀት የተያዘለት የገንዘብ መጠን 86 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ መጠን ከዘንድሮው በጀት ጋር ሲነጻጸር በ17 ቢሊዮን ብር ገደማ ጭማሪ ያሳየ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ለተቀመጠው የትምህርት ዘርፍ 79.8 ቢሊዮን ብር ሲመደብ፤ መከላከያ በበኩሉ 65.7 ቢሊዮን ብር ተበጅቷል።
የቀጣዩ ዓመት የመከላከያ በጀት ዘንድሮ ከነበረው በ15 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው። በወጪ ድርሻው መከላከያን ተከትሎ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የጤናው ዘርፍ፤ 33.90 ቢሊዮን ብር ተመድቦታል። በረቂቅ በጀቱ ላይ ለፍትህ እና ደህንነት 27.64 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚባለው ግብርና፤ በፌደራል መንግስት ዋና ዋና ወጪዎች ዝርዝር የተቀመጠው ስምንተኛ ደረጃ ላይ ነው። ዘንድሮ ለግብርና የተመደበው የገንዘብ መጠን 19.21 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ ይህ በቀጣዩ በጀት ዓመት ወደ 22.92 ቢሊዮን ብር ከፍ እንደሚል በረቂቅ በጀቱ ላይ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)