ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ በላይ ማናዬ እና ቴዎድሮስ ዘርፉ ከእስር ተፈቱ

በሙሉጌታ በላይ

ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ያቀረቡት ሶስት ጋዜጠኞች ከእስር ተፈቱ። ዛሬ እና ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ከእስር የተለቀቁት ጋዜጠኞች በቃሉ አላምረው፣ በላይ ማናዬ፣ ቴዎድሮስ ዘርፉ ናቸው።   

ሶስቱ ጋዜጠኞች የፌደራል ፖሊስ “ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጣስ በእስር እንዲቆዩ” ማድረጉን በመጥቀስ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት ነበር። ከአቤቱታ አቅራቢዎች አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ በላይ ከእስር የተፈታው፤ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 10፤ 2016 ከሰዓት መሆኑን ባለቤቱ በላይነሽ ንጋቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። 

“ኢትዮ ኒውስ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በላይ፤ በህዳር 2016 በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለው በኋላ ለሰባት ወራት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በእስር ላይ ቆይቷል። ጋዜጠኛው ባለፈው ግንቦት ወር አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ መዘዋወሩ ይታወሳል። 

አስር ወራትን በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ በእስር ያሳለፈው ሌላኛው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ፤ ባለፈው አርብ ሰኔ 7፤ 2016 ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ በማግስቱ ከእስር መለቀቁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። “ምኒልክ” እና “ዓባይ”በተሰኙ የበይነ መረብ እና የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻናሎች ላይ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ያዘጋጅ የነበረው ቴዎድሮስ፤ በፖሊስ ቁጥር ስር የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማ ከጸደቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር። 

ከአማራ ክልል በተጨማሪ እንዳስፈላጊነቱ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት እንዲኖረው የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በመጀመሪያ ከተቀመጠለት የስድስት ወራት የጊዜ ወሰን በተጨማሪ አራት ወራት ተራዝሞ እንደነበር አይዘነጋም። “በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ኃይል ትደግፋለህ” በሚል ምክንያት በፖሊስ መያዙን የሚገልጸው ጋዜጠኛው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላም ለ10 ቀናት በእስር ላይ ቆይቷል። 

ጋዜጠኛው ባለፈው ሳምንት አርብ ከአዋሽ አርባ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ፤ “የሲቪል ልብስ በለበሱ” ሁለት ግለሰቦች ጥያቄዎች እንደቀረቡለት ገልጿል። “ምርመራ ይሁን፤ ምን ይሁን በማታውቀው ሁኔታ ቢሮ ላይ ጠርተው ያነጋግሩሃል” የሚለው ጋዜጠኛው፤ በሁለቱ ሲቪል ግለሰቦች የህይወት ታሪኩን መጠየቁን ጠቁሟል። 

በዚህ ጊዜ ሁለቱ ግለሰቦች “ለእኛ እንደተመደቡልን፣ ኮምዩኒኬት እንደሚያደርጉን እና ወደ ፊትም እንደሚያገኙን ነግረውናል” ያለው ቴዎድሮስ፤ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ “ስልኩን እንዳይዘጋ” እንደተነገረው ጨምሮ ገልጿል። ከቴዎድሮስ ጋር በተመሳሳይ ቀን ወደ አዲስ አበባ  እንዲመጣ የተደረገው፤ ጋዜጠኛ በቃሉም ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደቀረቡለትም አክሏል። 

“አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ካሳለፈ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር። በቃሉ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ለአምስት ወራት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ታስሯል።

ጋዜጠኛው ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የተደረገ ቢሆንም፤ “ህክምናውን ሳይጨርስ” በሚያዝያ ወር አጋማሽ በድጋሚ ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ቤተሰቦቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር መናገራቸው ይታወሳል። በቃሉ ወደ አዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ባለፈው አርብ በድጋሚ እንዲመጣ ከተደረገ በኋላ ዛሬ አመሻሹን ተፈትቶ ቤተሰቦቹን መቀላቀሉን ባለቤቱ ወ/ሮ ሔለን አባተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)