ህወሓት “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገብ፤ የፍትሕ ሚኒስቴር ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቀረበ

በተስፋለም ወልደየስ

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በፓለቲካ ፓርቲነት “በልዩ ሁኔታ” መመዝገብ እንዲችል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ቀረበ። ምርጫ ቦርድ ጥያቄው ከፍትሕ ሚኒስቴር እንደቀረበለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። 

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት “ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን” እንዳረጋገጠ በመጥቀስ የፖለቲካ ፓርቲውን “ህጋዊ ሰውነት” የሰረዘው በጥር 2013 ዓ.ም ነበር። ቦርዱ በወቅቱ ባስተላለፈው ውሳኔ፤ የህወሓት ኃላፊዎች “በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉ” እገዳ መጣሉም ይታወሳል። 

የህወሓት ተወካዮች ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት በጥቅምት 2015 ከተፈራረሙ ከመንፈቅ በኋላ፤ ቦርዱ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲያነሳ ፓርቲው በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት ያቀረበው የህጋዊ ሰውነት የማስመለስ ጉዳይ “በህግ የተደገፈ ሆኖ አለመገኘቱን” በመጥቀስ ጥያቄውን “አለመቀበሉን” በግንቦት 2015 በይፋ አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሰው፤ በ2011 ዓ.ም የጸደቀውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅን ነው። በዚህ አዋጅ “ለህወሓት ህጋዊ ሰውነትን ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች” እንደሌሉ የገለጸው ቦርዱ፤ ፓርቲው እውቅና ሊያገኝ የሚችለው “በድጋሚ የምዝገባ ጥያቄ ሲያቀርብ” መሆኑን በደብዳቤው አመልክቶ ነበር።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በህወሓት ጉዳይ ያነሳውን ይህን የህግ ክፍተት የሚደፍን የአዋጅ ማሻሻያ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ አጽድቋል። የአዋጅ ማሻሻያው “በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበሩ” የፖለቲካ ፓርቲዎችን “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገቡ የሚያስችል ነው። 

“አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። 

ፎቶ፦ ፍትሕ ሚኒስቴር

የፍትሕ ሚኒስቴር ይህንኑ አዋጅ መሰረት በማድረግ፤ ህወሓት “በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል” ምርጫ ቦርድ “አስፈላጊውን ትብብር” እንዲያደርግ በደብዳቤ ጥያቄ አቅርቧል። ከሁለት ቀን በፊት ሰኞ ሰኔ 17፤ 2016 ለምርጫ ቦርድ የተላከው ይህ ደብዳቤ፤ በግልባጭ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መላኩ ተገልጿል። 

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ መድረሱን የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ “በስራ ላይ ካሉ ህጎች አንጻር በመመርመር ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ” የኮሚዩኒኬሽን ክፍሉ ገልጿል።

ከሶስት ሳምንት በፊት የጸደቀው የአዋጅ ማሻሻያ፤ “በሰላማዊ እና ህጋዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ” መስማማታቸውን ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ ያገኙ የፓለቲካ ቡድኖች፤ ማመልከቻቸውን እና አባሪ ሰነዶችን ባቀረቡ በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ምርጫ ቦርድ “ምዝገባውን ይፈጽማል” ሲል ይደነግጋል። ለምርጫ ቦርድ ከሚቀርቡት ሰነዶች ውስጥ፤ የፖለቲካ ፓርቲው “ፕሮግራም” እና “የመተዳደሪያ ደንብ” ይገኝበታል። 

የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች “በኃላፊነት ለመስራት መስማማታቸውን” የሚያስረዳ ሰነድ “በፊርማቸው ተረጋግጦ” መቅረብ እንዳለበት የአዋጅ ማሻሻያው በተጨማሪነት ያዝዛል። የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና አድራሻም እንዲሁ በምዝገባ መስፈርትነት ተቀምጧል።

ምርጫ ቦርድ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ማመልከቻ “ውድቅ የማድረግ አማራጭ” በአዋጅ ማሻሻያው አልተሰጠውም። ሆኖም “ቦርዱ አመልካቹን በቀጥታ ያለምንም ማጣራት የሚመዘግበው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በቀጣይ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርግበት ስርዓት” በማሻሻያው እንደተካተተ አዋጁ ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት የተሰራጨ የማብራሪያ ሰነድ ያስገነዝባል።

በአዋጅ ማሻሻያው የተካተተው ይህ ድንጋጌ፤ ምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ” በመዘገበው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ “ለሁለት ዓመታት” ያህል “ልዩ ክትትል” እንዲያደርግ የሚፈቅድ ነው። በዚህ መሰረት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ፤ የተመዘገበው ፓርቲ “የፖለቲካ ሰነዶቹ ከአዋጅ ማሻሻያው ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ” ማድረግ ይኖርበታል።

በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲው “ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ” ወይም “ሌሎች መሰል የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ”፤ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ትእዛዝ እንደሚሰጥ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል። ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲው “በቀሪዎቹ ጊዜያት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” ክትትል የማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ኃላፊነትም በአዋጅ ማሻሻያው ተሰጥቶታል።  

ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲው “በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ካላስተካከለ እና ጉልህ የህግ ጥሰት የፈጸመ ከሆነ” በምርጫ ቦርድ ሊሰረዝ እንደሚችል በአዋጅ ማሻሻያው ተደንግጓል። ምርጫ ቦርድ ይህን ድርጊት የፈጸመን የፓለቲካ ፓርቲ ምዝገባ የሚሰረዝው፤ “የተለየ አካሄድ ሳይከተል” መሆኑም በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)