የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ፤ “የፍርድ ቤትን መሰረታዊ ስልጣን የሚወስድ ነው” በሚል ተተቸ  

በናሆም አየለ

ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣንን ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ኃላፊ የሚሰጠው የአዋጅ ማሻሻያ፤ “የፍርድ ቤትን መሰረታዊ ስልጣን የሚወስድ ነው” በሚል ተተቸ። ማሻሻያው “ከኢሚግሬሽን ተልዕኮ እና ባህሪ የሚመነጩ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ እንጂ”፤ ፍርድ ቤት የሚያከውናቸውን ስራዎች “ደርቦ ለመስራት በማሰብ” የቀረበ እንዳልሆነ የመስሪያ ቤቱ አመራሮች ገልጸዋል። 

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት አመራሮች ይህን የገለጹት፤ ትላንት አርብ ሰኔ 7፤ 2016 በተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ ይፋዊ የህዝብ ውይይት ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። የምክር ቤቱ የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው በዚህ  ውይይት፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ለፓርላማ በቀረቡ ሶስት የአዋጅ ረቂቆች ላይ የህዝብ ጥያቄ እና አስተያየቶች ተስተናግደዋል። 

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የህግ ጥናትና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አሮን ደጎል፤ በኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ ላይ “ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣንን” በተመለከተ ስለተቀመጠው ድንጋጌ ጥያቄ አንስተዋል። “ከዚህ በፊት የነበረው ድንጋጌ፤ ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው ወይ የመዘዋወር መብቱ ሊገደብ የሚችለው በፍርድ ቤት እና በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ [ነበር] የሚለው” ሲሉ አቶ አሮን አስታውሰዋል።  

ለፓርላማ በቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ ላይ ግን “የፍርድ ቤትን መሠረታዊ ስልጣን የመውሰድ አካሄድ ነው የሚታየው” ሲሉ ዳይሬክተሩ ተችተዋል። አቶ አሮን የጠቀሱት የአዋጅ ማሻሻያው ድንጋጌ፤ ማንኛውንም ሰው ከሀገር ውስጥ እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ የሚሰጥ ነው። 

የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ እግዱን የሚጥለው “በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽ እና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን” መሆኑ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተቀምጧል። የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር የእግዱን ውሳኔ የሚያስተላልፈው፤ “ከሚመለከታቸው የደህንነት አገልግሎት እና ህግ አስከባሪ አካላት ከሚያገኘው መረጃ” አሊያም መስሪያ ቤቱ “በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት” መሆኑ በማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተወካይ አቶ አሮን “ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን የሚያረጋግጠው ማነው? ወይንስ [ዋና ዳይሬክተሩ] ማመኑ ብቻ ነው?” ሲሉ በትላንቱ ውይይት ላይ ጥያቄ ሰንዝረዋል። “በዋና ዳይሬክተሩ ዘፈቀዳዊ ስልጣን እንዳይንቀሳቀስ የታገደ ሰው ቢያንስ የይግባኝ መብትስ ሊኖረው አይገባም ወይ? ‘አላግባብ ነው የታገድኩት’ በሚል ይግባኝ የሚልበት ስርዓት ሊኖር አይገባም ወይ?” ሲሉም ተያያዥ ጥያቄ አክለዋል።

አዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ ይግባኝን በተመለከተ ያስቀመጠው ግልጽ ድንጋጌ ባይኖርም፤ “ያለ አግባብ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት እንዳይገድብ” በሚል ግን ተጨማሪ ድንጋጌ ማካተቱ በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል። ይህ ተጨማሪ ድንጋጌ፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት “ከሀገር እንዳይወጣ ያገደውን ሰው ይዞ የሚያቆይ ከሆነ ፍርድ ቤት መቅረቡን ማረጋገጥ አለበት” የሚል ነው።

