የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በስድስት ዓመት ለአራተኛ ጊዜ አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተሾመለት

በተስፋለም ወልደየስ

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ አስተዳደር እና አመራርን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት ለተጣለበት  ኮርፖሬሽን፤ በስድስት ዓመት ውስጥ ለአራተኛ ጊዜ አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተሾመለት። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሃ ይታገሱ ናቸው።

ከመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተመሰረተው በ2006 ዓ.ም ነው። ተቋሙ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስሩ ያስተዳድራል። በድሬዳዋ የሚገኘው ነጻ የንግድ ቀጠናም በኮርፖሬሽኑ ስር ያለ ነው። 

ተቋሙን ላለፈው አንድ ዓመት ከስምንት ወራት በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አቶ አክሊሉ ታደሰ እና አዲሱ ተሿሚ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 24፤ 2016 የስራ ርክክብ ማድረጋቸውን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። ዶ/ር ፍስሃ ወደ አሁኑ የኃላፊነት ቦታ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ላለፉት ስድስት ወራት በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሰርተዋል።

ፎቶ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

ዶ/ር ፍስሃ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በነበራቸው አጭር ቆይታ ሲመሩ የቆዩት የንግድ ስርዓት እና ላይሰንሲንግ ዘርፍን ነበር። አዲሱ ተሿሚ በብዙዎች ዘንድ እውቅና ያገኙት፤ ብሔራዊ የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ጣቢያዎችን በስሩ የሚያስተዳድረውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዲመሩ በተሾሙበት ወቅት ነው። 

ኢቢሲ በእርሳቸው ኃላፊነት ወቅት፤ በአዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ አዲስ “የሚዲያ ኮምፕሌክስ” አስገንብቶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተገኙበት አስመርቋል። በ10 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ “የሚዲያ ኮምፕሌክስ”፤ ዘጠኝ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎች እንዲሁም ቢሮዎችን የያዙ ሁለት ህንፃዎች፣ አምፊ ትያትር እና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን የያዘ ነው። 

ዶ/ር ፍስሃ ከመስከረም 2015 ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር በዋና ስራ አስፈጻሚነት በኢቢሲ በቆዩበት ጊዜ፤ ተቋሙ አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻናሎችን ከፍቷል። ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነ ጹሁፍ ታሪክ በጉልህነት ከሚጠቀሱ ስራዎች አንዱ የሆነውን “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ ወደ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ቀይሮ ለማስተላለፍ ስምምነት የተፈራረመውም በእርሳቸው የኃላፊነት ጊዜ ነው። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1998 ዓ.ም. ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በሳይኮሎጂ ያገኙት ፍስሃ፤ ስራቸውን የጀመሩት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ውስጥ ነበር። ዶ/ር ፍስሃ በኢንሳ ውስጥ ለአራት ዓመታት በመረጃ ትንተና ባለሙያነት ሰርተዋል። በወቅቱ የኢንሳ አመራር የነበሩት አብይ አህመድ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፤ በእርሳቸው መስሪያ ቤት ስር የነበረውን የመረጃ ማዕከል በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተመድበዋል።   

የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል ይባል የነበረው ይህ ተቋም፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ በ2004 ዓ.ም የተቋቋመ ነው። ተጠሪነቱ ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በነበረው በዚህ ማዕከል ውስጥ ፍስሃ ለሁለት ዓመት አገልግለዋል። አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ወደ ጽህፈት ቤታቸው ካመጧቸው ወጣት የስራ ኃላፊዎች መካከልም አንዱ ፍስሃ ነበሩ። 

የ37 ዓመቱ ፍስሃ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የጥናት እና ምርምርን ስራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ጽህፈት ቤት እያሉ የጀመሩትን የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት በቅርቡ ማጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል። የዶክትሬት ዲግሪ ጥናታቸው “ልማታዊ መንግስት በኢትዮጵያ የነበረውን ተሞክሮ” የሚፈትሽ እንደሆነም አክለዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

ዶ/ር ፍስሃ ወደ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተሳቡት፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዲቨሎፐመንት ኢኮኖሚክስ ከሰሩ በኋላ መሆኑን በቅርበት የሚያውቋቸው ይናገራሉ። ከዚያ አስቀድሞ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ባገኙበት የሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ይዘዋል። 

ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ቅርብ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ወጣት የስራ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ፍስሃ፤ በተመሳሳይ መልኩ ስማቸው የሚነሳው ሳንዶካን ደበበ ይመሩት የነበረውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ከዛሬ ጀምሮ ተረክበዋል። በአሁኑ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳንዶካን የኮርፖሬሽኑ ኃላፊ ሆነው በሰሩበት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ፤ ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርፍ ማስመዘገብ መጀመሩን አስታውቆ ነበር።

ከምስረታው ጀምሮ በኪሳራ ውስጥ የቆየው ኮርፖሬሽኑ፤ በ2014 በጀት ዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን እና 340 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዘገቡ በወቅቱ ተገልጿል። አቶ ሳንዶካንን በመተካት ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ሆነው በቆዩት በአቶ አክሊሉ ታደሰ የኃላፊነት ጊዜም፤ ተቋሙ ትርፋማ ሆኖ መቀጠሉ ተነግሯል።

ፎቶ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት ብቻ፤ 992 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ባለፈው የካቲት ወር አስታውቆ ነበር። ኮርፖሬሽኑ በዚሁ ጊዜ ያገኘው ትርፍ ከ244 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ተቋሙ አመልክቷል። የመንግስት ልማት ድርጅቱ የስራ አፈጻጸሙን “አበረታች” ሲል ቢጠራውም፤ ይህ ውጤት በተገለጸ ከአራት ወራት በኋላ ግን ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ አክሊሉ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።

አቶ አክሊሉ ከዛሬው የስራ ርክክብ በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በኮርፖሬሽኑ የቆዩበትን ጊዜ “ወርቃማ” ሲሉ አወድሰውታል። በተቋሙ የነበራቸው የአመራርነት ጊዜም “ብዙ ወጤቶች የተመዘገበበት ነው” ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ “በአስተማማኝ እጅ ላይ ማረፉን” የጠቀሱት አቶ አክሊሉ፤ አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ተቋሙን “ከቀድሞ በላቀ ደረጃ” እንደሚያሳድጉት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ተሰናባቹ ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው መሾማቸውን ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ባወጣው መረጃ አመልክቷል። ይህንኑ መረጃ በፌስቡክ መልዕክታቸው ያረጋገጡት አቶ አክሊሉ፤ ሹመቱን “ትልቅ ኃላፊነት” ብለውታል። አቶ አክሊሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ከመሾማቸው በፊት፤ በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የወጣቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሊጉ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)