በሙሉጌታ በላይ
በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ባለፈው ቅዳሜ በእስረኞች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭት ሳቢያ፤ ቢያንስ አምስት ታራሚዎች መጎዳታቸውን የእስረኛ ቤተሰቦች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በዕለቱ ግጭት እንደነበር ቢያረጋግጥም፤ በክስተቱ “ቀላል ጉዳት የደረሰበት አንድ ታራሚ ብቻ ነው” ሲል አስተባብሏል።
ግጭቱን ተከትሎ በማረሚያ ቤቱ ሆነው የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ጋዜጠኞች እና ሌሎች እስረኞች ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ መደረጉን የእስረኞቹ ቤተሰቦች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በቃሊቲ ማረሚያ ቤቱ ግጭት ተቅስቅሶ የነበረው፤ ከሁለት ቀን በፊት ጠዋት ሶስት ሰዓት ገደማ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ልጃቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንደታሰረ የጠቀሱ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ ቅዳሜ ጠዋት በቤት ውስጥ እንዳሉ “የመሳሪያ ተኩስ ድምጽ” መስማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በድንጋጤ ውስጥ ሆነው ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ማረሚያ ቤት አቅጣጫ ሲሄዱ፤ በአቅራቢያው ባሉ መንገዶች “በፓትሮል የመጡ” በርካታ የፌደራል ፖሊሶች መመልከታቸውን አስረድተዋል።
በማረሚያ ቤት የታሰረ የቤተሰብ አባላቸውን ለመጠየቅ በዕለቱ በስፍራው ተገኝተው የነበሩ የዓይን እማኝም ይህንኑ አረጋግጠዋል። “የታጠቁ የፌደራል ፖሊስ አባላት ማረሚያ ቤቱን ዙሪያውን ከበውት ነበር” የሚሉት እኚሁ የዓይን እማኝ፤ “ጋሻ ነገር የያዙ፣ ሄልሜት ያደረጉ፣ የታጠቁ፣ ዱላ የሚመስል ነገር የያዙ የአድማ በታኝ ፖሊሶች” በማረሚያ ቤቱ መግቢያ አካባቢ መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
እስረኞችን ለመጠየቅ የሄዱ ቤተሰቦች፤ እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ ወደ ማረሚያ ቤት እንዳይገቡ ተከልክለው እንደነበርም አመልክተዋል። ፖሊሶች ግጭቱን “እስከሚቆጣጠሩት ድረስ” ቤተሰብ እንዳይገባ ቢከለከሉም፤ ማረሚያ ቤቱ አካባቢ ሲጠብቁ የነበሩ ቤተሰቦች ከሰዓት ስምንት ሰዓት ገደማ ተፈቅዶላቸው እስረኞቹን መጎብኘት መቻላቸውን አክለዋል።
የቅዳሜው ግጭት የተቀሰቀሰው ታራሚዎች “ከቃሊቲ ወደ ሌላ ቦታ ሊዘዋወሩ ነው” የሚል መረጃ በእስረኞች መካከል መሰራጨቱን ተከትሎ እንደሆነ በአካባቢው በሸቀጥ ንግድ ስራ የሚተዳደሩ ነዋሪ ተናግረዋል። ከማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች የሰሙትን መረጃ በመንተራስም፤ “ውስጥ ያሉ እስረኞች ወደ አባ ሳሙኤል እና ዝዋይ [ማረሚያ ቤት] ትዘዋወራላችሁ ተብለው ነው የተጋጩት” ሲሉ መንስኤውን ያብራራሉ።
እስረኞቹ የተጋጩት “በመጡበት አካባቢ እና ሰፈር ተቧድነው” እንደነበር የጠቀሱት እኚሁ ነዋሪ፤ በዚህም ሳቢያ ስምንት እስረኞች እንደተጎዱ መስማታቸውን ገልጸዋል። በግጭቱ ዕለት ወደ ማረሚያ ቤቱ አምቡላንስ ሲመላለስ መመልከታቸውንም እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
በግጭቱ ማግስት እስረኛ ለመጠየቅ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ የሄዱ አንድ ጎብኚ በበኩላቸው፤ በግጭቱ አምስት እስረኞች ተጎድተው እንደነበር መስማታቸውን “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጉዳት የደረሰባቸው ታራሚዎች በማረሚያ ማዕከል ውስጥ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ህክምናቸውን እንደተከታተሉ ጨምረው ገልጸዋል።
በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው፤ ክስተቱ “በሁለት እስረኞች መካከል የተፈጠረ ቀላል ጸብ” እንደነበር አስረድተዋል። በዕለቱ ማረሚያ ቤቱ “ዞን ሁለት” በሚባለው ቦታ ያሉ ታራሚዎች “ጎራ ለመፍጠር ሞክረው” እንደነበር የገለጹት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ ሁኔታው “ወዲያውኑ” በማረሚያ ፖሊስ አባላት አማካኝነት መረጋጋቱን አብራርተዋል።
በቅዳሜው ግጭት አንድ ታራሚ “መለስተኛ ጉዳት” እንደደረሰበት የጠቆሙት አቶ ገረመው፤ እዚያው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ ባለ ጤና ጣቢያ ህክምና እንዲያገኝ መደረጉንም አመልክተዋል። በዕለቱ የተፈጠረው ግጭት መንስኤ፤ እስረኞችን ወደ ሌላ ቦታ ከማዘዋወር ጋር የተያያዘ እንዳልነበርም አጽንኦት ሰጥተዋል።
“ቃሊቲ ማረሚያ ማዕከል ለማረም፣ ለማነጽ፣ አጠቃላይ ለጥበቃ እና ለደህንነት ስራችን ምቹ ስላልሆነ፤ ‘አባ ሳሙኤል’ ወደሚባል ደረጃውን የጠበቀ ማረሚያ ቤት ታራሚዎችን ለመውሰድ ሂደት ላይ ነን” ያሉት የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ መስሪያ ቤታቸው በዚሁ ጉዳይ ላይ ወደፊት መግለጫ እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እስረኞችን የማዘዋወር ሂደቱ ገና መሆኑን ቢገልጽም፤ ከቅዳሜው ግጭት በኋላ በዶ/ር ወንደወሰን አሰፋ መዝገብ ስር የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ የተወሰኑ ተከሳሾች ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የግጭቱ ዕለት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተወሰዱት ውስጥ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው እና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እንደሚገኙበት ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ ጋዜጠኞች በቃሊቲ ማረሚያ ቤት “ከሞት ፍርደኞች፣ ከተፈረደባቸው ታራሚዎች፣ ከባድ የወንጀል ሪከርድ ካለባቸው” ፍርደኞች ጋር ካለፈው ሚያዝያ ወር ወዲህ እንዲታሰሩ መደረጋቸውን በመቃወም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቤቱታ አስገብተው ነበር። አቤቱታው የቀረበለት ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሁለተኛ ችሎት፤ ጉዳዩን ተመልክቶ ሁኔታው እንዲስተካከል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።
ሆኖም የቃሊቲ ማረሚያ ቤቱ ይህን ትዕዛዝ “ሊፈጽም ባለመቻሉ” ተከሳሾቹ በድጋሚ ለችሎቱ አቤቱታ ማስገባታቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለፍርድ ቤት ከቀረበ የአቤቱታ ሰነድ ላይ ተመልክታለች። ይህንኑ አቤቱታ ለመመልከት ፍርድ ቤቱ ትላንት ሰኞ ሰኔ 17፤ 2016 በሰጠው ቀጠሮ፤ ጋዜጠኞቹ በችሎት ቀርበው እንደነበር ቤተሰቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)