ለ21 ዓመታት በስራ ላይ የቆየው ነባሩ የኢሚግሬሽን አዋጅ ለፍርድ ቤት ሰጥቶት የነበረው ዜጎችን ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ “ብቸኛ ስልጣን”፤ በማሻሻያ ላይ ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ኃላፊ ጭምር እንዲሰጥ መደረጉ በትላንቱ ውይይት ተጨማሪ ጥያቄ ተነስቶበታል። በፓርላማው የህዝብ ውይይት አስተያየታቸውን ካቀረቡት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኖህ የሱፍ የተባሉ ተሳታፊ፤ “አዋጁ የህግ የበላይነትን በህግ የመገደብ አካሄድ ያለው ይመስላል” ሲሉ ተደምጠዋል። 

“የህግ የበላይነት ከሚገለጽባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ የፍርድ ቤቶች ወይንም ደግሞ የህግ ተርጓሚው ነጻነት ነው። የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት የሚገድበው ፍርድ ቤት መሆን አለበት።  ህገ መንግስቱም እንደዚያ ነው የሚለው። ይህንን ለአንድ ተቋም የምንሰጠው ከሆነ ህገመንግስቱን እየጣስን ወይንም ደግሞ የህግ የበላይነትን እየተጋፋን እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል”  ሲሉ አቶ ኖህ አሳስበዋል።

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭ የተወሰደ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን የወከሉት አቶ ኑህ እና ሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች ላነሷቸው ትችቶች፣ ስጋቶች እና ጥያቄዎች፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል። የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ፤ ጉዳዩ መታየት ያለበት “ከብሔራዊ  ደህንነት አንጻር” እንደሆነ በምላሻቸው አመልክተዋል።  

“መደበኛው የፍርድ ቤት መንገድ ሄዶ እስከሚያልቅ ድረስ ተጓዞች ምን አልባት ሊመጡ ስለሚችሉ፤ ኢሚግሬሽን ጋር ያንን የማድረግ አስገዳጅ ሁኔታ ሊኖር ይችላል” ያሉት አቶ ጎሳ፤ “ከኢሚግሬሽን ተልዕኮና ባህሪ የሚመነጩ ገዳዮችን መነሻ በማድረግ የማገድ እንጂ፤ ሌሎች ፍርድ ቤት የሚያከውናቸውን ደርቦ የመስራት ፍላጎት እንዳልሆነ” መረዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ አዋጁ ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣንን ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ኃላፊ የሰጠው “የሚመጣብን ችግር ታሳቢ በማድረግ” መሆኑን ተናግረዋል። ድንጋጌው በአዋጅ ማሻሻያው የተካተተው “ድርስ ችግር ከሆነ፣ አደገኛ ከሆነ፤ ባለው ስርዓት ሂደቱን ተከትሎ በአጭር ጊዜ መገደብ የማይቻልበት ሁኔታ በማስረጃ ሲረጋገጥ፤ መቆም የሚችልበት መንገድ መኖር አለበት” በሚል መሆኑን አብራራተዋል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“አንድ ሀገር ነው ያለን። ሀገራችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ኢሚግሬሽን ደግሞ ለመጠበቅ የመጀመሪያው በር ጠባቂ ሆኖ የተቀመጠ ተቋም ነው። ያንን ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ መጻፍ የሚኖርበት ህግ አለ” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ የማሻሻያ አዋጁን አስፈላጊነት አስረድተዋል። “በአዋጁ ላይ ዋና ዳይሬክተር በሚል የገባው፤ [የማገድ ስልጣን] የተቋሙ የበላይ ኃላፊ መሆን ስላለበት፤ ታች ባለው ሰራተኛ  ወይንም በኦፊሰር ደረጃ ብቻ የሚወስን ተብሎ መድሎ ውስጥ እንዳይገባ ታሳቢ ተደርጎ ነው” ሲሉም አክለዋል።

በትላንትናው ይፋዊ የህዝብ ውይይት ላይ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ እጸገነት መንግስቱ፤ በውይይቱ ላይ ቋሚ ኮሚቴው ማየት የሚገባቸው “በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን” አድንቀዋል። በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሊሻሻሉ የሚገቡ ጉዳዮችን በጹሁፍ ማድረስ የሚፈልጉ አካላት፤ እስከ ቀጣይ ሳምንት ድረስ ለፓርላማው እንዲያስገቡም ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)